ፀሀፊ፡ ዶ/ር ቤንጃሚን ዲን
ተረጓሚ፡ ዶ/ር በቀለ ደቦጭ
ንባብ፡ ምሩቅ ዩሐንስ
ማውጫ
- ምዕራፍ 8 የኢየሱስ ትንሣኤ አስፈላጊነቱ 00:00
- ምዕራፍ 9 የኢየሱስ ትንሣኤው ፋይዳዎች 00:00
- ምዕራፍ 10. የኢየሱስ ትንሣኤ ውጤቶች 00:00

ምዕራፍ 8
የኢየሱስ ትንሣኤ አስፈላጊነቱ
የኢየሱስ ትንሣኤ ዐዋጃዊ፣ ምሳሌያዊና መሣሪያዊ መሆኑ
የኢየሱስ ከሙታን መነሣት ከሌሎች ነገሮች ሁሉ የተለየ ታሪካዊ ሃቅ አይደለም። ክሥተቱ ለክርስቶስ ራሱ፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለዓለም ሁሉ አስገራሚ ትርጒም የሚሰጥ ነው (ባቪንክ፣ 367)። በርግጥ የክርስቶስ ትንሣኤ እያንዳድኑን የዐዲስ ኪድና ትምህርቶች የመሸፈን ባሕርይና ፋይዳ ያለው ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ የሚሰጣቸውን ጥቅሞች በተለያዩ መንገዶች መግለጽ ይቻላል። ለምሳሌ፣ ጌርሃርደስ ቮስ የተሰኘ ምሁር የክርስቶስን ትንሣኤ ከሦስት የተለያዩ ጥቅሞች አንጻር ያስቀምጣል፣
- ዐዋጃዊ ፋይዳ፥ ይህ ማለት የክርስቶስ ትንሣኤ የመታወጅ ባሕርይ ያለው ሲሆን፣ ርሱ ከሞት በመነሣት ምክንያት በማንነቱ፣ በሞቱና በትንሣኤው የሠራቸው ሥራዎች ወደ ሌሎች ሰዎች ይደርሳል ማለት ነው።
- ምሳሌያዊ ፋይዳ፥ ይህ ማለት የክርስቶስ ትንሣኤ ሥራው የሚከወንበት መንገድ ለሌሎች የክርስቶስ ተከታይ አማኞች ትልቅ ምሳሌ ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው።
- መሣሪያዊ ፋይዳው፥ ይህ ማለት የክርስቶስ ትንሣኤ መሠረቱና ጥቅሙ የርሱ አማኞች የሆኑ በሙሉ ያንኑ መንገድ ተከትለው ለሙታን ስለሚነሡ እንደ ቀዳሚ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው (ቮስ 5.47-48; Single-Volume Edition, 582-83)።
ከዚህን በተጨማሪ ዋርፊልድ የተሰኘ ምሁር የክርስቶስን ትንሣኤ ፋይዳ፣
የኢመዋቲነት እውነታ አብዮታዊ በሆነ መልኩ መገለጡ፣ ሁሉም አማኞች ማመን የሚችሉት እውነተ መንጸባረቁ፣ የሁሉም ተስፋዎች ታማኝነት መረጋገጡ፣ የርሱ የማዳን ሥራ ፍጹም የመሆን ማረጋገጫ መሰጠቱ እና እና የራሳችንን ትንሣኤ ማግኘት እንደምንችል መኻላ ማገኘታችን ለእኛ በትንሣኤው ኢየሱስ ለምናንም ሁሉ የተሰጠ መለኮታዊ ማረጋገጫ ናቸው በማለት ገልጿል።[1]
በመሆኑም፣ በመጀመሪያ የክርስቶስ ትንሣኤው ትርጒምና አስፈላጊነቱን፣ ሁለተኛ ትሩፋቶቹን፣ እንዲሁም ሦስተኛ ውጤቱን በተመለከተ ጒዳዩ በጥልቀት ልናስብበት የተገባ ነው።
እግዚአብሔር ስለ ኢየሱስ ማንነት ሙሉ የሆነ ዐዋጃዊ ዕውቅና ተጥቷል
ኢየሱስ ከሙታን ሲነሣ እግዚአብሔር የክርስቶስ ሙሉ ማንነቱ እንዲታወጅ በማድረጒ ምክንያት፣ ይህ ክሥተት ከየትኛውም ነገር በበለጠ የርሱን ማንነት ግልጽ አድርጐ ያሳየ ነበር።
የኢየሱስ መለኮታዊነቱ
በመጀመሪያ ደረጃ ትንሣኤው የክርስቶስን መላኮታዊ ባሕርዩን በመግለጥ ሙሉ ማንነቱ እንዲታወቅ ማድረግ ችሏል። የክርስቶስ መስቀል ስለ ኢየሱስ ሥራዎች ሙሉ መረዳት ማግኘት የምንችልበት መሠረታዊ እውነት ይዟል። ሞቶ የተቀበረው ኢየሱስ በሞት ኀይል ታስሮ የሚቀር አይደለም፤ ሞትን አሸንፎ በሦስተኛው ቀን ተነስቷል (ማቴ. 16፥1618፡21)። በመሆኑም ኢየሱስ አምልኮ የተገባው አምላክ ነው፤ ከእግሩ ሥር ወደቀው ሰግደውለታልም (ማቴ. 28፥9)። እነዚህ እውነቶች የሚያመለክቱት ትንሣኤው የኢየሱስን መለኮታዊ ባሕርይ መግለጡን ነው። በትንሣኤው አማካይነት የኢየሱስ መለኮታዊ ማንነቱ ግልጽ የመሆኑን እውነት ከዮሐንስ ወንጌል 20፥28 መገዘብ እንችላለን። የአራተኛው ክፍለ ዘመን ሂላሪ፣ ኢየሱስ ከሙታን ሕይወት አግኝቶ የተነሣው በተፈጥሯዊ መንገድ ሳይሆን በራሱ መለኮታዊ ሥልጣን ነው ማለቷ ትክክል ነበር።[2]
በተጨማሪም ቮስ ይህን እውነት፥
ርሱ በሞት ተሸንፎና ለዘላለም ሟች ሆኖ ያለመቅረቱ እውነት በራሱ አሳማኝ በሆነ መልኩ የመለኮት ባሕርይ የተጐናጸፈ መሆኑ ማሳያ ነው። ማንኛውም ተራ ፍጡር ቢሆን ኖሮ በሞት ተውጦ በቀረና እንደገና በሕያዋን ዓለም ራሱን ከፍ አድርጐ ባልገለጠ ነበር። ከዚህ በተቃራኒ ግን፣ ርሱ በሞት ኀይል ተይዞ አልቀረም
በማለት ገልጾ ነበር።[3]
ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክት መግቢያው ላይ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ሲያወሳ፣ ዋና ትኩረቱን ሰዋዊነቱ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ከእዚአብሔር ጋራ እኩል በሆነበት መለኮታዊ ማንነቱ ላይ ጭምር ትኲረት አድርጐ ነበር። ጳውሎስ የትንሣኤውን ኢየሱስ፣ “በቅድስና መንፈስ ደግሞ ከሙታን በመነሣቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በኀይል ስለ ተገለጠው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” በማለት ይገልጸዋል (ሮሜ 1፥3-4፤ በተጨማሪም 9፥5 ይመ.)።
ትንሣኤው ልጁ ከአባቱ ጋራ አንድ መሆኑን ስለሚያመለክት፣ በክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት የተገለጠው የእግዚአብሔር ሥራ ለሥላሴ አስተምህሮ መሠረት ነው (ዮሐ. 10፥30፤ 17፥11፤1፥1፡14፤ 3፥18፤ 10፥34-38፤ 12፥45)። በመሆኑም፣ ትንሣኤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአባቱ ከእግዚአብሔር አብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ የተሳሰረ መለኮታዊ ማንነት እንዳለው መገለጫ ነው።
ዘላለማዊ ልጅና መሲሓዊው ንጉስ
ኢየሱስ በትንሣኤው ምክንያት መሲሓዊ ንጉሥ፣ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ልጅ፣ ጌታና መለኮት መሆኑ ተገልጧል (ሮሜ 1፥3-4)። በርግጥ፣ “ክርስቶስ” የሚለው ስም መሲሓዊ መጠሪያ ነው። ይህ መሲሓዊ መጠሪያ ደግሞ በብሉይ ኪዳን ተስፋ የተሰጠው ነው። ይህ የብሉይ ኪዳን ተስፋ ለወደፊት የእግዚአብሔር የማዳን ውጥን ከግብ የሚያደርስ መሲሕ እንደሚመጣ ያትታል። “ክርስቶስ የሚለው መጠሪያ በዐዲሱ መደበኛ ትርጒም፣ በተለይም በማርቆስ ወንጌል መግቢያ መሲሑ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ አጽንኦት ሰጥቶ ተገልጧል።
የብሉይ ኪዳንን ታሪካዊ ዳራ ስንመለከት ስለ ካህናት፣ ፈራጆች፣ ነገሥታትና ነቢያት መነሣት ያወሳል። ከዚህ በተቃራኒ ግን ዐዲስ ኪዳን በግሪኩ በግሪኩ egeiro እና anhistēmi የሚሉ ቃላትን በመጠቀም ኢየሱስ ክርስቶስ በልዩ ዐይነት አገልግሎት ስለመቀባቱ ይናገራል። ማርቆስ 15፥34 ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቱ በእግዚአብሔር ጭምር ስለ መረሳቱ ወይም ስለ መተዉ ሲናገር፣ በተቃራኒው ደግሞ ማርቆስ 16፥6 ላይ መልአኩ በመቃብር ስፍራ ለተገኙ ሴቶች ኢየሱስ በመቃብር ውስጥ እንደሌለና ከሙታን እንደተነሣ ሲያበስር የተጠቀመው ēgerthē የሚል ቃል ነበር። ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ የተነገረው ይህ እውነት ርሱ በግልጽ በሚታይ መልኩ መነሣቱን ብቻ ሳይሆን፣ ክፉውብ የሚበቀል መሲሕ መሆኑንም ጭምር ነው። ይህ የኢየሱስ መሲሓዊ ማንነቱ የክህነት፣ የንጉሥነትና የነቢይነት ሥልጣን የያዘ ነው። በተጨማሪም እንደ ቶራንስ ገለጻ ከሆነ፣ የክርስቶስ ትንሣኤ ርሱ በታላቅ ክብር በዙፋኑ ላይ መውጣቱንና ክርስቶስ ሆኖ መሾሙን የሚያሳይ ነው (ቶራንስ፣ 33)። ይህ የሚያሳየው ክርስቶስ የነቢይነት፣ የክህነትና የንጉሥነት አገልግሎት እንዳለው ነው። በተጨማሪም ክርስቶስ ክፉውን ሁሉ የሚበቀልና የሰው ልጆችን ታሪክ በሙሉ የሚያጠቃልል መሲሕ ነው፤ በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጅ በሙሉ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ተመደበለት ስፍራ የሚሄድበትን ፍርድ የሚያውጀውም በ መሲሑ ክርስቶስ ትንሣኤና ፍርድ መሠረት ነው (ዮሐ. 11፥24-25)።
ክርስቶስ ሞት ቢቀር ኖር ከማንኛው ሰው የተለየ ታሪክ አይኖረውም ነበር። ነገር ግን ርሱ ሞትን ድል አድርጐ ስለ ተነሣ፣ ከሳሾቹ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መናገሩ ሐሰት እንደሆነ አድርገው ቢከሱትም፣ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆኑ እውነት በትንሣኤው ተረጋግጧል (ሉቃ. 4፥3፡9፤ 22፥70-71)። ባቪንክ ይህን እውነት፣ ከሳሾቹ ኢየሱስን እግዚአብሔርን ተሳድቧል ብለው የሞት ፍርድ በማስተላለፍ ቢገድሉትም (ማር. 14፥61-64)፣ በርሱ ላይ የተላለፈ ፍርድ ግን የሞት ፍርድ ሳይሆን፣ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ፍርድ ነበር በማለት ገልጿል (369)። ይህ እውነት የሚያሳየን፣ ኢየሱስ በኀይልና በፍጹምነት የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ነው (ሮሜ 1፥4፤ በተጨማሪም ዮሐ. 2፥19 ይመ.)።
የክርስቶስ ከሙታን መነሣት የመሲሕነቱ ማረጋገጫ እንደሆነ ሐዋርያት ተረድተው ነበር (ሐዋ. 2፥22-24፡36)። ትንሣኤው በዲያቢሎስ ለተጨቆኑት ሁሉ ፈውስና ነጻ መውጣት የተገለጠበት መልካም የምስራች፣ ለድንቆቹና ለተኣምሮቹ ዕውቅና የሚሰጥ ክሥተት ነው። በሐዋርያቱ አማካይነት ይደረግ የነበረው ተኣምርና ነጻ መውጣት እግዚአብሔር በኀይል ከሙታን አስነሥቶ በቀባው የትንሣኤው ክርስቶስ የተደረጒ ነበሩ (ሐዋ. 10፥38)። ይህ የትንሣኤው ኢየሱስ በርሱ ለሚያምኑ ሁሉ ሕይወትና ብርሃን (ሐዋ. 3፥15)፣ የተቀባ ንጉሥ (ሐዋ. 4፥16)፣ የድኅነት ሁሉ መሪ (ሐዋ. 5፥31) እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈርድ ጌታ (ሐዋ. 10፥42) ሆኖ ተገለጠ።
በርግጥ የክርስቶስ ንግሥና የጀመረው በፍጥረት ነበር (ዮሐ. 1፥1-4፤ ቈላ. 1፥15-20፤ ዕብ. 1፥1-3)። ርሱ ከዘላለም ከእግዚአብሔር አብ ጋራ የነበረ ሲሆን፣ በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ የዘላለም ንጉሥ ነው። ፍጥረት ሁሉ ከርሱ አገዛዝና ቊጥጥር ሥር ነው። ይህ ዘላለማዊ ንጉሥ ኀጢአተኛ፣ ዐመፀኛውንና የጠፋውን ፍጥረት ለማዳን ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጣ። የዘላለማዊ ንጉሥነት ክብሩ በሰውነቱ ውስጥ ተሰወረ። ሰው የሆነው መለኮት ተዋረደ፣ ተጠላ፣ ተሠቃየ በመጨረሻም ተገደለ። የባሪያ መልክ ይዞ በመምጣቱ ምክንያት ንጉሣዊና መለኮታዊ ግርማው ተሰውሮ ነበር።
እንደ ኦደን አገላለጽ ከሆነ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ አገልግሎቱ ዘመን ሁሉ ማንነቱ ለሁሉም እንዲገለጥና ጒዳዩም ርግጠኛ እንዲሆን እየጠበቀ ነበር። ኦደን፥
ኦደን እንዳለው፡- ጌታ ኢየሱስ በመላው የምድራዊ አገልግሎቱ ዘመን ሙሉ ማንነቱ ለሁሉም እንዲገለጥና ጉዳዩም እርግጠኛ እንዲሆን ጊዜ እየጠበቀ ነበር፡፡
በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት የኢየሱስ ማንነት (እንደ ራሱ ምስክርነት ከሆነ) ወደፊታዊ ማረጋገጫ ይጠብቅ ነበር። እውነተኛ ማንነቱን እንዲገልጥ ለሚገፋፉ ኀይላት ቅጽበታዊ ምላሽ አልሰጠም ነበር። በአገልግሎት ዘመኑ የገለጠው ማንነቱ ወደፊት በግልጽ እንደሚረጋገጥ ዘወትር ያስብ ነበር ይላል።[4]
ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ አገልግሎት ዘመን እጅግ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቷል፣ ድንቅ ትምህሮቶችን አስተምሯል። የስሙና የማንነት የመጨረሻ መገለጫው በሙታንና በሕያዋን ላይ ፈርጆ የዓለምን ታሪክ የሚዘጋበት ክሥተት ነው (ራእ. 22፥10፤ስቲቨን ሞትየር፣ Apollos, 2016)። ይሁን እንጂ ትንሣኤው የኢየሱስ ማንነትና የንጉሥነት ዐዋጁ ልዩ መገለጫው ነው። ይህ ማንነቱና የንጉሥነት ዐዋጁ ደግሞ ርሱ ሰማይንና ምድርን የሚጠቃልል መሆኑን ማረጋገጫ ነው። በተለይም በዚህ ተግባሩ ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅና መካከለኛ ንጉሥ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል (ሮበርት ሌተም፣ 1993፡220)። የክርስቶስ ልዩ መገለጫ አድርገን ልንወስደው የተገባው ነገር፣ ርሱ ከሥቃዩና ከሞቱ በኋላ (ሉቃ. 24፥26) ከሠራዎች ድንቅ ሥራዎች አንዱና ዋናው የኀጢአት ይቅርታ በርሱ አማካይነት መገኘት መቻሉና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ መስጠቱ ነው (ሐዋ. 2፥33፡38)። ርሱ ኀጢአተኞችን ከአብ ጋራ አስታርቋል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች በአጭሩ ሲገለጹ፣ ትንሣኤውን ተከትሎ የኢየሱስ ክርስቶስ ልዩ መሲሓዊና ንጉሣዊ አገዛዙ፣ እንዲሁም ርሱ የእግዚአብሔር የማዳን ኀይል ልዩ መገለጫ መሆኑ ሊገለጥ ችሏል።
ኢየሱስ ጌታ ነው
የኢየሱስ ክርስቶስ ጌትነት የተገለጠው ኀጢአትንና ሞትን በማሸነፉ ብቻ ሳይሆን፣ በትንሣኤው አማካይነት የትኛውም ኀይል ሊቋቋመው በማይችል መልኩ አሁናዊ አገዛዙ ግልጽ ሆኖ በመታየቱም ጭምር ነው። የትንሣኤው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ፣ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” በማለት የትንሣኤውን ድል ክብር አብስሯል (ማቴ. 28፥18)። ይህ የትንሣኤ ድልና ክብር ደግሞ በምድር ላይ የተቀበላቸውን መከራዎችና ሥቃዮችን ሁሉ ተቃርኖ የሚቆም ነው።
የክርስቶስ ማእረግ፣ ሥልጣኑና በምንም ሊገደብ የማይችለው ሰማይና ምድርን የሚተቀልለው ኀይሉ በትንሣኤ አማካይነት ተገልጧል። በሌላ ቋንቋ፣ የክርስቶስ ትንሣኤ ርሱ የሁሉ የበላይ ስለመሆኑ ዕውቅና ያገኘበት ነው (ጆኤል ቢል፣ 202፣ 2፡1129)። በእግዚአብሔር ኀይል ከሙታን የተነሣና በክብር ከፍ ከፍ ያለው፥ የድነት ምንጭ፣ መሠረትና ራስ የሆነው ክርስቶስ ከዚያ በፊት የተናቀው፣ የተነቀፈውና በግፍ የተገደለው ኢየሱስ ነበር (ሐዋ. 3፥13፤ 4፥10-12)። ይህ የትንሣኤ ጌታ በክርብ ከፍ ያለ የዓለም ሁሉ መሪና አዳኝ ነው (ሐዋ. 5፥31)። በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “የተቀመጠውም ከግዛትና ከሥልጣን፣ ከኀይልና ከጌትነት እንዲሁም በአሁኑ ዘመን ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዘመን ቢሆን ሊሰየም ከሚቻለው ስም ሁሉ በላይ ነው” ይላል (ኤፌ. 1፥21)።
በዐዲስ ኪዳን በተለያዩ ምንባባት ከመቶ ጊዜያት በላይ አጽንኦት ተሰጥቶ ከተጠቀሱ እውነቶች አንዱ፣ “ኢየሱስ ጌታ” እንደሆነ የሚያወሳ ሲሆን፣ ይህም ርሱ ሕያው ሆኖ የሚኖር ዘላለማዊ አምላክ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ይህ እውነት ደግሞ በትንሣኤው ላይ የተመሠረተ ነው። ይህን እውነት ጳውሎስ፣ “ለዚሁ፣ የሙታንና የሕያዋን ጌታ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ ሞቷል፤ በሕይወትም ተነሥቷል” በማለት ይገልጻል (ሮሜ 14፥9)። በመሆኑም ትንሣኤው የጌትነቱ መገለጫ ነው። በተጨማሪም ዋርፊልድ፥ በትንሣኤው አማካይነት ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ መሆኑ ተረጋግጧል፤ በዚህም ምክንያት ርሱ ሁሉም የሚገዛና ሰማይና ምድርን በክንዱ ደግፎ የያዘ ሆኗል ይላል (545)። ሁሉን ባጠቃለለ የክርስቶስ አገዛዝና ሥልጣን ላይ ወደ ተመሠረተውና ወደ ተደገፈው ዓለም የክርስቶስ ወንጌል ዘልቆ መግባት የሚችለውን በትንሣኤው ኢየሱስ ሥልጣን ነው። ደቀ መዛሙርቱን ለዚህ የወንጌ ሥራ ሥልጣን ሰጥቶ የላቸው የትንሣኤው ክርስቶስ ነው። ይህ በሰማይና በምድር ሥልጣን ያለውና ሁሉን የሚገዛ ጌታ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከላካቸው ደቀ መዛሙርቱ ጋራ እንደሚሆን ተናግሯል (ማቴ. 28፥20)። የትንሣኤው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ዓለም ሁሉ በመሄድ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ እንዲሰብኩ ትእዛዝ መስጠቱ፣ ይህ የትንሣኤው የምስራች ርሱ በሚገዛው ምድር ለሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ያለ ምንም ልዩነት እንዲዳረስ መፈለጒን ነው (ሊዮን ሞሪስ 1992፡746)።
የትንሣኤው ክርስቶስ ሁሉ ቻይ የሆነን መለኮታዊ ሥልጣኑን በከንቱ አይጠቀምም። ርሱ ይህን ሰማይና ምድርን ያጠቃለለ ሥልጣኑን በሰይጣንና በክፉ መናፍስት የተያዘውን፣ በኀጢአተኛ ዐመፀኛ የሰው ልጆች የተባላሸውን ዓለም ለማዳን ይገልጠዋል (ኤፌ. 1፥21፤ 6፥12፤ ራእ. 12፥717)። የክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጆችንና የክፉ መላእክትን የዐመፀ ተግባር በመደምሰስ የድል ዙፋን መሥርቷል። ጳውሎስ ይህን እውነት፣ “እግዚአብሔርም ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛለት፤ በቤተ ክርስቲያንም በማንኛውም ነገር ላይ ራስ አድርጎ ሾመው” በማለት ይገልጣል (ኤፌ. 1፥22)። በተጨማሪም ባቪንክ እንዳተተው ክርስቶስ ኢየሱስ የሕይወት ሁሉ ራስ፣ የድነት ምንጭና በሕያዋንና በሙታን ሁሉ የመፍረድ ሥልጣን እንዲኖረው በእግዚአብሔ የተሾመ ፈራጅ ንጉሥ ነው (ባቭንክ፣ 370፤ በተጨማሪም ሐዋ. 3፥15፤ 4፥12፤ 10፥42 ይመ.)።
እግዚአብሔር ለኢየሱስ ትምህርት ዕውቅና ሰጠ
የኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱ ልዩ በሆነ መልኩ በድንቅና ተኣምራት የተጀበ መሆኑ እግዚአብሔር ስለ ርሱ ማንነት ዕውቅና ስለመስጠቱ ማረጋገጫ ነው (ሐዋ. 2፥22)። በተጨማሪም በሕዝብ ሁሉ ፊት በአደባባይ የተገደለውን ኢየሱስን እግዚአብሔር በተኣምራዊ ኀይሉ ከሙታን በማስነሣት ከፍ ከፍ አደረገው (ሐዋ. 2፥23-24፡32)።
የክርስቶስን የአደባባይ ሕይወትና አገልግሎቱን በተመለከተ ከትምህርቶቹ በቀላሉ መረዳት እንችላለን። ትምህርቱን አንዳንዶች በመደነቅና በደስታ ሲቀበሉት፣ በሌሎች ዘንድ ግን ንዴትና ቁጣ ፈጥሯል (ማቴ. 21፥12-17)። ከሁሉ በላይ ደግሞ የርሱ የቅርብ ወዳጆቹ በሆኑት ዘንድ ጭምር ትምህርቱ ግራ የሚያጋባ ሆኖ ተስተውሏል (ዮሐ. 6፥60)። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሙታን በማስነሣት ርሱ በሕይወት ሳላ ያስተማራቸው ትምህርቶች በሙሉ ትክክል ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ሊሰጥ ችሏል (ሃበርማስ፣ ምዕራፍ 2-6)። በሌላ ቋንቋ የኢየሱስ ትንሣኤ የትምህርቶቹ ትክክለኛነት ማረጋገጫ ነው ማለት ይቻላል። በተጨማሪም ትንሣኤው ትምህርቶቹን በምንረዳባቸው መንገዶች ላይ ዐዲስ ብርሃን ፈንጥቋል። ትንሣኤው የኢየሱስ ትምህርቶችና ተስፋዎች ርግጠኛ እንደሆኑ ማጽኛ ሰጥቷል። ለዚህ ሁሉ ዋናው መሠረት ደግሞ የክርስቶስ መለኮታዊ ማንነት ባሕርዩ ነው። በመሆኑም ክርስቶስ ኢየሱስ በትንሣኤው አማካይነት በተለያዩ ስፍራዎች ላስተማራቸው ትምህርቶች፣ ለሰጣቸው ተስፋዎችና ትእዛዛት መለኮታዊ ማረጋገጫ ማህተም አኑሯል ማለት ይቻላል።
ትምህርቶችና ትንሣኤው ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደነበረ ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ማን እንደሆነም ማሳያ ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሞቱ በፊት ለሚቃወሙት ሰዎች ትንሣኤውን በተመለከተ በምሳሌ ያስተማረ ሲሆን፣ በተለይም ደግሞ በምድር እንብርት ለሦስት ቀንና ሌሊት እንደሚቆይ የተናገረውን ነገር በዋናነት መጥቀስ ይቻላል (ማቴ. 12፥38-40)። ይህ ትምህርት በጊዜው ከፊቱ ቆመው ለሚሰሙ ሰዎች ምንም ትርጒም ሊሰጥ ባይችልም፣ የተናገረው ነገር ግን ከብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ጋራ ትስስር ያለው ነገር በመሆኑ ሊፈጸም ችሏል። የክርስቶስ ትንሣኤው በራሱ በክርስቶስ የተነገረ ብቻ ሳይሆን በብሉይ ኪዳንም ጭምር የተተነበየ በመሆኑ ተፈጻሚነትን አግኝቷል (ማቴ. 28፥6)።
ያለ ክርስቶስ ትንሣኤ የትኛውም ዐይነት ትምህርት እንደ አቧራ ብናኝ የሆነ ከንቱ ነገር ነው። ትንሣኤ ባይኖር አይደለም የሌሎች ሰዎች ትምህርት ይቅርና የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች ራሳቸውም ቢሆኑ ከንቱ መሆን በቻሉ ነበር። ሞቶ ከሙታን እንደሚነሣ አስቀድሞ የተናገረ በመሆኑ ትንሣኤው የኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኝነት ብቻ ሳይሆን ርሱ ከሰው ልጆች ሁሉ ተለይቶ የእግዚአብሔር ተወካይና እውነተኛ ምስክር ነቢይነት መሆኑን ጭምር ያረጋግጣል። እግዚአብሔር ሰው ሆኖ የተናገረው ሁሉ እውነተኛ መሆኑ የታወቀው በትንሣኤው ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ቃል መገለጥና በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የግንኙነት መስመር ነው፤ የዚህን ሥራ እውነተኝነት ያጸናው ደግሞ ትንሣኤው ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስን በመተለከተ እግዚአብሔር፥ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ ርሱን ስሙት” የሚል ምስክርነት ሰጥቶ ነበር (ሉቃ. 9፥35)። ሞትን ድል አድርጐ የተነሣው ኢየሱስ ዘወትር እየታሰበ ሊኖር የተገባው በመሆኑ ምክንያት ደቀ መዛሙርቱ ትንሣኤውን ለዓለም ሁሉ እንዲሰብኩ አሳሰባቸው፤ በርግጥ ደግሞ ርሱ ራሱ ደግሞ ተመልሶ እንደሚመጣ ተስፋ ሰጥቷል። ርሱ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ትእዛዛት እውነትና ርግጠኛ መሆናቸውን ከዐይን ምስክሮች መረዳት ይቻላል (ማቴ. 28፥19-20፤ ሉቃ. 24፥44-49፤ ዮሐ. 20፥17-19፤ ሐዋ. 1፥30)። እነዚህ ትእዛዛት ርሱ በምድር በነበረበት ጊዜ ያደርጋቸው የነበሩ ትምህርቶችና አገልግሎቶች ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ ዋስትና የሚሰጡ ነበሩ።
ከሐዋርያት ትምህርት ማእከላዊው እውነት ከሥራዎቹና አገልግሎቶቹ አንጻር ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ከሁሉ በላይ የዚህ ማንነት ዋና ማጽኛው ትንሣኤው ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው አማካይነት የማንነቱንና የትንሣኤውን ምስጢር ለሐዋርያቱ ግልጽ አድርጐ ነበር። የሐዋርያት አገልግሎትና ትምህርት በዋናነት በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ የተመሠረተ ነበር። ከትንሣኤው በኋላ የተገለጡ የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጦች የርሱን ማንነት በሚገባ የሚገልጡ ነበሩ። በትንሣኤው አማካይነት የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ተገልጧል ማለት ተከታዮቹ ርሱን ፊት ለፊት በዐይናቸው አይተውታል ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ያስተምራቸው የነበረው ትምህርት እውነትነትና ዋናውን ዓላማ በሚገባ ተረድተዋል ማለትም ጭምር ነው (ዮሐ. 21፥1)።
እግዚአብሔር ለክርስቶስ የመስተሠሪያ ሥራ ቤዝዎታዊ ዋጋ ማረጋገጫ ሰጥቷል
የክርስቶስ ትንሣኤው በአደባባይ የተደረገ አሳፈርም በሥቃይ የተሞላ የዐመፀ ድርጊት ውጤት የሆነውን ሞት ተከትሎ የመጣ ነው። ከዚህም የተነሣ የክርስቶስ ሞት የሰውም ሆነ የእግዚአብሔርን ቁጣ ውጤትና ያበቃለት ጒዳይ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ደግሞ ትንሣኤው የሰው ልጆችና የተፈጥሮን ሕግጋት በሙሉ ጥሶ ባልተጠበቀ መንገድ የእግዚአብሔር ኀይል፣ ዓላማና አሠራሩን የገለጠ ክሥተት ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ የአስደናቂ ሞቱ ውጤት ሲሆን፣ የትንሣኤው ድል ደግሞ የክርስቶስ ድል፣ የእግዚአብሔር ኀይልና የማዳን ሥራ ማሳያ ነው (ሐዋ. 2፥23-24)።
የክርስቶስ ትንሣኤ የሞት ፍርዱን የቀለበሰ ክሥተት ነው። የክርስቶስ ሞት የርሱን እስከ ሞት ድረስ የታዘዘበትን ፍጹም መታዘዝ ሲያሳይ፣ ትንሣኤው ደግሞ የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያሳያል። ኢየሱስ የመዋጀትን ሥራ ከግብ ያደረሰው በሞቱና በትንሣኤው ነው። ስለዚህም ነው ቮስ የተሰኘ የነገረ መለኮት ሊቅ፣ “እግዚአብሔር አምላክ ክርስቶስን ከሙታን ሲያስነሣው የክርስቶስ መታዘዝ በሁሉም አቅጣጫ ግቡን ሊመታ ችሏል” ያለው (ቮስ፣ 582)። በመሆኑም ኢየሱስ በሞቱም ሆነ በትንሣኤው በሁለቱም የተሳካለት ነበር። ከዚህ እውነት የምንረዳው የክርስቶስ ሥራ ግቡን እንደመታ እና የመዋጀት ተግባሩም በትክክል እንደተከናወነ ነው።
የመሥዋዕታዊ ፍቅር ኀይል
ከክርስቶስ ሕዝቡን የመዋጀት ሥራ ጋራ በተያያዘ በላቀ መልኩ ሊተሰብበበትና ሊደነቅ የሚገባው እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞት ፍቅሩን መግለጥ የመቻሉ እውነት ነው (ዮሐ. 3፥16-17፤ ሮሜ 5፥6-8፤ 1ዮሐ. 4፥8-10)። ይህ እውነት በቤዝዎት ተግባር ውስጥ እግዚአብሔር አብና ወልድ ያላቸውን መለኮታዊ አንድነትና ፍቅር የሚያሳይ ሲሆን፣ እግዚአብሔር ለኀጢአተኛ የሰው ልጆች የገለጠውን የማዳን ሥራውንም የሚገልጥ ነው። በክርስቶስ ሞት አማካይነት የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ጋራ ይታረቁ ዘንድ እግዚአብሔር ጠላቶቹ የሆኑ የሰው ልጆችን ወደደ (ሮሜ 5፥10)። በመሆኑም የክርስቶስ ትንሣኤ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፍቅር መገለጫ ነው።
በእግዚአብሔር ተረግሞ ሞተ በእግዚአብሔር ከሙታን ተነሣ
ክርስቶስ ርሱ ራሱ አምላክ ሆኖ ሳለ ከእግዚአብሔር ጋራ መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር ሳይቆጥር የባሪያን መልክ ይዞ ሰው ለመሆን እሰከመታዘዝ ዝቅ አለ (ፊልጵ. 2፥6-8)። በትሕትና ራሱን ዝቅ አደርጎ እስከ ሞት የታዘዘውን ኢየሱስን እግዚአብሔር አብ በትንሣኤው ከፍ ከፍ አድርጐ አከበረው። ኢየሱስ በእናቱ ማኀፀን ሰው ሆኖ ከተፀነሰበት ጊዜ አንሥቱ ሞቱ እስኪቀበር ድረስ ያለው ሕይወት የዝቅታውንና የመዋረዱን ጥልቀት ያሳያል። ከዚህ አሳፋሪ ውርደት እግዚአብሔር አብ ኢየሱስ በትንሣኤው አማካይነት በክብር ከፍ ከፍ አደረገው።
የመስቀል ሞት የእግዚአብሔር ሕግ የጣሱ ወንጀለኞች ከታላቁ የእግዚአብሔር የቁጥጣ ፍርድ በታች ሆነው እንደ ተረገመ በመቆጠር ቅጣታዊ ሞት የሚቀበሉበት ነው (ዘዳ. 21፥33)። ስለዚህም የኢየሱስ የመስቀል ላይ ሞት በእግዚአብሔር የመቀጣት ተግባር ነው። ይህን እውነት ጳውሎስ፥ “በዕንጨት ላይ የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል፤” በማለት ይገልጻል (ገላ. 3፥13)። በመሆኑም የክርስቶስ ከሞት መነሣት ማለት ርሱ የሞትን ኀይል ማሸነፉን ማሳያ ብቻ ሳይሆን፣ ከእኛ ላይ የሞት ርግማን መስበሩንም ጭምር መግለጫ ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ በርግማን ቅጣት ፍርሀት ሆነን በኀሊና ክስና ፀፀት ውስጥ ከመኖር ይልቅ በርሱ ያገኘነውን ድነትና የዘላለም ሕይወት እያሰብን እንድንኖር ያስችለናል። ብራውተን ኖክስ የተሰኘ ጸሐፊ ይህን እውነት፥
በእግዚአብሔር ተረግሞ ሞተ፣ በእግዚአብሔር ከሙታን ተነሣ፤ ለወንጌል ስብከት ማእከላዊ የሆነው ይህ አያዎአዊ እውነት ነው። ምክንያቱ ደግሞ፣ ‘እንድንድንበት ዘንድ የተሰጠ ሌላ ስም ከሰማይ በታች ስለሌለ ነው።’ በእግዚአብሔር ተረግሞ የተሰቀለው ኢየሱስ ከመቃብር ውስጥ ሞትን ድል አድርጐ በመነሣት በእግዚአብሔር ቀኝ በዙፋኑ የተቀመጠው ኢየሱስ የስብከት ማእከላዊ ጭብጥ ወደ መሆን መጥቷል። እግዚአብሔር ረግሞት ለመስቀል ሞት ዳረገው፤ እግዚአብሔር ከሙታን አስነሥቶ በማጽደቅ የክብር ዘውድ ጭኖ በቀኙ አስቀመጠው
በማለት ይገልጻል።[5]
ስለዚህም ክርስቶስ ተሰቀለ፣ ተቀበረ፣ በእግዚአብሔር ኀይል ከሙታን ተነሣ፣ እንዲሁም እግዚአብሔር እንደ ተረገመ ሆኖ የተሰቀለውን ክርስቶስን የሞትን ኀይል ሰብሮ አስበሣው የሚለው ሐሳብ የወንጌል ስብከት ማእከላዊ ጭብጥ ሊሆን ችሏል (ሐዋ. 5፥30፤ 10፥39-40፤ 13፥29-30)።
የኢየሱስ ሥቃይና ሞት ዘላለማዊ ውጤት
የክርስቶስን መስቀል ምስጢር በትክክል መረዳት የሚቻለው ከመስቀሉ በፊትና በኋላ ስለ ተደረጒ ነገሮች በሚገባ በማወቅ ነው። በትንሣኤው ምክንያት፣ 1) የክርስቶስ ሞት ድንገቴ ክሥተት ሳይሆን፣ መለኮት ሥጋ የሆነው ለዚሁ ዓላማ መሆኑን አመልካች ነው፤ 2) ከርሱ ሞት የተነሣ የተገኙ ውጤቶች ምን እንደሆኑ ታይተዋል። የክርስቶስ ሞት እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅርና ርሱም በእኛ ምትክ ለመሞት ያለውን ፈቃድ የሚያሳይ ነው። ክርስቶስን ያዳነን በሞቱ ብቻ ሳይሆን፣ በመስቀል ላይ በሞተው ሞት ስለ እኛ በከፈለው መሥዋዕታዊ ሥራው ነው። በመሆኑም የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሥቃይና ሞቱ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ የሚገለጥበት መንገድ ነው። ክርስቶስን ከሞት በማስነሣት እግዚአብሔር ለድነት ሥራው ማረጋገጫ ዋስትና ሰጥቷል። በእኛ ምትክ የተከሰሰውና የተቀጣው ኢየሱስ በአባቱ የተባረከ ልጁ ነበር። በመስቀል በተሰቀለበት ወቅት በአባቱ የተረሳውና የተተወዉ ኢየሱስ በሥራዎቹ እግዚአብሔ አብ የተደሰተበትም ነበር። በምድር ላይ የተገፋውና የተጠላው ኢየሱስ በሰማይ በአባቱ ቀኝ በታላቅ ግርማ የክብር ዘውድ ጭኖ የተቀመጠው ክርስቶስ ነው።
የክርስቶስ የውርደት ሞት እኛን ከኀጢአትና ከሞት ለመዋጀት የተደረገ መሥዋዕትነት ሲሆን፣ ትንሣኤው ዕዳችን የመከፈሉና የመዋጀታችን ማረጋገጫ ነው (ፊልጵ. 2፥9፤ 1ቆሮ. 15፥15)። ብራይን የተሰኘ ጸሐፊ ይህን እውነት፣
እንዲሁም ብራይ የተባለ ጸሃፊ እንዳለው፡-
በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ከሙታን ተነሥቶ ለደቀ መዛሙርቱ የታየው ሞቶ የተቀበረው ኢየሱስ እንጂ መልአክ አይደለም። የክርስቶስ ከሙታን መነሣት ከኀጢአት ሙሉ ለሙሉ መውጣታችንና የኀጢአታችን መከፈሉን የሚያበስር መልካም የምስራች ነው። የክርስቶስ ከሙታን በአጃል መነሣት እኛ ከኀጢአት ባርነት ነጻ ወጥተን ለዘላለም የመዋጀታችን እውነት ማረጋገጫ ማኅተም ነው
በማለት ይገልጣል (ገጽ 595)።
ከሞት የተነሳው አዳኝ
የክርስቶስን የመስቀል ላይ ሞትና ውርደቱን በትክክል መረዳት የምንችለው፣ ርሱ ከሞት ተነሥቶ በአብ ቀኝ መክበሩን በተረዳንበት መጠን ነው (ፊልጵ. 2፥9)። ክርስቶስ ከሙታን ያልተነሣ ከሆነ መሞቱ ምንም ፋይዳ ያለው ነገር አይሆንም። በመሆኑም የክርስቶስ ትንሣኤ የርሱ ሞት ብቻ ሳይሆን የሞቱ ፋይዳ ምን እንደሆነም አሳይቶናል። ትንሣኤው ከገለጣቸው ፋይዳዎች አንዱና ዋናው የክርስቶስ ሞት እኛን ከኀጢአት ዕዳ ነጻ ለማውጣት የተከፈለ መሥዋዕትነት መሆኑን ነው። ጳውሎስ ይህን እውነት፣ ‘“በዕንጨት ላይ የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል፤” በማለት ይገልጣል (ገላ. 3፥13)።
በተጨማሪም የዕብራውያን ጸሐፊ፣ “በዘላለም ኪዳን ደም የበጎች ታላቅ እረኛ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የሰላም አምላክ፣ …” በማለት የክርስቶስ ሞት ውጤት ሰላም ስለመሆኑ ይገልጻል (ዕብ. 13፥20)። ስለዚህም የክርስቶስ ትንሣኤ የመስቀሉ ውጤት ነው። እግዚአብሔር አብ ልጁ የመስቀል ሞት እንዲሞት በማድረግ ታላቅ የማዳን ሥራ ፈጸመ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ሳይይዘው ሕያው ሆኖ ከመነሣቱ የተነሣ ዘላለማዊ አምላክ ሆኖ ይኖራል። በዚህም ምክንያት ርሱ ዘላለማዊ የክህነት አገልግሎት የመፈጸም መስፈርት የሚያሟላ ሆኗል። ርሱ በሞቱና በትንሣኤው ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ዙፋን የማቅረና ለሕዝቡ የመማለድ አገልግሎት ስለተቀበለ (ዕብ. 7፥23_25) በርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ማዳን ይችላል።
በኀጢአትና በሞት ላይ የተቀዳጀው ድል መርህ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው በርሱ ላይ የታወጀውን ሞት ብቻ ሳይሆን የእኛንም ሞት ጭምር አሸንፏል። ክርስቶስ በትንሣኤው ያበሰው ድል ስውር ቢመስልም እንኳን፣ ድሉ በግልጽ የታወጀና በአደባባይ የተበሰረ ነበር። በመሆኑም በክርስቶስ ትንሣኤ ውስጥ በክርስቶስ ማንነትና ሥራ አማካይነት እግዚአብሔር በኀጢአትና ሞት ላይ የተቀዳጀውን ድል እንመለከታለን። ይህም በሰው ልጆች ሕይወት ላይ የተጀመረው የዐዲስ ሕይወት ምዕራፍ ነው።
ሞትን መጋፈጥ
ከጥንት እስከዚህ ዘመን ድረስ በርካቶች ስለ ሞት ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ስለሞት ለማወቅ ዝግጁ አይመስልም። በተለይም ደግሞ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የመድኃኒት አቅርቦት ሞት ከበርካቶች ዕይታ እንዲሰወርባቸው ያደረገ ይመስላል። ሞት ቀላልና ለንግግር ምቾት የሚሰጥ ርእሰ ጒዳይ አይደለም። በልዩ ልዩ ምክንያቶች በርካቶች ስለሞት ለመወያየት ዝግጁ አይደሉም። ከዚህም የተነሣ ስለሞት ተገቢ ግንዛቤ የላቸውም።
አብዛኞቻችን እንደምንረዳው ሞት ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝ ውጤትና የኀጢአት ዋጋ ነው (ሮሜ 6፥23)። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቷል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤” ይላል (ሮሜ 5፥12)።
በክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ከተረጋጋጡ እውነቶች አንዱና ዋናው ርሱን ሞት ሊይዘውም ሆነ ሰይጣን ሊገዛው ያለመቻሉ ሲሆን፣ ከሲኦልና ከመቃብር በላይ አሸናፊ ሆኖ ተነሥቷል። የዕብራውያን ጸሐፊ ዕብራውያን 2፥14 ላይ፣ “ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቷል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤” ይላል (ባቪንክ፣ 368)።
የክርስቶስ ትንሣኤ የምያረጋግጥል እውነት ክክርስቶስ ሞቶ የተነሣው ሞትን ለማሸነፍና ለማስወገድ መሆኑን ነው። ትንሣኤው እግዚአብሔር በኀጢአት፣ በክፋት፣ በሞትና በዲያቢሎስ ላይ የተቀዳጀው የመጨረሻው ድል ነው። በአጠቃላይ በግልጽ በአደባባይ የታወጀው የእግዚአብሔር ድል የመጣው በክርስቶስ የመስቀል ሞትና ትንሣኤ አማካይነት ነው ማለት ይቻላል።
የክርስቶስ ሞት የሞትና ትንሣኤ የሞት ኀይል ትጥቁን እንዲፈታ አድርጓል። ከሞት በኋላ የመጣው የዘላለም ሕይወት በመሆኑ ዲያቢሎስ በከፍተኛ ተስፋ መቊረጥና በመደናበር ውስጥ ሊገባ ችሏል። ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተነሣ የሞት ኀይል በክርስቶስ ተዋጠ፤ መዋጥ ብቻ ሳይሆን፣ ትንሣኤው የዘላለምን ሕይወት በማምጣቱ ምክንያት የሞት ኀይል ምንም ዐይነት ሥራ የመሥራት ዐቅም እንዳይኖረው ሆነ።
በርግጥ በክርስቶስ ትንሣኤ የተሸነፈ ቢሆንም፣ የሞት ኀይል ለጊዜውም ቢሆን በመካከላችን በመኖር ይቀጥላል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ፥ ሞት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰሱን ያወሳል (1ቆሮ. 15፥26)። ይህም የሚሆነው በመጨረሻው ዘመን አማኞች በሙሉ አካለ ትንሣኤ ሲያገኙ ነው። አማኞች በአሁኑ ዘመን መንፈሳዊ ትንሣኤ አግኝተው ከክርስቶስ ጋራ የተነሡ ሲሆን (ኤፌ. 2፥6፤ ቈላ. 3፥1)፣ በመጨረሻው ዘመን ደግሞ በአካላ ትንሣኤ ይነሣሉ። ሁላችንም በክርስቶስ ሕይወት አግኝተናል። በመሆኑም በዲያቢሎስ ላይ ዐምፀን ለእግዚአብሔር ክቡር አገልግሎት ለማገልገልና አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተን በጌታ ያገኘውን ዐዲሱን ሕይወት በመኖር ልንቀጥል ይገባናል (ኤፌ. 2፥10)። የክርስቶስ አካላዊ ትንሣኤ ርሱ ዳግመኛ በሚመለስበት ጊዜ እኛ ለምናገኘው አካላዊ ትንሣኤ ዋስትና ይሆነናል (1ቆሮ. 15፥20፡23)።
ብራክል የተሰኘ ጸሐፊ፣ እግዚአብሔር ውድ ልጆቹን ወደ ሰማያዊ ቤታቸው የሚመራበት መንገድ በብዙ መስቀሎች አማካይነት ነው። እያንዳንዱ አማኝ ጊዜያዊውን የሥጋ ሞት የሚሞተው በየራሱ መስቀል ነው። በአስቸጋሪ መከራዎች የተመላ ቢሆንም፣ ይህ መንገድ በኀጢአት ምክንያት ከመጣብን ቅጣት በመዳን በክርስቶስ የተገኘውን የድል መንገድ የምንጓዝበት ብቸኛው መንገድ ነው ይላል።
ሰብእነትን እንደገና ማወጅና ፍጥረትን ማደስ
ክርስቶስ መቃብር ፈንቅሎ ከሙታን በመነሣት የኀጢአትን ኀይል በመስበሩ ምክንያት ኀጢአት ኀይሉን አጥቷል። የሰውንም ልጆች ከሐጢኣተኛ ባሕር,ይ ወይም ከተበላሸ ማንነት ነጻ በማውጣትና ከሰይጣን እስራት ከሚያስከትለው የዘላለም ሞት በመታደግ ወደ ከፍታ አምጥቶታል። ከዚያም አልፎ በክርስቶስ የተገኘውን ዐዲስ ማንነት መፈጠር ምልክት ብቅ ማለቱን ምልክት አሳይቶናል። የዚህ የዲስ ማንነት ፈጣሪና ወኪሉም የእግዚአብሔር የዘላለም ልጁ የሆነ ኢየሱስ እንደሆነ የዕብራውን ጸሐፊ በግልጽ ይነግረናል (ዕብ. 2፥5-9)። ይህም እግዚአብሔርር ክርስቶስን ከሙታን በማስነሣቱ የሰውን ልጅ እንደ ፈጠረ ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደገና እንደፈጠረና ዐዲስ ሕይወት በመስጠት ልዩ ዓለም እንደ ፈጠረለት ማየት ይቻላል። ስለዚህ የክርስቶስ ትንሳሣኤ የሰውን ልጆች ሁሉ የዘላለም ኑሮውንና የሕይወትን አቅጣጫ ሁሉ በመቀየር ወደ ዘላለም ሕይወት እንደ መራው እንመለከታለን። ይህም የሚያሳየን በቀላሉ የሰውን ልጆች ማንነት ከተበላሸበት ስፍራ ወደ ተሐድሶ የማምጣትን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሕይወት አቅጣጫው በሙሉ ተቀይሮ ወደ ዘላለም ከፍታ መውጣቱንና መክበሩን ነው።
አንዳንድ የነገረ መለኮት አጥኚዎች የክርስቶስን ትንሣኤ በቀን ጊዜ ወይም በቀትር የተከናወነ ድርጊት አድርገው ለመተረክ ይሞክራሉ። ለዚህም ማስረጃ እንዲሆን በማቴዎስ ወንጌል 28፥1 ላይ የተጻፈውን ገና ሲነጋ ተነስቶ በቀትር አካባቢ የሆነ ክሥተን እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ይህም ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ የንጋት ኮከብ (ራእ. 22፤16)፣ የጽድቅ ጸሐይ (ሚልክ. 4፥2)፣ ከላይየተገለጠ (ሉቃ. 1፥78)፣ ለአሕዛብም ብርሃን ወይም ብርሃንን ያመጣ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ሕያው ሆኖ የተነሣው በቀን ጊዜ እንደሆነ ይሞግታሉ። እንዲሁም ዐዲስ ኪዳን የክርስቶስን ትንሣኤ ሲተርክ፣ ይህ ከሙታን የተነሣው ክርስቶስ የትንሣኤ በኩር እንደሆነ ሲገልጽ (1ቆሮ. 15፥20) ክርስቶስ ከሞት ላዳናቸውና ዳግመኛና ለተወለዱት ብቻ ሳይሆን፣ ዓለምም ጭምር በእርሱ ትንሣኤ አማካኝነት ዳግመኛ ልደት እንደሚታገኝም ይገልጻል። ይህም ሲባል በክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያት የፍጥረታት ሁሉ ትንሣኤ ሊሆን የሚችልበትን እድል ለማሳየትና እግዚአብሔርም ክርስቶስን ከሙታን ሲስነሣው ዓለም እንደገና እንድትወለድና ፍጥረትም ሁሉ እንድታደስ ያወጣውን የመጀመሪያ እቅዱን የሚያስረዳን መልእክት አለው ማለት ነው።
በክርስቶስ ሞት ምክንያት ኀጢትና ክፋት ሁሉ ተፈርዶባቸዋል። በትንሣኤው ደግሞ የኀጢኣት ውጤቶች በሙሉ ፈጽመው ተወግደዋል። ይህም የሚያሳየን በኀጢኣት፣ በሞትና በክፉ ኀይላት ሁሉ ላይ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ድል ብቻ ሳይሆን፣ እኛንም ሞት እንዳያገኘን እግዚአብሔር ያረጋገጠልንን የዘላለምን ዋስትናችን ጭምር ነው (1ቆሮ. 15፥53-57፤ ሮሜ 8፥34-39፤ 2ጢሞ. 1፤10)። በተመሳሳይ መልኩም የክርስቶስ ትንሣኤ አሮጌውን ሁሉ አሳልፎ ዐዲስን ፍጥረት ያስጀመረ ሲሆን፣ ርሱ ሁሉን ዐዲስ ያደርጋል (ራእ. 21፥4-5)።
ከመለኮት ጋራ ዘላለማዊ ውሕደት በመፍጠር ሂዳት ፍጹምነትን ያገኘው የክርስቶስ ሰውነት
የክርስቶስን ነፍስ ከዐዲሱ መንፈሳዊ አካሉ ጋር እንደገና በማጣመር ወይም አንድ በማድረግ ትንሣኤው የቃሉን እውነተኛነት አረጋግጦ አሳይቶናል። ጌራልድ ብሬይ የተሰኘ ምሁር፣ “ኢየሱስ ሥነ ነስቶ በምድር ላይ በመገለጡ ምክንያት መለኮታዊ ማንነቱን ወይም የእግዚአብሔር ልጅነቱን ሳይለቅ ሁለተኛ ማንነት የሆነውን ሰው-ነትን ሊይዝ ችሏል” ይላል።[6] ክርስቶስ ገና ከመጀመሪያው በኀጢኣት የወደቀውን አሮጌ የሰብኣዊ ባሕርይ ጉዳይ በመረዳቱ ቀጥሎ ሊመጣ ያለውን ዐዲስ የትንሣኤ ሕይወት እና ፍጹም የሆነ የራሱን መልክ ገና ከሩቅ ተመልክቶ ነበር ማለት ይቻላል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ትንሣኤ ሥጋ ነስቶ የመገለጡን ምስጢር ግልጽ የሚያደርግና በዚህም ተግባሩ ምክንያት የሰውን ልጆች ሁሉ ባልተጠበቀና ባልተለመደ መልኩ ከፍ አድርጎ እንደሚያከብር ማረጋገጫ ነው። የክርስቶስ መወለድና መሞቱ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው። ምክንያቱም እርሱ በእውነት ተወልዶ በሁሉ ዘንድ በተለመደ መንገድ ሞቷልና።
የሰውን ሥጋ ነስቶ በሰው መልክ የተገለጠው የኢየሱስ ትንሣኤ በእግዚአብሔር እና በሰው ልጆች መካከል ያለውን የግንኙነት ሁኔታ በሚገባ ግልጽ የሚደርግ እውነት ነው። ክርስቶስ በአካል ከሙታን መነሣቱ ሥጋ ነስቶ በምድር ላይ መገለጡን አበክሮ የሚገልጽ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን፣ ሰብኣዊ ምንነቱንም ዘላለማዊ በሆነ መልኩ ለሁሉ የሚያስተዋውቅ መልዕክት ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ ገና ኢየሱስ በእናቱ ማህፀም ውስጥ ተፀንሶ በነበረበት ወቅት ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠ እውነት ነበር። ከዚያች ነጥብ አንስቶ የልጁ የኢየሱስ መለኮታዊ ባሕርዩ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለዘላለም አንድ ሆኖ (ተዋሕዶ) እንደቀረ ማየት ይቻላል።
የክርስቶስ ትንሣኤ ሰብኣዊ ማንነቱን ወደ መለኮታዊነት አልቀየረውም። ነገር ግን የእርሱን እውነተኛና ፍጹም ሰብኣዊ ማንነቱን ከመለኮታዊ ማንነቱ ጋር በማጣመር ወይም በማዋሐድ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዳደረሰው መገንዘብ ይቻላል። ክርስቶስ በሚያስደንቅ ትሕትናው እና ከሁሉ በላይ በክብር ከፍ በማለቱ መለኮት-ሰው ወይም አምላክ-ሰው (God-man) ተብሎ ሊጠራ ችሏል። ትንሣኤው ሰብኣዊ ማንነቱ ወደ ታላቅ የፍጹምነት ደረጃ ላይ ከፍ ሲያደርገው፣ የሰብኣዊና የመለኮታዊ ባሕርዩ መዋሐድ ወይም መጣመር ደግሞ የክርስቶስን ዘላለማዊነት ግልጽ አድርጎ ሊያሳየን ችሏል። “ቃልም ሥጋ ሆነ” የሚለውን እውነት ይህን ሐሳብ ግልጽ ያደርግልናል። ይህ ሥጋ ነስቶ በመካከላችን በማደሩ ምክንት በኀጢኣት የወደቀን የሰው ልጅ የመሰለው የእግዚአብሔር ልጅ አሁን ደግሞ በትንሣኤው አማካይነት በመንፈስ ቅዱስ ሐይል የታደሰና ዳግመኛ የተፈጠረ መልክ ይዞ ሊገለጥ ችሏል። የሰውም ዘር ሁሉ በመጀመሪያ በመልኩ የፈጠርና የአባቱን ፍጹም ማንነት የተላበሰው ልጁ ኢየሱስ አሁን ደግሞ ከሙታን በመነሣቱ ፍጹም የሆነ የራሱንና የአባቱን መልክ ይዞ ሊገለጥ ችሏል። በመሆኑም ነው ዌነንድ ተባለ ጸሐፊ፣ “አሁን ልጁ የፍጹም አምሳሉ ፍጹም አምሳል ነው” ያለው (ገጽ 397)።
የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች፣ ማለትም አዳምና ሔዋን በአንድ ላይ የተፈጠሩበት ኅብረታዊ መልክ በሚገልጥ የእግዚአብሔር አምሳል ነው። ኅብረታዊነትን በሚገልጥ መልኩ በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠር ማለት በሥሉስ አሓዱ አምላክ ማለትም በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለውን የፍቅርና የአንድነት ማኅበር ለሚገልጥ ሕይወት መፈጠር ማለት ነው (ዘፍ. 1፥26-27)። አሁን ደግሞ ኢየሱስ እውነተኛ ማንነቱ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ እንደ ወንድማችን፣ እንደ ሊቀ ካህናች፣ በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል እንደ አማላጃችን ሆኖ ወደ አባቱ የሚጸልይልንና የሚያማልድልን ሆኖ ሊገለጽ ችሏል (ዕብ. 2፥14-18፤ 4፥14-16፤ 7፥25)።
[1] Warfield, Selected Shorter Writings, 1:201.
[2] Hilary of Poitiers, The Trinity, 7.12; NPNF 2.9:122.
[3] Vos, Reformed Dogmatics, 3.5.54; Single-Volume Edition, 592.
[4] Oden, Systematic Theology, 2:456.
[5] Knox, Selected Works, 3:41, 43.
ምዕራፍ 9
የኢየሱስ ትንሣኤ ፋይዳዎች
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ እግዚአብር ለሰው ልጆች የሕይወት ተሐድሶ ያቀደውን ዕቅድ በተግባር እንዳበሰረው መገንዘብ ይቻላል። ስለዚህ የእርሱ ትንሣኤ የኛን የሕይወት ተሐድሶና ያም መታደስ ያመጣውን ለውጥ ወክሎታል ማለት ይቻላል። ምክኒንቱም የሕወታችን ለውጥ ወይም ተሐድሶ ውጤቱም ሙሉ በሙሉ በክርስቶስ ሥራ መጽቅን ዳግመኛ መወለድንና ከርሱ ጋራ ከሙታን መነሣት እንዲሁም በእግዚአብሔnር ጥበብ በመፈጠሩ የተገኘው የፍጥረታት ሁሉ መልካምነትና ፍጹምነት እንደ ዋና ዋና ትሩፋቶች የሚጠቀሱ ናቸው። እንደ ሰው ልጅና በሁሉ ላይ የበላይ የሆነ አምላክ ኢየሱስ፣ አሁንም ለዘላለምም ሕያው ሆኖ ይኖራል። ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ በሙሉ ዐቅሙና ችሎታው የኛ ነው ማለት ነው። ርሱ ሞቶ ከሙታን በመነሣቱ (ራእ. 2፥8) የትንሣኤው ውጤት በክብር ወደ ላይ ማረግ ነበር፤ በዚህም ርሱ ለፈጠረው ፍጥረት ከፍ ብሎ የመክበር ፍጻሜ አምጥቶለታል። በዚህም ምክንያት በርሱ የሚያምኑ ሁሉ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት ዳግመኛ እንዲወለዱ አደረገ (1ጴጥ. 1፥4)።
ዘካሪያስ ኡርሲነስ እና ካስፐስ ኦሌቪነስ የተባሉ ምሁራን ከክርስቶስ ትንሣኤ ስለምናገኘው ፋይዳ ጥያቄ ከሰነዘሩ በኋላ፣ ለጠያቄያቸው ሄድልበርግ የተሰኘ ጸሐፊ፣ “የክርስቶስ ትንሣኤ ፋይዳው በመጀመሪያ ደረጃ እርሱ ሞትን አሸንፎ በመነሳሣቱ እኛንም የጽድቁ ተካፋዮች ማድረጉ ነው በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አሁን እንኳን በእርሱ ኀይል ከሙታን ተነሥተን ወደ ዲስ የሕይወት ምዕራፍ መሸጋገራችን ነው። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የክርስቶስ ትንሣኤ በመጨረሻ ቀን የኛም ትንሣኤ ሊሆን ጽኑ ተስፋ መሰጠቱ ነው” የሚል በማለት ምላሽ ሰጥቷል።
እነዚህን እውነቶች ከዚህ በታች አንድ በአንድ ለመመልከት እንሞክራለን።
መጽደቅ፥ ከእግዚአብሔር ጋራ ትክክል ወደ መሆን ሕይወት መመለስ
ሐዋሪያው ጳውሎስ በሮሜ 10፡9-10 ባለው ክፍልኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ በልባችን ማመንና እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በአፋችን መመስከር ስለ መጽደቃችንና ከእግዚአብሔር ጋራ ወደሚኖረን ኀብረት እንዲመጣ በማድረግና ድነን ከክፉው ኀይል ነጻ እንድንወጣ እንዳደረገን ይገልጻል። ያም የሚያጸድቀን እምነት የሚባለው የግድ ሞትን ድል አድርጎ በተነሣው ጌታ በኢየሱስ ላይ ሊኖረን የሚገባው እምነት ነው። በሌላ አባባል አንድ ሰው እንደጸደቀ የሚቆጠረው ከሙታን በድል በተነሣው በጌታ በኢየሱስ ላይ እምነቱን መጣል ሲችል ብቻ ነው (ሮሜ 4፥24)። ይህም ሊሆን የሚችልበት ምክንያት እውነተኛ ማንነቱን በመግለጡ፣ ትምህርቶቹንም በማጽናት እና ለኀጢኣታችንም የመሞቱን እሴቶች በማጽናቱ ሞትና መቃብርን ሁሉ በመበቀሉ ነው (ዮሐ. 16፥10)። ፍርዳዊ በሆነ መልኩ በትንሣኤ ክፍ ያለው የክርስቶስ ለእኛ ጽድቅ ፍርዳዊ ፋይዳ ያለው ነው[1]
እግዚአብሔር አባቱ ልጁን ክርስቶስን ከሙታን በማስነሣቱ ፍጹም የሆነ ኀይሉንና ሥልጣኑን በገሃዱ ዓለም በግልጽ እንዳሳየና የተስፋውንም ቃል ኪዳን በመፈጸም የክርስቶስን ፍጹም የሆነ ጽድቅ እንዳወጀለተት እንመለከታለን። ይህም የታወጀው ጽድቅ የሚባለው በክርስቶስ በማመናችን ምክንያት የሚደረግልንን ጽድቅ የሚያሳይ ነገር ነው (ሮሜ 4፥25)። ምክንያቱም ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ግ በመታዘዝ የሕጉንም መጠይቅ ሁሉ በፍጹም መታዘዙ በማሟላት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ወደ ትክክለኛ መስመር አምጥቶታልና። በትንሣኤው ይላል ቮስ፣ በክርስቶስ የሚያምን አካል ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ተደርጎ ይቆጠር ዘንድ ፍርድ ታውጇል፤ በመጨረሻም ለዚህ በክርስቶስ አምኖ ጻድቅ በመባል ለታወጀው ሰው የሚጠብቀው መጽደቁን በግሉ እንዲያውቅ ለመደረግ ያለፈ ነገር አይደለም።”[2]
የመጽድቃችን በአደባባይ መታወጅ
ጽድቃችን የተረጋገጠበት ዋናው ምክንያት ክርስቶስ ስለኛ በመሞቱ ነው። በሮሜ 5፥9፣ “በደሙ ከጸደቅን በእርሱ (በክርስቶስ) ከእግዚአብሔር ቁጣ እንድናለንና” ይላል። ይህም በግልጽ የሚያሳየን የክርስቶስና የአማኞችን ጽድቅ የሚያገናኘው የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ እንደሆነ ነው። ይህን እውነት ባቪንክ፣
የክርስቶስ ሞት የመሥዋዕትነት ሞት ሲሆን፣ ከኀጢኣታችንም ሙሉ በሙሉ ተዋጅተን ወደ ዘላለም ጽድቅ የገባነው በዚያው ሞቱ አማካይነት ነው። በትንሣኤውም አማካይነት ራሱ ኢየሱስ ብቻ ሳይሆን፣ እኛም ጽድቅን አግኝተናል። የእርሱም ከሙታን መነሣት የመፈታታችንና ነጻ የመውጣታችን ግልጽ የሆነ አዋጅ ነበር። እንዲሁም ደግሞ እርሱ ከሙታን በመነሣቱ እና እኛም በትንሣኤው ኀይል በማመናችን ከእግዚአብሔር ጋር ወደ መታረቅ እንደመጣን እንረዳለን። ስለዚህ የክርስቶስ ትንሣኤ እኛም የመጽደቃችን ማስረጃ ነው ማለት ይቻላል
በማለት ገልጿል (ባቪንክ፣ 370)።
የክርስቶስ ሞት የእግዚአብሔርን ጽድቅ በኛም ላይ ግልጽ አድርጎጐ ገልጦታል ሲባል ልጁ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ቊጣና ፍርድ ሁሉ ተሸክሞ በእኛ ፈንታ መሥዋዕታችን መሆኑን ነው። በቀላሉ ሲታሰብ ክርስቶስ ከሥቃይ፣ ከሞቱና ከመቀበሩ ተስፋ የሌለው ደካማ ሆኖ ሊታ ይችላሉ።ል ትንሣኤው ግን ኀይሉንና ሥልጣኑን ከማረጋገጡም ዐልፎ በክርስቶስ ሞት አማካይነት የተገለጠውን የእግዚአብሔርን የጽድቅ ሥራ ግልጽ አድርጎ ያሳየናል። የክርስቶስ ትንሣኤ የእግዚአብሔርን ግልጽ ማረጋገጫ የሚያሳይ ሲሆን፣ ያም ማረጋገጫው የጽድቃችን ጉዳይ በትክክል ግቡን እንደ መታ የሚያሳይ ነገር ነው። የነገረ መለኮት ምሁሩ ግሩዳ፣ “እግዚአብሄር የክርስቶስን ትንሥኤ ጉዳይ አረጋግጦ ማወጁ የኛንም ትንሣኤ አረጋግጦ ማወጁን የሚያሳይ ሃቅ ነው” ብሎ ነበር (ግሩደም፣ 756)። ስለዚህ ክርስቶስ ተነሥቷ፤ ኀጢኣትንም ተበቅሎታል። እንዲሁም ስለ ኀጢኣታችንም ይቅርታ ማግኘታችንና ፈጽሞ ስለ መጽደቃችን ዋስትና እንዳገኘንና በእግዚአብሔርም ዘንድ ተቀባይነት እንዳለን እርግጠኞች መሆናችንን ክርስቶስ አረጋግጦልናል።
ጽድቅ ታደሰ፣ ሕይወት ከፍ አለ
የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ አንድ ላይ ከእግዚአብሔር ሕግ ጋራ በተቆራኘ ድነት ሊገኝ የሚችልበትን መሠረት ሊጥሉ ችለዋል። የክርስቶስ ትንሣኤ ከኀጢኣታችን ነጻ ለመውጣታችን፣ ከሞት ለመዋጀታችንና ከእግዚአብሔርም ጋራ ለመታረቃችን ትልቁ መሠረት ሆኗል። በመሠቃየቱና በመሞቱ ምክንያት ክርስቶስ የኀጢኣታችንን ዕዳ እንደ ከፈለልንና ቅጣታችንንም እርሱ እንደ ተሸከመው እንረዳለን። ያለ ክርስቶስ ትንሣኤም የእርሱ ጽድቅ ምንም ጥቅም የሌለው ሆኖ ይቀራል። ነገር ግን ርሱ በመነሣቱ ጽድቁ ግልጽ ሆኖ እንደታየና ታላቁም ድል እንደተበሰረ ማየት ይቻላል። በሮሜ 4፥5 እንደምናነበው፣ የክርስቶስ ሞቱና ትንሣኤው በአንድ ላይ ለሚያምኑት ሁሉ የጽድቃቸው መሠረት ሆኗል። እንዲሁም ደግሞ በሮሜ 4፥25 ላይ እኛን ለማጽደቅ ኢየሱስ ከሙታን እንደ ተነሣ ከተረዳን እኛም የጸደቅንበትና ጽድቃችንም የተረጋገጠው በእርሱ ትንሣኤ ነው ማለት ነው። ይህን እውነት በተመለከተ ቶማስ ሽራይነር የተሰኘ የዐዲስ ኪዳን ምሁር፣ የክርስቶስ ትንሣኤ የሚያሳየው እርሱ በኛ ፈንታ ታላቁን ሥራችንን ሠርቶ እንደ ጨረሰልን ነው በማለት ገልጾ ነበር (1998፡244)። በተጨማሪም ካልቪን ይህ ጒዳይ፣
በክርስቶስ ሞት አማካይነት ኀጢኣታችን ተወግዷል፤ በትንሣኤውም አማ
ካይነት ጽድቃችን በእርሱ ተመልሷል። ታዲያ ርሱ ራሱ ለሞት ዐልፎ ከተሰጠ እንዴት እኛን ከሞት ነጻ ሊያወጣን ቻል? ርሱ በሞተበት ወቅት በነበረው ትግል የተሸነፈ ከመሰለስ እንዴት ድልን በማግኘት እኛንም የድሉ ተካፋዮች አደረገን? ስለዚህ እኛም የድነታችን መሠረቱ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ስንገልጽ በሞቱ አማካይነት ኀጢኣታችን እንደተወገደ እና ሞትም ለዘላለም ኀይሉን እንዳጣ፣ በትንሣኤውም አማካይነት ጽድቃችን እንደ ታደሰና ሕይወት ወደ ተገቢው ቦታው እንደተመለሰ እንረዳለን። ርሱ ሞቶ በመነሳቱ ምክንያት የድነታችንንና የመጽደቃችን ውጤት በግልጽ ታይቶአልና
በማለት ግልጽ አድርጐ ያስረዳል።
ዳግም ልደት፣ በመንፈሳዊ ትንሣኤ ለእግዚአብሔር ሕያው መሆን
ቅዱስ አውግስጢኖስ የተሰኘ የቤተ ክርስትያን አባት፣ “የጌታችን አካላዊ ትንሣኤ የውስጣዊ ሕይወታችን ትንሣኤ ምልክት ነው፤ ስለዚህ አንዱ የርሱ ትንሣኤ ለእኛ ሁለት ትንሣኤን አምጥቶልናል ማለት ነው” በማለት አትቶ ነበር (አውግስጢኖስ፣ 1991፡157)።
የመጀመሪያ ትንሣኤ ዳግመኛ ከመወለድ ጋር ተያያዥነት አለው። ይህ ሐሳብ የሰውን ልጆች መንፈስ ነፍስ ትንሣኤን እንዳገኘ የሚገልጽ መልእክት የያዘ ነው። ሃቤርማስ፣ ዮሐንስ 5፥24 ላይ እንደተገለተው ይህ ዐይነቱ ሕይወት የአንድን ግለሰብ ከመንፈሳዊ ሞት ወደ መንፈሳዊ ትንሣኤ መሻገርን የሚያሳይ እውነት ብሏል (744)።
የኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅና በእርሱ ሞትና ትንሣኤ አምነው ከእርሱ ጋር በእምነት የሚጣመሩት አማኞች ትንሣኤ ዳግመኛ ስለመወለዳቸው ወይም ለነፍሳቸው ዘላለማዊ ድነትን ስለማግኘታቸው ጠንካራ መሠረት ይጥልላቸዋል በሌላ አባባል በወንጌሉ ለሚተማመኑት ሁሉ በክርስቶስ ትንሳሣኤ አማካይነት የተገለጠው የዘላለማዊ ሕይወት እውነተኛነት ተረጋግጦ ዋስትና ይሆንላቸዋል ማለት ነው (1ቆር. 15፥1-4፡20፤ ሃቤርማስ፣ 744)። ምክንያቱም በክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት አማኞች ሁሉ ወደ ዐዲስ የሕይወት ምዕራፍ ተሸጋግረዋልና (ሮሜ 6፥4-5፤ ኤፌ. 2፥4-5፤ 1ጴጥ. 3፥21)።
ዳግመኛ መወለድ የሚለው ቃል ከመጀመሪያ መፈጠርና እንደገና ደግሞ እንደቀደመው መወለድ ጋር ተያይዞ የሚነሣ ሲሆን፣ ሐሳቡም በዐዲስ ኪዳን ሁለት ጊዜ ብቻ ተጠቅሶ ይገኛል። በማቴዎስ ወንጌል 19፥28 ላይ ሰፋ ያለ ስሜት የሚሰጥና በተለይም የሰው ልጅ (ኢየሱስ) በታላቅ ክብሩ ተገልጦ በከበረ ዙፋኑ ላይ ለፍርድ በሚቀመጥበት ጊዜ የሚገለጠውን የፍጥረተ ዓለሙን ሁሉ እንደገና መታደሥ የሚያሳይ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ቲቶ 3፥5 ላይ ስንመለከተው ይህ ዳግመኛ መወለድ የሚለው ቃል ጠበብ ባለ መልኩ የግለ ሰቦችን ዳግመኛ መወለድ ወይም በክርስቶስ የመዳንን ስሜት ያሳያል። በሌላ አባባል ይህ እውነት የግለ ሰቦችን መንፈሳዊ መወለድ ወይም ትንሣኤ ያሳያል ማለት ነው ይህም ማለት የሰዎችን አካላዊ ያልሆነ ወይም መንፈሳዊ ማንነትን እንደገና ወደ ሕይወት መመለስን ወይም ሕይወትን ወደ ተሐድሶ ማምጣንት የሚያሳይ ሐሳብ ነው።
ለዘላለም ሕይወት አሁንዳግመኛ መወለድ
ከዮሃሐንስ ወንጌል እንደምንማረው መንፈሳዊ መወለድ፣ የዘላለም ሕይወትና በክርስቶስ ትንሣኤ ውስጥ የተጠቀሱ ጭብጥ ሐሳቦች በአንድ ላይ የተያያዙ እውነቶች ናቸው (ዮሐ. 3፥18፤ 5፥19-30፤ 11፥24-29)። በቃል ኪዳኑ መሠረት በመጨረሻው ቀን ተፈጻሚነትን ያገኘው በመንፈስ የሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋ በሰው ልጆች ሕይወት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ሊኖረው የተገባ የሽግግር ምዕራፍ ነው። እግዚአብሔር አባቱና ልጁ ኢየሱስ በሥጋም ሆነ በመንፈስ የሞቱትን ሁሉ ወደ ዘላለም ሕይወት በማምጣት ኀይልና ሥልጣን ተጐናጽፈዋል። የኢየሱስንም ድምፅ ሰምተው ለሚያምኑበት ሁሉ ትንሣኤና ሕይወት ኢየሱስ ራሱ እንደሆነ በግልጽ ተቀምጦልናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን እውነት፣ “የሚያምንብኝ ሁሉ ቢሞትም እንኳን ሕያው ሆኖ ይኖራል እንጂ ለዘላለም አይሞትም” በማለት ይገልጻል (ዮሐ. 11፥25_26)። በሌላ አነጋገር በክርስቶስ ማመን ማለት ዳግመኛ ከመወለድ ጋር ተያይዞ ከመንፈሳዊ ሞት ወደ ዘላለማዊ ሕይወት መሻገርን የሚያሳይ ሐሳብ ሲሆን፣ በመንፈሳዊም ቃላት ስናስበው በምንም ዐይነት መንገድ ከመሞት የራቀ የሚል እውነት ያዘለ ነው። በክርስቶስ ማመን የሚለው ቃል ዳግመኛ መወለድ ከሚለው ቃል ጋር ሲያያዝ ከመንፈሳዊ ሞት ወዲያው ወደ ዘላለማዊ ሕ,ይወት መሸጋገርን የሚያመለክት ሲሆን፣ ሞትን ለዘላለም ላለማየት ከሞት ማምለጥንና ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን የሚያሳይ ሐሳብ ነው (ዮሐ. 3፥36፤ 5፥24፤ 8፥51)።
ኢየሱስ ራሱ የኀጢኣታችንን እዳ ክፍሎ ራሱንም ቤዛ አድርጎ በማቅረብ ለእኛም የዘላለምን ትንሣኤ በመስጠት የሕይወትን መንገድ ከፍቶልናልና። የሰው ልጆች በሥጋ መሞታቸው የማይቀር እውነት ነው። ይሁን እንጂ ሞት በአማኞች ላይ የመጨረሻ ሥልጣን የለውም፤ ምክንያቱም በክርስቶስ ለሞቱት ሁሉም በክርስቶስ የትንሣኤ ተስፋ አላቸውና (ፕተር ቦተንፍ 2008፡98)። መጽሐፍ ቅዱስ አሁን በክርስቶስ የተዘጋጀልንና የተረጋገጠልን መንፈሳዊ ትንሣኤ በመጨሻው ቀን ደግሞ በአካል የምንነሣበት አካላዊ ትንሣኤ ሆኖ እንድምጠብቀን ያውሳል (ዮሐ 11፥24)። ኢየሱስ ራሱ ትንሣኤና ሕይወት እንደመሆኑ መጠን (ዮሐ. 11፥25) ከአባቱ ከእግዚአብሔር ጋራ በአንድ ላይ ሙታንን በማስነት የዘላለምን ሕይወት ይሰጣል (ዮሐ. 5፥25)። በተመሳሳይ መልኩም ጴጥሮስ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት አማካይነት ሳይሆን፣ በርሱ ትንሣኤ አማካይነት ለዘላለም ተስፋ ዳግመኛ የተወለድን እንደሆንን አረጋግጦ ይናገራል (1ጴጥ. 1፥3)።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት፣ የክርስቶስ ትንሣኤ የእኛም ደግመኛ የመወለዳችንና በክርስቶስ ዐዲስና ዘላለማዊ ሕይወት የማግኘታችን ምክንያት እንደሆነ ያመለክታሉ በሌላ አባባል የዘላለም ሕይወታችንና የመንፈሳዊ ትንሣኤያችን ዋናው ምክንያት የክርስቶስ ትንሣኤ ነው ማለት ነው። በታሪክ ሁሉ እምብርት ውስጥ ክርስቶስ ዐዲስ ሕይወት ሆኖ ከሙታን ተነሣ ማለት እኛም እንደገና በመወለድ ለእግዚእብሔር ሕያዋን ሆንን ማለት ነው (ሮሜ 6፥11)። ለመንፈሳዊ ትንሣኤያችን እጅግ አስፈላጊ የነበረው ይል በክርስቶስ ትንሳሣኤ ውስጥ የነበረውና በዚያ ሥልጣኑ የተገለጠው የክርስቶስ ትንሣኤ ኀይል ነበር። ካልቪን የድነታችን መጀመሪያ ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገራችን ነው። ምክንያቱም በክርስቶስ በማመናችን ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረናልና ይለናል (Institutes, 3.14.6፣ 774)። በዐዲሱ መንፈሳዊ ሕይወት መወለድ ማለት በበደላችንና በኀጢኣታችን ምክንያት ሙታን ከነበርንበት ኑሮ (ኤፌ. 2፥1) ከእግዚአብሔር ጋራ በሚኖረን ግንኙነት ዳግመኛ ይወት አግኝተን እንደገና መቆምና ሕይወት ተዘርቶልን የመነሣታችን ምልክት ሲሆን፣ ከክርስቶስ ጋራ ሕያው ሆኖ ወደ ሕይወት ተሐድሶ መምጣት ማለት ነው (ኤፌ. 2፥5፤ ቈላ. 2፥13፤ ሮሜ 6፥4)።
ይህን እውነት ዌናንዲ የተሰኘ ጸሐፊ፣
ሞትን ድል አድርጎ የተነሣውና ሥጋ ነሥቶ በምድር ላይ የተገለጠው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ የሆነውን ዐዲስ ሕይወት ለመላክ የሚያስችል ኀይልና ሥልጣን የተጐናጸፈ ሲሆን፣ በመሥዋዕታዊ ሞቱም አማካይነት መለኮታዊ ሕይወትን የሚያፈስ እንደሆነ እንገነዘባለን። በርሱም መንፈስ አማካይነት የሰው ዘር በሙሉ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን በልጁም መልክና አምሳል ዳግመኛ እንደተፈጠረ እንመለከታለን። ስለዚህ ኢየሱስ ከሙታን እንደተነሣ እንደ እግዚአብሔር ልጅ ዐዲሱ አዳም እንደ ተባለና የዐዲሱ የሰው ዘር ሁሉ አባት እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል (ሮሜ 5፥14፤ 1ቆሮ. 15፥45)
በማለት ይገልጻል (ዌናንዲ፣ 397)።
ከክርስቶስ ጋራ የመነሣት ሁለት ደረጃዎች
የክርስቶስ ትንሣኤ በርሱ የሚያምኑትን የሰውን ልጆች ሁሉ ወደ ተሐድሶ እንዳመጣው በማወጅ የአማኞቹንም ጽድቅ፣ ዳግመኛ መወለድና የዘላለም ትንሣኤ ያበስራል። ክርስቶስ ቢሞትም ዳግመኛ ወደ ሕይወት መጣ ማለት እኛም በርሱ በማመን ዳግመኛ ተወልደን ወደ ዐዲሱ ሕይወት እንመጣለን ማለት ነው። በርግጥ የሰው ልጆች ሁሉ በተለይም በኢየሱስ የሚያምኑት እርሱ በመሞቱና በመነሣቱ ምክንያት የተገኘውን ትርፍ እንዳጣጣሙት ማየት ይቻላል። ይህም በሁሉ ደረጃዎች የተፈጸመ ሲሆን፣ 1) አሁኑኑ በርሱ አምኖ ደግመኛ በመወለድ ዳግመኛ ላለመሞት የተገኘውን መንፈሳዊ ትንሣኤን የሚያሳይ ነው (ቲቶ 3፥5፤ ዮሐ 11፥26)። ይህም ማለት በክርስቶስ ያመኑት ሁሉ ሞትን ለዘላለም ላለማየት የሚነሱበት ዐይነት ልዩ ትንሣኤ ነው፤ 2) በመጨረሻው ቀን ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት፣ በአባቱ ቀኝ ከፍ ብሎ ያለው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ በታላቅ ክብር ሲገለጥና ለፍጥረታትም ሁሉ ዳግመኛ መወለድ ሲሆን፣ እንዲሁም ርሱ ሁሉን በሚገዛበት ቀን በእርሱ የሚያምኑትም ድነታቸው ፍጹም በሚሆንበት ጊዜ የሚሆነው ትንሣኤ ነው። ይህን እውነት ቅዱስ አውግስጢኖስ፣ “አሁን በነፍሳችን የሙታን ትንሣኤ እናምናለን፤ እንዲሁም ደግሞ በመጨረሻ ው ቀን በአካል ከሙታን እንነሣለን” በማለት ገልጾ ነበር (348)።
የሙታን ትንሣኤ፣ የአጽናፈ ዓለሙ ታሪክ ውጤት
የክርስቶስ አካላዊ ትንሥኤ የተከሠተው ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በኢየሩሳሌ ከተማ ነበር። ይህ ክሥተት በጣም አስፈላጊና ሁሉን ነገር ባጠቃለለ መልኩ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ነው። ምክንያቱ ደግሞ ይህ ትንሣኤው የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ዓላማና የዓለምን ሁሉ ታሪክ በወሳኝነት የያዘ ነገር ስለሆነ ነው። በመጨረሻም ቀን የነገር ሁሉ ፍጻሜ በሚሆንበት ቀን የራሳችንን ምንነት በሚገባ እናውቀዋለን። ነገር ግን የኢየሱስ ትንሣኤ የሁሉንም ነገር (ያለፈውን፣ አሁን ያለውንና የሚመጣውን ሁሉ) ብቻ ሳይሆን፣ የመጨረሻውንም ነጥብ ጭምር በግልጽ ያሳየናል። ይህንንም የሚያደርገው በሁለት መንገዶች ነው፤ በአንድ ጎኑ ሲታይ በሥጋ በሚታይ መልኩ ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ አሁን የሰው ልጆች ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የሚኖራቸውን ዘላለማዊውን ሕይወት ጉዳይ የሚያሳይ ሐሳብ ነው ምክንያቱም የክርስቶስ ትንሣኤ የአማኞች ትንሣኤ ምሳሌ ስለሆነ መጨረሻቸውም የክርስቶስን የትንሣኤ ይወት መካፈል ይሆናልና። በሌላ ጎኑ ደግሞ የኢየሱስ ትንሣኤ ለእኛም የትንሣኤያችን ምክንያት በመሆን በመጨረሻው ቀን የሰብኣዊውን ፍጥረት ሁሉ የዘላለም ሕይወት ፍጻሜ በቀጥታ የሚያፋጥን እንደሆነ ያሳየናል (ዮሐ. 6፥39፡40፡ 44፤ 11፥23-24)። የህም ማለት የክርስቶስ ትንሣኤ ለእኛ አካላዊ ትንሣኤያችን እንደ ግልጽ መሣሪያ የሚያገለግል ነገር እንደሆነ ነው። በሌላ አባባል የኛ ትንሣኤ የክርስቶስ ትንሣኤ ውጤት ነው ማለት ነው። ምክንቱም የትንሣኤያችንን መሠረት የጣለው ኢየሱስ በትንሣኤው በመሆኑ ነው። በዚህ መንገድ የኢየሱስ ትንሣኤ የአጠቃላዩን የሰውን ዘር ሁሉ ታሪክ የያዘ ነው። ታሪክም ወደ ነገር ሁሉ ማጠቃለያ በፍጥነት በመገስገስ ላይ ያለ ነገር ሲሆን አሁን ግን ለገሃዱ ዓለም ሂደቱ ብዙም ግልጽ አይደለም። ይሁን እንጂ በኢየሱስ ዘንድ ነገር ሁሉ ግልጽና የተራቆተ ነው። ስለዚህ በመጨረሻው ቀን ርሱ ሁሉን ነገር ወደ ተሐድሶ በማምጣት የኛንም የተዋረደ ሥጋችንን ለውጦ እንደ ራሱ ክቡር ሥጋ ያደርገዋል (ፊጵ. 3፥21)።
ከታላቅ ዐቅም ጋራ መፈጠር
በመጀመሪያ ልክ ሰማይና ምድር እንደተፈጠሩ ሁሉ የሰውም ልጆች መፈጠር በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ በጣም መልካም እንደሆነ ታውጆ ነበር (ዘፍ. 1፥4፡10፡12፡18፡21፡25፡31)። የሰው ልጆች ከሚታይ ቁሳዊና ከማይታይ መንፈሳዊ ነገር በአንድ ላይ መፈጠሩ የመልካምነቱ ሁሉ ምንጭ ታላቁ ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር እንደሆነ የሚያሳይ እውነት አለው። የሰውን ዘር ጨምሮ ፍጥረታት ሁሉም እጅግ በጣም መልካም እንደሆኑ እንረዳለን፤ ምክንያቱም ደግሞ የመልካምነታቸው ምንጭና ወሰንና ገደብ የሌለው የፈጣሪያቸው መልካምነት መልካም መሆኑ ነው። ሰዎችንና ከሰው ውጪ ያሉ ፍጡራንን ጨምሮ፣ የመጀመሪያዎቹ ፍጥረታት ሁሉም ፍጹም የሆነ መልካምነትና ውበት የነበራቸው ቢሆንም፣ እነዚህ ፍጥረታት ሁሉ የማደግና ወደ ፊት ግልጽ የሆነ የመሻሻል ዐቅምና እድል ነበራቸው። የሰው ዘር ገና ከአፈጣጠሩ ጀምሮ በአካላዊና በአእምሯዊ ማንነቱ የማደግና የመሻሻል ዐቅም እንደነበረው ስናስተውል፣ መልካምነት በውስጡ እንደነበረ መገንዘብ ከባድ አይሆንም።
የሰው ዘር ሁሉ በዐመጹና በኀጢኣቱ ምክንያት ወደ ክፋት ውስጥ ጠልቆ መዘፈቁ፣ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶችና ሁኔታዎች ወደ ሞት አፋፍ መድሱ፣ የሰው ዘር ከዚህ ክፉ ኀይል በእግዚአብሔር ብቻ ነጻ የሚወጣበትንና ተሐድሶ የሚያገኝበትን መንገድ ፈጥሮለታል። በኀጢኣቱ ምክንያት የወደቀውን የሰውን ዘር እግዚአብሔር ለማዳን ያወጣው የመዋጀት ዕቅድ ተፈጻሚነትን የሚያገኘው ለዘላለም ልጁ በሆነው በኢየሱስ ሥጋ ነሥቶ ወደ ምድር በመምጣት እና ቃል ሥጋ ሆኖ ሙሉ መለኮታዊ አካል በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ነው። ቃል ሥጋ ሲሆን፣ በአካል ሰው መሆንና ቁሳዊና አካላዊ የሰው ሕይወት ክፉ ስላለመሆኑ ሙሉ ማረጋገጫ ልናገኝ ችለናል።
የሙታን ትንሣኤ በታሪክ መጨረሻ ላይ በመላው የሰው ልጅ ማንነት ላይ፣ ማለትም በሥጋና በነፍስ የሚደረግ ተሐድሶና ለውጥ ነው። የትስጒእቱ የእግዚአብሔር ልጅ አካላዊ ሥጋ በትንሣኤ መነሣቱ፣ በመርህ ደረጃ እግዚአብሔር በፍጥረት ወቅት በአዳም ሔዋን ውስጥ ላኖረው አምሳለ መለኮት እግዚአብሔር ዋጋና ክብር የሚሰጥበትንና ያን ዋጋ ከግብ የሚያደርስበትን መንገድ ያነቃቃል። ዘላለማዊ ቃል በትስጒእት ሥጋ መንሣቱና ያን ሥጋ በቋሚነት የማንነት አካል ማድረጉ፣ ይህ የትስጒእት ማንነቱ እንደገና በትንሣኤው ፍጹም ተደርጐ የዘላለማዊው ቃል ክርስቶስ ማንነት የሚሆንበትን የትንሣኤው አካል እንደገና ማግኘቱ፣ አካላዊ የሰው ሥጋና አካላዊ ሕይወት በእግዚአብሔር ዐይን ታላቅ ዋጋ ያለው መሆኑ ደግሞ ደጋግሞ ያረጋግጣል። እግዚአብሔር በክርስቶስ አካል አማካይት በታሪክ ውስጥ ዐዲስ ዐይነት የትንሣኤ ማንነት ወጥኖ ይህንንም ከግብ አድርሶታል። ይህም ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ለእኛም አካል ተመሳሳይ ሐሳብ አለው፤ በመሆኑም በታሪክ መጨረሻ አሁን ያለውን በኀጢአት የተያዘውን ጠፊውን አካል በዐዲስ አካል ለውጦ ያስነሣዋል።
ሞትና መበስበስ የማይቀለበሱ ነገሮች አይደሉም
የክርስቶስ ትንሣኤ በመጨረሻም የሰው ቁሳዊው አካል መልካም የመሆኑን እውነት ያጸናልናል። በተጨማሪም በሞት አማካይነት ሥነ ሕይወታዊ መጥፋትና አካላዊ መበስበስና መጥፋት ተመልሶ የማይመጣ ቢመስልም፣ እነዚህ ነገሮች በእግዚአብሔር እጅ ላይ የማይመለሱ ሳይሆኑ ተቀልብሰው እንደገና የሚመለሱ ናቸው። ትንሣኤ የሚያሳየው አንዱ እውነት ሞት የሰው ሕይወት የመጨረሻ ፍጻሜ ቢመስል በእግዚአብሔር መንግሥት አሠራር ውስጥ ሞት የሰው ልጅ መጨረሻው ሳይሆን የሕይወት መጀመሪያ መሆኑን ነው። የትንሣኤ መሠረታዊው ክሥተት፣ “ቃብሮች ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው የነበሩትም ብዙዎች ቅዱሳን ተነሡ፤ ከመቃብርም በመውጣት ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ገብተው ለብዙዎች ታዩ” በሚለው እውነት ውስጥ ተጠቅሷል (ማቴ. 27፥52-53)።
የክርስቶስ አካላዊ ሕይወት በጊዜያዊነት ሥራውን ያቆመው በትንሣኤ እስኪታደስ ድረስ ብቻ ነበር።[3] ክርስቶስ ዐዲስና የተሻለ የትንሣኤ አካል ወዲያው ማግኘት ችሏል። እንዲሁም እኛም ተመሳሳዩን የትንሣኤ አካል እናገኛለን። የክርስቶስ ትንሣኤ ይፋ ካደረጒ ነገሮች አንዱ፣ ሞት ቋሚና ዘላለማዊ መስሎ ቢታይም፣ ጊዜያዊና ጠፊ መሆኑን ነው። ምክንያቱም ሞት ለክርስቶስ ሕይወት የመጨረሻውን ፍጻሜ ማኖር አልቻለም። ስለዚህም ለእኛም ቢሆን ሞት የመጨረሻው ፍጻሜያችን አይሆንም።
የክርስቶስና የእኛ ትንሣኤ ሁለቱም አንድ እውነታ ነው
በዓለም መጨረሻ የሚሆነው የሙታን ትንሣኤ የእግዚአብሔርን የማዳን ዕቅድ ከግብ ያደርሳል። ትንሣኤያችን … ቤተ ክርስቲያን ስትሰብክ የኖረችው የድነት እውነት ሙላቱን እንዲያገኝ ያደርጋል … የክርስቶስ ገዢነት ሙላቱን የሚያገኘው ሞት ለመጨረሻ ጊዜ ሲወገድ ነው፤ የቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ትንሣኤ ማግኘት ክርስቶስና የእኛ ትንሣኤ በመሠረታዊነት አንድ እውነታ ስለመሆናቸው ማስረገጫ ነው … በ33 ዓ.ም በተከናወነው የክርስቶስ ትንሣኤ እና በዓለም መጨረሻ ላይ በሚከናወነው የእኛ ትንሣኤ መካከል ያለው ቁርኝት እጅግ ተቀራራቢ ነው፤ ስለዚህም ሁለቱም ክሥተቶች የማይነጣጠሉ በመሆናቸው ምክንያት አንደኛው እውነት ካልሆነ ሌላኛው ስሕተት ይሆናል። ትንሣኤ አንድ ክሥተት በመሆኑ ምክንያት በውስጡ ያሉ ክሥተቶች አንዳቸው ከሌላቸው የሚለዩት በዐይነት ቅጽበት በሆነና ለቁጥር በሚያዳግት ጊዜ ነው። የትንሣኤ አካል ባሕርይ ለክርስቶስም ሆነ ለአማኞች አንድና ተመሳሳይ ነው … የክርስቶስ የሆኑ ሁሉ የክርስቶስን ዐይነት በመንፈስ ቅዱስ ተጽእኖ ሥር የሚሆን ኀያል፣ የከበረና የማይበሰብስ የትንሣኤ አካል ይጋራሉ።[4]
ብሉይ ኪዳን የትንሣኤን እውነተኛ ተስፋና በእግዚአብሔር መገኘት ውስጥ ለዘላለም የመኖርን እውነት ይዟል። ይሁን እንጂ በላቀው መልኩ ለሰው ልጆች ስለ ዘላለም ሕይወት ጥልና ታላቅ የተስፋ መሠረት የጣለው የክርስቶስ ትንሣኤ ነው። በዐዲስ ኪዳን ትንሣኤ በሰው ልጆች አካላዊ ማንነት ውስጥ ቀስ በቀስ እየተከናወነ የሚከናወንና የሰውን ነፍስ ወደ ኢመዋቲነት የሚለውጥ ውስጣዊ ኀይል ሆኖ አልቀረበም። በተጨማሪም ትንሣኤ ሰው በመወለድ ያገኘው የሕይወት መርህ ወይም የአንድ ሰው በሂደት የሚቀዳጀው በእግዚአብሔር በመፈጠኑ ምክንያት የተሰጠው ውስጣዊ ብቃት አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ፣ የሙታን ትንሣኤ ሙሉ ለሙሉ በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ መሠረቱን ያደረገ ክሥተት ነው። “በመሠረታዊነት የሙታን ትንሣኤ የክርስቶስ ትንሣኤ ለውጣዊ ኀይል ውጤት ነው፤ ኮኖም ይህ ውጤት የዐዲስና ዐዲሱን ነገር ተከትሎ የሚመጣ ተራ ክሥተት ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም የተደረገውን የክርስቶስን ትንሣኤ አመልካች የሆነ ነገር ነው።”[5] የአማኞች ትንሣኤ ስለ እኛና እኛን ወክሎ ትንሣኤ ባገኘው በክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት የሚደረግ የሰው አካል እንደገና የመፈጠር ሂደት ነው። እውነታውን በግልጽ ለማስቀመጥ ያህል፣ በታሪክ መጨረሻ የሚከናወነው የሙታን ትንሣኤ ስለ እኛና እኛን ወኪሎ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኀጢአታችንን፣ በደላችንና ሞታችንን ተቀብሎ ምትካዊና ቅጣታዊ ሞት በመሞት ወደ ሲኦል የወረደውንና በታሪክ ውስጥ ከሙታን የተነሣውን የክርስቶስን ትንሣኤ ተከትሎ የሚመጣ ክሥተት ነው።[6]
ፈጽሞ ለሞት ያለመሸነፍ
በርካታ ፈላስፎችና ሃይማኖተኞች በዘላለም ሂደት ውስጥ የሰዎች መንፈስ ኢመዋቲና ዘላለማዊ እንደሆኑ ሲያምኑ፣ የሰው አካል ግን አላስፈላጊ፣ ጠፊና አላፊ እንደሆነ ያስባሉ። ከዚህ በተቃራኒ ግን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ከሆነ የአማኞች ሞትን አትንሣኤ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ መንገድ ተከትሎ የሚፈጸም ክሥተት ነው (1ተሰ. 4፥14)። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ “በሞቱ ከእርሱ ጋር እንደዚህ ከተባበርን፣ በትንሣኤው ደግሞ በርግጥ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” (ሮሜ 6፥5) እንዲሁም፣ ‘እግዚአብሔር ጌታን ከሙታን እንዳስነሣው፣ እኛንም ደግሞ በኀይሉ ከሙታን ያስነሣናል” (1ቆሮ. 6፥14) ይላል። የክርስቶስ ትንሣኤ በመሠረታዊነት አካላዊና መንፈሳዊ ነው። ኢመዋቲነትን ለማግኘትና ከነፍሱ ጋራ ውህደት ለመፈጸም የክርስቶስ አካል በበርካታ ለውጥ ውስጥ አልፏል።
ክርስቶስ አካላዊ ትንሣኤና የማይሞት ቊሳዊ ማንነት ያገኘው በእግዚአብሔር ኀይል ነው። ይህ እውነት አማኞች የክርስቶስን የትንሣኤ አካል የሚመስል የማይሞትና የማይበሰብስ፣ የማይጠፋም የትንሣኤ አካል እንዲያገኙ እግዚአብሔር እንዳለው ያረጋግጣል።[7] ኢመዋትነት ማለት ያለመሞት ማለት ነው፤ ለሞት ያለመሸነፍ ነው። ከሞት ኀይል በላይ መሆን ነው። ወደ አካላዊ መበስበስ የሚያመራ ሞትን ያለመሞት ነው።[8] ትንሣኤ ከሰው ማንነት ውስጥ የመበከልና የመበስበስን ድካም መወገድ ማለት ነው። ትንሣኤ ማለት ለአካላዊና መንፈሳዊ አካል የማይቋረጥ፣ በቋሚነት ከሞት በላይ የሆነ ዘላለማዊ ሕይወት መስጠት ማለት። “ኢመዋቲነት በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ሕይወት ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ፣ ማለትም ከክርስቶስ ጋራ የሚኖረን ሕይወት ማጣጣም በመሆኑ ምክንያት፣ በዐዲስ ኪዳን ያለመሞት ማለት በአሁኑ ዓለም ያሉ የሰው ልጆች በሙሉ የሚኖራቸው ነገር ሳይሆን፣ በሚመጣው ዓለም አማኞች የሚያገኙት ነገር ነው። በዚህም ምክንያት ኢመዋቲነትና ትንሣኤ ተመሳሳይ ሐሳቦች ናቸው።”[9]
ከላይ እንዳወሳነው፣ ምንም እንኳን በብሉይ ኪዳን ውስጥ የኢመዋቲነት ሐሳብ የተንጸባረቅ ቢሆንም፣ ስለ ኢመዋቲነት ባሕርይ ያላቸው ዕውቀት አነስተኛ ነበር። ነገር ግን በክርስቶስ ትንሣኤ የሞት ኀይል ከመደምሰሱ የተነሣ፣ “ሕይወትና ኢመዋቲነት ወደ ብርሃን ወጣ” (2ጢሞ. 1፥10)። በመሆኑም ተስፋ የምናደርገው የማያረጀውን፣ የማይሞተውንና ዘላለማዊውን የከበረና መልካም ሕይወት መውረስን ነው (1ቆሮ. 9፥25፤ 1ጴጥ. 1፥3-4፡23)። በተጨማሪም በክርስቶስ ትንሣኤ መሠረት የሆነ ዘላለማዊና የማይጠፋ የትንሣኤ አካል እንለብሳለን። አካላዊ ትንሣኤያችን በባሕርዩ በቀጥታ የክርስቶስ ትንሣኤ ጋራ የተቆራኘ ነው።
አሁን እየተለማመድን ያለው አካላዊ ህላዌና ቊሳዊው ዓለም የተበከለ በመሆኑ ምክንያት አሁን ባለው መልኩ ወደ ዘላለም አይሻገርም። በህላዌው የማይሞትና የማይበሰብስና የማይጠፋ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ኢመዋቲነት እንዲመጣ ቊሳዊው ሁኔታ መለወጥ አለበት፤ ይህ ማለት ሰውነታችን ብቻ ሳይሆን ነፍሳችንና መንፈሳችንም ጭምር፣ እንዲሁም መላው ፍጥረተ ዓለም መለወጥ አለበት። ለጒዳት፣ ለድካምና ለሞት የተጋለጠ የክርስቶስ ሟቹ ሥጋ በትንሣኤ አማካይነት ወደ ኢመዋቲ አካል ተለወጠ። አካላዊ ትንሣኤ ዐዲስ ፍጥረት መሆንን ስለሚያካትት የመጀመሪያው ማንነት ይለወጣል። በተመሳሳይ መልኩም የእኛም አካላዊ ትንሣኤ የክርስቶስን ፈለግ ተከትሎ ተሐድሶና ለወጥ ያገኛል።
የአማኞች ትንሣኤ የሚከናወነው ደረጃ በደረጃ ነው። በዐዲስ ልደት ወቅት አማኞች ወዲያውኑ የማይቋረጥ ዘላለማዊ ሕይወትና ከእግዚአብሔርና ከቅዱሳን ሁሉ ጋራ ኀብረት የማድረግ ኀይል ተቀብለዋል። በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የትንሣኤ ክርስቶስ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ነው፤ “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋራ ነኝ” (ማቴ. 28፥20)። አማኞች ሲሞቱ ወዲያውኑ፣ “ከጌታ ጋራ መኖር ይጀምራሉ” (2ቆሮ. 5፥8)። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የምያስተምረን እውነት አማኞች በመጨረሻ ዘመን ትንሣኤ ወቅት የከበረውን የትንሣኤውን ክርስቶስ አካል የሚመስል ዐዲስና ኢመዋቲ አካል እንደሚለብሱ ነው (ፊልጵ. 3፥21፤ 1ዮሐ. 3፥2)።
የሙሉ አካል ፍጹም ለውጥ
ይህ ብቻ አይደለም፤ ትንሣኤ የሙሉ አካል መለወጥን ያካተተ ነው። በትንሣኤ የሟቹ ሰው ነፍስ ከአካሉ ጋራ እንደገና ተዋሕዶ የመንፈሳና የአካል ውጤት የሆነ ሙሉ ማንነት እንደገና ይፈጠራል።
“ይህም መክበር ተብሎ ይጠራል። ይህ ደረጃ መላውን ማንነት የመቤዥት ሥራ የነፍስና የአካል እንድነትን ፈጥሮ ፍጹም ሙላቱን የሚያገኝበት ነው። በዚህ ሂደት የእግዚአብሔር ሕዝብ ትንሣኤ አግኝቶ የተቤዥ ክቡር ሕዝብ በመሆን ሙሉውን የአምሳለ መለኮት ማንነት እንደገና ያገኛል። የተዋረደው ሥጋቸው ክርስቶስ የከበረበትን የትንሣኤ አካል አግኝቶ ወደ መክበር ይለወጣል።[10]
ይህን ካልን በኋላ፣ የእያንዳንዱ ግለ ሰብ የትንሣኤ አካል ቀድሞ የነበረው ሙሉው ማንነት ወደ መታደስና ወደ መክበር ይለወጣል እንጂ በትንሣኤ አማካይነት ዐዲስ አካል አይፈጠርም የሚለውን የአንዳንድ ሰዎች ዐይነት አስተያየት እስከመሰንዘር መድረስ አላስፈላጊ ነው።[11] በርግጥ ልዩ በሆነ መልኩ የኢየሱስን ትንሣኤ ከተመለከትን የሆነው ከዚህ እውነት ጋራ ተመሳሳይ ነገር ነው። ሞቶ የተቀበረው የክርስቶስ አካል በስብሶ አልተበታተነም ነበር። በርግጥ በክርስቶስና በእኛ ሞት መካከል ልዩነት አለ። ከክርስቶስ አካል በተቃራኒ የእኛ አካል ሞቶ በመበስበስ ይበታተናል። ከዚህም በተጨማሪ በእኛ ሰውነት ውስጥ ያለው ሕዋስ (ከአእምሯችን ሕዋስ በስተቀር) በየጊዜው እየሞተ በሌላ እየተተካ ይሂዳል። ስለዚህም የእኛን አካል ትንሣኤ በተመለከተ፣ በቅንጣት ንጥረ ነገር ደረጃ ካሰብነው፣ አሁን ያለው አካል ምንነት ለማብራራት መጣር አስቸጋሪ ነው።
አሁን ያለውን የእኛን ልዩ አካል ለማብራራት አስቸጋሪ እንደሆነ ሁሉ ከሙታን የተነሣውና ፍጹም የሆነው አካላችን ምን እንደሚመስል አሳማኝ በሆነ መንገድ ለማብራራት መጣር አስቸጋሪ ነው። “ከትንሣኤ በኋላ አንዳችን ሌላችንን የምንለየው በምንድን ነው? በትንሣኤ አካላችን ወጣት ሆነን ነው የምንነሣው ወይስ አርጅተን? የትንሣኤ አካላችንን ሁኔታ በተመለከተ ነገሩ ምስጢር ስለሆና ግልጽ መረዳት ስለሌለን ያለን ብቸኛው ማራጭ ጊዜው እስኪመጣ ጠብቀን ማየት ነው።”[12] በመጨረሻው ዘመን አካላዊ ትንሣኤ እንደምናገኝ እውንና ግልጽ ቢሆንም፣ ዕውቀቱ ግን ከፍልና እግዚአብሔር በገለጠልን ልክ የተወሰነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ወደፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም” ይላል (1ዮሐ. 3፥2)። ይሁን እንጂ ደግሞ ሁለት ነገሮች ግልጽ ናቸው፤ 1) ልክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በመጨረሻው ዘመን የራሳችን የሆነና ልዩ አካል ይዘን እንነሣለ፤ 2) ልክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በመጨረሻው ዘመን ከሙታን የሚነሣውና የከበረው፣ “መንፈሳዊ አካል” እወነተኛ አካል ቢሆንም በይዘቱ አሁን ካለው አካል ልዩ የሆነና የተለወጠ ሲሆን፣ የራሳችን ግላዊ አካል መሆኑ በግልጽ የሚታወቅ ነው።[13] አካለ ትንሣኤ ማለት፣ የሞተው ግለ ሰቡ የራሱን ሙሉ አካል ይዞ ከሙታን ይነሣል ማለት ነው።[14]
በሚመጣው ሕይወት የክርስቶስ ወዳጆች
የክርስቶስ ትንሣኤ ውክልናዊ ትንሣኤ ነው ማለት ይቻላል፤ ትንሣኤ የራሱ አካል ትንሣኤ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችንም ወኪሎና ለሌሎች ጥቅም ጭምር የተደረገም ነው።
የክርስቶስ ትንሣኤ በውስጡ የኅብራታዊ ትንሣኤን እውነት ያዘለ ነው። ከሙታን የተነሣ ዘር የመሲሑ ኢየሱስ ግላዊ አካላ ብቻ ሳይሆን፣ በመሲሑ ቅባት ውስጥ የተካከተተው የሰው ዘር በሙሉ ከርሱ ጋራ የትንሣኤው ተካፋይ ሆኗል። በዘመን መጨርረሻ ሊሆን ያለው ትንሣኤ በሙሉ ርግጠኛ በሆነ መንገድ በክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ተከናውኗል። ዐዲስ የሰው ዘር ከክርስቶስ ጋራ ተነሥቷል።[15]
ኢየሱስ የሞተው ለራሱ ሳይሆን ለሌሎች እንደመሆኑ መጠን፣ ከሙታን የተነሣውም ለራሱ ሳይሆን ለሌሎች ነው። ከሁሉ በላይ፣ ልክ እንደሞቱ ሁሉ የክርስቶስ ትንሣኤ ለሕዝቡ ጥቅምና ከሕዝቡ ጋራ በኅብረት በተቆራኘ መልኩ የሆነ ነው። ርሱ በኀጢአትና በሞት ላይ ድል የተቀዳጀው ሕዝቡን ወኪሎ ነው። “ክርስቶስ ከሙታን የተነሣው በሚመጣው ዓለም ሕይወት ከርሱ ጋራ አብረን እንድንኖር ነው።”[16] ትንሣኤ የከበረ እውነት የሚያደርገው ይህ ነው። በርሱ ትንሣኤ የተጀመረው ነገር፣ “የአካሉ ብልቶች ትንሣኤ ይደመደማል።”[17] የክርስቶስ ትንሣኤ በመጨረሻው ዘመን ሙታን በሙሉ እንደሚነሡ ዋስትና የሚሰጥ ነው (1ቆሮ. 15፥20-23፤ ራእ. 1፥17-18)። “የክርስቶስ ትንሣኤ የእኛን ትንሣኤ ወደርሱ የትንሣኤ ባቡር ስቦ የሚያስገባ ነው።”[18] የክርስቶስ ትንሣኤ ለእኛ ትንሣኤ ቀዳሚና ፈር ቀዳጅ ነው። “ነገር ግን ክርስቶስ በውስጣችሁ ካለ፣ ሰውነታችሁ ከኀጢአት የተነሣ የሞተ ቢሆንም፣ መንፈሳችሁ ከጽድቅ የተነሣ ሕያው ነው። ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፣ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው፣ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ ሟች ለሆነው ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣል” (ሮሜ 8፥10-11)።[19] የክርስቶስ ትንሣኤ ለአማኞች ትንሣኤ ርግጠኝነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ መኻላ ነው።
በርግጥ የክርስቶስ ትንሣኤ በመርህ ደረጃ ከእኛ ትንሣኤ ይለያል። ለምሳሌ፣ የርሱ ሰውነት ሞቶ በመበስበስ አልበታተነም። ቢሆንም ደግሞ ልክ እንደሞቱ ሁሉ ትንሣኤውም እኛ ራሳችን የምንካፈልበትና ኅብረት የምናደርግበት ነው። “ከክርስቶስ ጋራ ተነሥታችኋል” በሚለው አረፍተ ነገር ላይ (ቈላ. 3፥4) ካልቪን አስተያየቱን ሲሰጥ፣ “እግዚአብሔር ልጁን ከሙታን ከሙታን ያስነሣው የልጁ ትንሣኤ ብቸኛ የኀይሉ መገለጫ እንዲሆን ሳይሆን፣ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው ያ መንፈስ ራሱ አማኞችን ከሙታን እንደሚያስነሣ ለማሳየትና በውስጣችን ያለውን የሟችነት ባሕርይ እንደሚያስወግድ ለማሳየት ነው” ብሏል።[20]
ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው ሕይወት ሰጪ መንፈስ በመጨረሻው ዘመን አማኞችንም ያስነሣል። እግዚአብሔር አብ ከሙታን የተነሣውን ክርስቶስን ከክርስቶስ በማይለይ መልኩ የአማኞች ጒባኤ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ አደረገው። ክርስቶስ ከሙታን የተነሣው የትንሣኤ በኩር ሆኖ ነው፤ በመሆኑም በመጨረሻው ዘመን የርሱን ትንሣኤ ተከትሎ አጠቃላይ ትንሣኤ ይሆናል። ይህን እውነት ጳውሎስ፣ “ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፣ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት” በማለት ይገልጻል (1ቆሮ. 15፥23)።
አስፈላጊና አይቀሬ ክሥተት
ይህን እውነት በተመለከት፣ ክሥተቱ አስፈላጊ ነው። የሰማይ ዜጐች እኛ አሁን ከሆነንነው በላይ ደስተኛ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ እኛ አሁን ካለን የተሻለ ዋስትና የላቸውም።[21] አማኞች የማይጠፋና የማይሞት የትንሣኤ አካል ሊለብሱ ይገባል (1ቆሮ. 15፥53)። በዚህ ምንባብ ውስጥ፣ “ይገባል” የሚለው እውነት በርግጠኝነት ከክርስቶስ ትንሣኤ የተወሰደ ነው፤ ለዚህም ርግጠኛ ዋስትና የርሱ ትንሣኤ ነው። በተጨማሪም የእኛ ግላዊ አካላዊ ትንሣኤ ከክርስቶስ ትንሣኤ ጋራ ተቆራኝቶ የሚፈጸም ነው (ሮሜ 8፥11)።
የክርስቶስ ትንሣኤ ትስስሩ ከክርስቶስ አካላዊ ትንሣኤ ጋራ ብቻ የተቆራኘ ሳይሆን፣ በርሱ የሆኑትን ሁሉ በመወከል የሆነ ነው፤ ርሱ ዐዲሱ አዳምና የዐዲስ ሰው ራስ እንደመሆኑ መጠን ትንሣኤ ዐዲሱን ሰው በመወከል የሆነ ነው። ስለዚህም የክርስቶስ ትንሣኤ ሌሎችን በመወከል የተደረገ የራስነት ሚና ያለው ድርጊት ነው፤ በርግጥ ርሱ ለሌሎች ትንሣኤ ዋስትና ሊሰጥ ከሙታን ቢነሣም፣ በትንሣኤ ደግሞ ለራሱ የሆነ ደስታና ክብርም ሊያገኝ ችሏል።[22]
በመሆኑም ትንሣኤ ማለት ለክርስቶስ ብቻ ሳይሆን ለእኛም ጭምር ወደ ኢመዋትነት መሻገሪያ መንገድ ነው።[23] ጳውሎስ ይህን እውነት፣ “ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እኛንም ደግሞ ከኢየሱስ ጋር አስነሥቶ ከእናንተ ጋር በፊቱ እንደሚያቀርበን እናውቃለን” በማለት ይገልጻል (2 ቆሮ. 4፥14)፤ በተጨማሪም፣ ‘ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፣ በኢየሱስ ሆነው ያንቀላፉትን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደዚሁ ያመጣቸዋል” ይላል (1ተሰ. 4፥14)።
የክርስቶስ ትንሣኤ አይቀሬ ክሥተት ነበር። ርሱ የኀጢአት ምትክ ሆኖ ቤዝዎትን ለመፈጸም ሕይወቱን ለሞት አሳልፎ እስከመስጠት ታዘዘ፤ ስለዚህም ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለም (ሐዋ. 2፥24)። ሞት ኢየሱስ ይዞ አላስቀረውም። በክርስቶስ የሆኑ ሁሉም ነገሩ ተመሳሳይ ነው። በክርስቶስ የሆኑትን ሁሉ ሞት ይዞ አያስቀራቸውም። የክርስቶስ ሞት በትንሣኤ ተቀለበሰ። እንዲሁም በክርስቶስ ሆነው ለሚሞቱ ሁሉ ሞታቸው በትንሣኤ ይቀለበሳል።
ይህን እውነት ባቪንክ፣ “ክርስቶስ እስከ መስቀል ሞት ድረስ በመታዘዝና እስከ መቃብር በመውረድ ኀጢአትንና የኀጢአትን መዘዞች ሙሉ ለሙሉ ድል ነሣ። ይህ እውነት ከሁሉ አስቀድሞ በአካላዊ ትንሣኤው ተረጋገጠ። ርሱ ከሕያዋን ምድር ተወግዶ ወደ ሙታን ዓለም ቢወረወርም፣ በትንሣኤው ግን የማይበሰብስ ዐዲስ ሕይወት ጃምሬ አበሰረ” በማለት ይገልጻል።[24]
ታላቁ ልውውጥ ገና ይመጣል
ክርስቶስ በሞቱና በትንሣኤ በኀጢአት ላይ የተቀዳጀው ታላቁ ድል በመጨረሻም አማኞች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል፤ ለሁሉም ይዳረሳ፤ በአደባባይ በግልጽ ይታወጃል። የሙታን ትንሣኤ ገና አልተፈጸመም (2ጢሞ. 2፥18)፤ ነገር ግን በዘመን መጨረሻ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ከፍጻሜ የሚያመጣበትን ጊዜ ይጠብቃል (1ቆሮ. 15፥12-55)። በርግጥ አብዛኛው ነገር አሁን እውን ተደርጓል፤ ይሁን እንጂ ታላቁ ልውውጥ ገና ይመጣል። ድነት ፍጹምነትን የሚያገኘው፣ “የሰውነት ቤዝዎት” ፍጻሜውን ሲያገኝ ነው (ሮሜ 8፥23)። አካላዊ ትንሣኤ አሁን በሕይወታች አልተከናወነውም። ሁሉም ነገር ዐዲስ የሚሆነው የቀድሞው ሥርዐት በሙሉ ካለፈ በኋላ ነው (ራእ. 21፥4)። “የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፣ ሞት በድል ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። እንዲሁም፣ ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መንደፊያህስ የት አለ?” የተባለው (1ቆሮ. 14፥54-55)እውን የሚሆነው የዚያን ጊዜ እንጂ ከዚይ አበፊት አይደለም። የሞት ፍርሀት እንደሚወገድ የተሰጠውን ተስፋ የሚያጸና እውነት የሚገኘው መልአኩ የኢየሱስ አስከሬን እየፈለች ለነበረችው ሴት፣ በተናገረውና “አትፍሪ” በሚለው የማጽናኛ ንግግር ውስጥ ነው (ማቴ. 28፥4-5)። በመቀጠልም መልአኩ፣ “እርሱ በዚህ የለም፤ እንደ ተናገረው ተነሥቷል፤ ኑና ተኝቶበት የነበረውን ቦታ እዩ” ነበር ያላት (ማቴ. 28፥6)። ይህ እውነት ዙሪያችንን ከከበበው ሞት፣ በተለይም ደግሞ ከክርስቶስ ሞት የተነሣ ከሚፈጠር ግራ መጋባት፣ ከጭንቀት፣ ለተስፋ መቁረጥና ከፍርሀት ነጻ የሚያወጣ ዜና ነው።
የመጀመሪያውና ምርጡ ክፍል
እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያሰባቸው ነገሮች በሙሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ተገልጸዋል፤ ተተግብረዋልም። ኢየሱስ ከሙታን የተነሣው፣ “ላንቀላፉት ሁሉ በኲራት ሆኖ ነው” (1ቆሮ. 15፥20፤ በተጨማሪም 15፥23 ይመ.)። በብሉይ ኪዳን አስተምህሮ፣ “በኲራት” የአጨዳው የመጀመሪያውና ምርጡ ክፍል ነው (ዘፀ. 23፥19)። በኲራት ሙሉውን ምርት የሚወክል ምርጡ ክፍል ነው። ክርስቶስ ኢየሱስ ለሙታን በመነሣት የዐዲስ ፍጥረት በኩር ነው (ቈላ. 1፥18)። የዐዲስ ፍጥረት በኲር እንደመሆኑ መጠን፣ አምላክ_ሰው የሆነው ኢየሱስ ዳግም ልደት ያገኘውን ሰው ይወክላል። የመጀምሪያ ፍሬና በኲራት በመሆኑ ክርስቶስ ከኀይላት ሁሉ የላቀ፣ በዘመናት ሁሉ ማለትም ባለፈው በአሁኑና በሚመጣው ዘመን ገዥ እና እግዚአብሔር በክብር በቀኙ ይስቀመጠው … የቤተ ክርስቲያን ራስ አድርጐ የሾመው ነው (ኤፌ. 1፥20፡22)። ርሱ በጊዜ ሂደት ከእኛ አስቀድሞ ከሙታን ተነሥቷል፤ በክብር ከእኛ የላቀ ነው። ይሁን እንጂ ደግሞ ይህን ሁሉ ያደረገው እኛን ወክሎ ለእኛ ጥቅም ነው። በዚህም ምክንያት የእኛን ትንሣኤ አስቀድሞ በመነሣት ትንሣኤያችን ርግጠኛ እንዲሆን አድርጓል። በመሆኑም፣ “በትንሣኤው የተረጋገጠውን የርሱን ዐይነት ትንሣኤ አናገኛለን።”[25]
በትንሣኤ አማኞች ለሕያው ተስፋ ዳግመኛ ተወልደዋል (1ጴጥ. 1፥3)። አማኞች በትንሣኤ ያገኙት የድነት ሥራ የመጀመሩንና የመቀጠሉን ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን፣ ፍጻሜ ማግኘት የመቻሉን ርግጠኝነት ነው። አማኞች የማይሞት፣ የማይጐድፍና የማይበሰብስ ማንነት በሰማይ ቀርቶላቸዋል። በምድር ሳሉ ደግሞ በመጨረሻው ዘመን ሊገለጥ ያለውን ድነት ይቀዳጁ ዘንድ በእግዚአብሔር ኀይል በእምነት ይጠበቃሉ።[26]
እያንዳንዱ ግለ ሰብ በትንሣኤ ይነሣል
ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብን ፈቃድ፣ “የአባቴ ፈቃድ ወልድን አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ” በማለት ነበር ያብራራው (ዮሐ. 6፥40)። “እኔም አስነሣዋለሁ” የሚለው ንግግር ተደጋግሞ ቀርቧል (ዮሐ. 6፥39፡44፡54)። ስለዚህም የክርስቶስ ትንሣኤ ጽናፋዊነትን በውስ የያዘ ነው። “እግዚአብሔር የሠረው ሥራ እንደመሆኑ መጠን የኢየሱስ ትንሣኤ ወሳኝ ክሥተት ነው፤ ይህ ክሥተት የሰው ልጆችን በሙሉ የሚያጠቃልለን የመጨረሻው ፍርድ፣ ህልውናችንን የሚናረጋግጥበት ሁኔታና የሰው ልጆችን የሚመለከቱ ሌሎች ሁኔታዎች ሁሉ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር ነው።”[27]
ይሁን እንጂ ደግሞ ክርስቶስ ከሙታን ትንሣኤ ጋራ በተያያዘ ክርስቶስ ያለው ልቀት ግርዶሻዊ ገጽታም ያለው ነው። ይህም፣ “ደግሞም እንደነዚህ ሰዎች ሁሉ፣ ጻድቃንና ኀጥኣን ከሙታን እንደሚነሡ በእግዚአብሔር ተስፋ አለኝ” በሚል ቀርቧል (ሐዋ. 24፥15)። ከሙታን ትንሣኤ ጋራ በተያያዘ በመጨረሻው ዘመን የሚነሡት አማኞች ብቻ ሳይሆኑ ኢአማንያንም ጭምር ናቸው፤ ስለዚህም በክርስቶስ ሳይሆኑ የሞቱ ሁሉ የመጨረሻው ዕጣ ፈንታቸው አሳዛኝ ነው (ራእ. 20፥11-15)። ኢአማንያን ከመስቀሉና ከባዶው መቃብር በፈነጠቀው ብርሃን ላይ ጀርባቸውን በማዞር የትንሣኤን ግርዶሻዊ ገጽታ ሊፈጥሩ ችለዋል። እነርሱም ቢሆኑ የኢየሱስን ድምፅ ሰምተው ከመቃብር ይወጣሉ።[28] የመጨረሻው ዘመን ትንሣኤ ለጻድቃን በናፍቆት የሚጠብቋቸውን ነገሮች በሙሉ በሙላት ይዞ ሲመጣ፣ በክርስቶስ ድምፅ አማካይነት የሚደረገው የሙታን ትንሣኤ በክፉኡ አድራጊዎች ላይ የመጨረሻው ፍርድ ለማስተላለድ ያመች ዘንድ ዐመፀኛችን ጭምር ከሞት ያስነሣል።
በመጨረሻው ዘመን ሙታንን የሚያስነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። ይህ እውነት፣ “ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቷል፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ” (ዮሐ. 5፥25)፤ በተጨማሪም፣ “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ 29መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ” በሚል ተገልጿል (ዮሐ. 5፥28-29)። የሙታን ትንሣኤ በሁለት ክሥተቶች አማካይነት የዐዲስ ፍጥረት ሥርዐት ይመሠርታል፤ በክርስቶስ ያመኑት ከእግዚአብሔር የተሰጠ የከበረ አካል ያለው ዘላለማዊ ሕይወት የሚያገኙ ሲሆን፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል በሠራቸው ሥራዎች ላይ ጀርባቸውን በማዞር ባለማመንና በዐመፅ የጸኑት ግን በትንሣኤ አካል ወደ ዘላለም ቅጣት ይሄዳል።
የሕይወት ዐዲስነት
የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሣኤ በአሁኑ ዓለም ጭምር ለምንኖረው ዐዲስ የሕይወት ሥርዐት ምክንያትና ምንጭ ሆኖ ያገለግላል። አማኞች ለኀጢአት ሞተው ለክርስቶስ ሕያው በመሆን ዐዲስ ሕይወት መኖር የሚችሉት በዚህ ምንክያት ነው (ሮሜ 6፥4፡11፤ 2ቆሮ. 5፥15፤ ገላ. 2፥20)።
ይህን እውነት ሮበርት ዶይሌ የተሰኘ ጸሐፊ፣
ለሙታን የተነሣው ክርስቶስ መንፈሱን መንፈሱን የላከ ሲሆን፣ ከዚህ የትንሣኤ ክርስቶስ ፋራ በእምነት አንድ የሆኑ ሁሉ፣ ከትንሣኤው በኋላ ከነበረው ዘመን ጀምሮ ሊመጣ እስካለው ዘመን ድረስ በሥራ ላይ ያለውን ኀይል ይቀበላሉ። ከጨለማው መንግሥት ወደ ብርሃን መንግሥት ተሻግረዋል፤ ከኀጢአትና ሞት ነጻ ወጥተው ወደ ሕይወት መጥተዋል (ኤፌ. 1፥15-2፥10፤ ቈላ. 1፥13፤ 1ጴጥ. 2፥9፤ ፊልጵ. 3፥7-10)
በማለት ይገልጻል።[29]
በመሆኑም ትንሣኤ አማኞች አሁን በዚህ ምድር ለሚኖራቸው ዐዲስ ዐይነት ሕይወት መሠረት ነው (ኤፌ. 1፥18_2፥10፤ ቈላ. 2፥9-15፤ 3፥1)። ክርስቶስ በራሱ ትንሣኤና ሕይወት እንደመሆኑ መጠን፣ በርሱ የሚያምኑ ሁሉ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት በመግባት የማይቋረጥ ዘላለማዊ ሕይወት ይኖራሉ (ዮሐ. 11፥25-26)። ከክርስቶስ ጋራ የተነሣን እንደመሆናችን መጠን፣ አሳባችን በላይ ባለው ነገር ላይ እንጂ በምድር ባለው ነገር ላይ መሆን የለበትም (ቈላ. 3፥1-2)። ካልቪን በዚህ ምንባብ ላይ አስተያየቱን ሲሰጥ፣ “የትንሣኤን ኢየሱስ ፈለግ ተከትለን የዐዲስ ሕይወት ኑሮ እንድንኖር ብቻ አልተጠራንም፤ ነገር ግን በትንሣኤው ክርስቶስ ኀይል የጽድቅ ሕይወት እንዴት መኖር እንዳለብን ተምረናል” ይላል።
ትንሣኤ ምግባራዊ እውነታ ነው
በመሆኑም ትንሣኤ ግብረ ገባዊ አንድምታ ያለው ምግባራዊ እውነታ ነው። የትንሣኤ የግብረ ገባዊ ሕይወት ዓለም ሲህን አሁን ባለንበት ሕይወት መኖር የተገባንን ዐይነት ባሕርይ ይቀርጽልናል። ትክክለኛው የክርስትና ሕይወት ማለት ዐዲሱን ሕይወት ለመኖር ከክርስቶስ ጋራ መነሣት ማለት ነው። ከኀጢአት ኀይል ነጻ የመውጣት ዋስትና የሚሰጠን ከክርስቶስ ትንሣኤ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር የለም። በመሆኑም የክርስትና ሥነ ምግባር ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ ላይ ተመሠረተ ነው።[30] አማኞች የሚኖሩት ዐዲሱ ሕይወት፣ ከትንሣኤው ክርስቶስ ጋራ ካላቸው ኀብረት የተነሣ የሚኖሩት ነው።[31] ይህ ማለት አሁን ባለን ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ የምንኖረው ሙሉው ሕይወታችን በትንሣኤ ክርስቶስ ሕይወት ኀይል የተነቃቃና በርሱ ችሎታ የተደገፈ፣ በሞቱና በትንሣኤው አንድ በመሆን የተገኘ፣ መንፈሳዊ፣ አካላዊና ቀጥተኛ ነው ማለት ነው (ሮሜ 6፥1-10፤ 2ቆሮ. 5፥14-15፤ ኤፌ. 2፥6፤ ቈላ. 3፥1፤ 1ጴጥ. 4፥1-2)።
ከትንሣኤው ኢየሱስ ጋራ ካለው አንድነት አንጻር መኖርና በዚያ መልኩ መመላለስ
የእውነተኛ ሕይወት ምግባራዊና ግብረ ገባዊ መሠረቱ ከትንሣኤ ክርስቶስ ሕይወት ኀይል ጋራ ከሚኖረን አካላዊና መንፈሳዊ ኀብረት የሚገኝ ነው። ክርስቶስ ከእኛ ጋራ አንድ ሆኗል፤ እኛም ከርሱ ጋራ አንድ ሆነናል። ይህ አንድነት ማለት ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶ መነሣቱ ማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ የእኛ ከርሱ ጋራ ሞተን መነሣትን ጭምር የሚያካትት ነው። “የእግዚአብሔርን ሕዝብ በሙሉ ከኀጢአት ኀይል ነጻ የማውጣት ዋስትና ሊሰጥ የሚችለው፣ ከክርስቶስ ጋራ ከሙታን እንደተነሡና ያን የትንሣኤ ኀይል እንደተቀበሉ ማመን ነው … በተጨማሪም የትንሣኤው ኀይል ለቅድስና ኑሮ የሚሆን መሠረት ይሰጠናል።”[32] ክርስቶስ ባለፉት ዘመናት በአካላዊ ትንሣኤ ስለተነሣ፣ በመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ በመወለድ እኛም አሁን በመንፈስ የተነሣን ሲሆን፣ በመጨረሻው ዘመን ደግሞ አካላዊ ትንሣኤ እናገኛለን፤ በእነዚህ ሁለቱ መካከል ስንኖር ከክርስቶስ ጋራ ከሙታን የተነሣውን አማኝ እውነተኛ ሕይወት መኖር ይጠበቅብናል። ምክንያቱ ደግሞ ከሞት ተነሥቶ ለዘላለም ከሚኖር ጌታ ጋራ አንድ የሆንን በመሆናችን ነው (ሮሜ 8፥34፤ ቈላ. 3፥1-17፤ 1ጴጥ. 3፥21)። ይህን እውነት ባቪንክ፣
በቅድሚያ ከእግዚአብሔር ጋራ ዕርቅ ሳይፈጠር የኀጢአት ይቅርታ ሊኖር እንደማይችል ሁሉ፣ በቅድሚ የኀጢአት ይቅርታ ሳይኖር መቀደስና መክበር ሊኖር አይችልም። በመጽደቅና በመቀደስ መካከል ባለመነጣጠል ለሚኖረው ግንኙነት መሠረቱ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚኖረን ሕይወት ነው። ኢየሱስ መሞት ብቻ ሳይሆን፣ ከሙታንም ተነሥቷል። ስለዚህም የሚሞት ማንኛውም ሰው ለኀጢአት ይሞታል … በሕይወት የሚኖር ማንኛውም ሰው ደግሞ ለእግዚአብሔር ይኖራል (ሮሜ 6፥10)። አማኝ ለኀጢአት ከሞተ በኋላ ከኀጢአት ኀይል ነጻ የወጣ ስለሆነ መኖር የሚችለው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው። አማኝ የክርስቶስን ሞትና ሕይወት በእምነት እንደሚቀብል በሚያውጅበት ጊዜ ለራሱ መሞቱን ያጸናል ማለት ነው፤ ይህም ንስሓና የኀጢአት ይቅርታ ተብሎ ይጠራል፤ በዚያው ቅጽበት አማኙ ዐዲስ ማንነት ይሰጠዋል
በማለት ይገልጻል።[33]
በርግጥ የትንሣኤ ኢየሱስ ባመኑ ሰዎችና ዳግመኛ የተወለደ ማኅበረ ሰብ ውስጥ ብቻ ይኖራል ማለት አይደለም (ገላ. 2፥20)። የአማኞች አእምሮና መንፈስ በሕይወትና በሰላም ውጤታማ በሆነ መልኩ የሚሞላው፣ ሕይወት ሰጪ መንፈስ በውስጣቸው በማደሩ ብቻ ነው፤ ይህ ሕይወት የሚሰጠው መንፈስ በአማኞች ውስጥ በሚያድርበት ወቅት ደግሞ፣ ከሞት የተነሣው ክርስቶስ በሕይወታቸው ያድራል (ሮሜ 8፥6፡11)። በክርስቶስ መሆን ማለት በክርስቶስ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኖ መቆጠር (ሮሜ 6፥11)፣ እንዲሁም ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው መንፈስ ወደ ውስጣን ሲገባ ለእግዚአብሔር ሕያው በመሆን (ሮሜ 8፥11) ነው። ክርስቶስ በሞቱ ከኀጢአት ጋራ የሚኖረንን ቁርኝት ሙሉ ለሙሉ ሰብሮ፣ ኀጢአትን ከሕይወታችን አርቆታል።[34] የክርስቶስን ሞት መተባበር ማለት ለኀጢአት መሞት ማለት ነው፤ ይህ ማለት ደግሞ በኀጢአት ያለመኖር ማለት ነው (ሜ 6፥2)። በትንሣኤው አማካይነት ከክርስቶስ ጋራ አንድ ለመሆን መጋጠም ማለት በዐዲስ ሕይወት መመላለስ ማለት ነው (ሮሜ 6፥4)።
አማኞች ከክርስቶስ ጋራ በሞቱን በትንሣኤው አንድ ይሆናሉ ማለት፣ አሮጌው ማንነታቸውና ሕይወታቸው ከሙታን በመነሣት የዐዲስ ሰው ባሕርይ ተቀብሎ፣ አሁን ባለው ሕይወት ሊመጣ ያለውን ዓለም ኀይል እየተለማመደ ነው ማለት ነው (ዕብ. 6፥5)። ከክርስቶስ ጋራ መነሣት ማለት አመልካች እውነት ሲሆን፣ ጠንካራ መሠረት ያለውን መንፈሳዊ እውነታ የሚያሳይ ነው። አመልካቹ እውነት ኀጢአት የሚሞትበትንና ለክርስቶስ ሕይወት የማይመቹ ባሕርያትን በሙሉ የማስወገድን እና ለክርስቶስ ሕይወት የሚመቹ ባሕርያትን በሙሉ የመልስበስን ነባራዊ እውነት ያመለክታል (ቈላ. 3፥1_17)። “በመሆኑም፣ እኛ የክርስቶስን ማንነት ይዘን ለእግዚአብሔር መኖር እንችል ዘንድ ርሱ የእኛ አካል ይዞ ሞተ፤ መለኮት የሆነው ርሱ ሥጋ በመንሳቱ እኛ በማይጠፋው የመለኮት ማንነት ተሳታፊ እንድንሆን አስቻለን በማለት መናገር እንችላለን።[35] አካላዊው የሰው ሕይወት በትንሣኤው ክርስቶስ አማካይነት ዘላለማዊ ዋጋና ጥቅም ያለው መሆኑ ታውቋል፤ ስለዚህም አሁን ያለው የእኛ ቊሳዊው አካል ዐዲስ ትርጓሜ አግኝቷል። የክርስቶስን የትንሣኤ ኀይል በመታጠቅ አሁን የምንኖረው ሕይወት በባሕርዩ ኢመዋቲ ሆኖ ለዘላለም የሚኖረው የትንሣኤ ሕይወታችን ነጻብራቅ ነው (ሮሜ 2፥7)።
የአንዳንድ ድል ሁኔታ
ከክርስቶስ ትንሣኤ አንጻር ሕይወትን ለእግዚአብሔር መኖር ሕይወትን ከተወሰነ ዐይነት ድል አንጻር ወደምመራበት ሁኔት አያመጣናል። ይህ የሚሆንበት ምክንያት የትንሣኤው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች የሆኑ ኀይላትና ዓላማዎቻቸው፣ በኀጢአት፣ በክፋት፣ በሞትና በሰይጣን ላይ ኀይል ባላቸው ኀይላትና ሥልጣናት ላይ ድልን ከመቀዳጀቱ የተነሣ ነው (ሮሜ 6_8፤ 2ቆሮ. 4፥4፤ ቈላ. 2፥11_15፤ ዕብ. 2፥14)። ይህን እውነት ዋርፊልድ፣
ልክ እንደ እኛ የሆነው ወንድማችን፣ ከሞት ጋራ ተዋውቋል፤ ይህም ባለፉት፣ በሚያልፉት፣ እና በሚመጡት ዘመናት ገዢ የሆነው ነው። ልባችን ተቃርኖ በቆመውና በከበበን በርካታ ቊጥር ባለው ሰራዊት ምክንያት የሚዝል ከሆነ፣ ከሙታን የተነሣውንና የዳዊ ዘር የሆነውን ክርስቶስን እናስታውስ
በማለት ይገልጻል።[36]
ለኀሊናችን የሆነ እምነት
ከትንሣኤው ድል ጋራ ተያይዘው ከቀረቡ ነገሮች አንዱ ከእግዚአብሔር የኀጢአት ይቅርታ የምቀበል እውነት ነው፤ ይህም ከእግዚአብሔር ጋራ ዕርቅና ሰላም የምንፈጥርበት መንገድ ነው። የትንሣኤው ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመጣ፣ “ሻሎም” ነበር ያላቸው (ዮሐ. 20፥19፡21፡26)። ይህ እውነት ትንሣኤ በአማኞችና በእግዚአብሔር መካከል ሰላምን እንዳመጣ ማሳያ ነው። ለዚህም ነው ብራኬል፣
አንድ ሰው በደልሉና በኀጢአቱ ምክንያት እግዚአብሔር እየቀጣው እንደሆነ በማሰብ አስፈሪ ስሜት ውስጥ ያለ ከሆነ፣ ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ጋራ ሰላም የሌላውና በኀሊና ወቀሳ የተወረረ ነው … እንዲህ ዐይነቱ ሰው የፍጹም ቅድስና ምሳሌ የሆነውን የትንሣኤውን ክርስቶስ ይዞ ወደ እግዚአብሔር ይቅረብ። ወደርሱ እየተጣራ ያለውንና ሙሉ ሰላምን ያለ ምንም ዋጋ የሚሰጠውን ክርስቶስን ይቀበል
በማለት የተናገረው።[37] በመሆኑም፣ ትንሣኤ ለኀሊና ዕረፍት የሚያመጣ እጅግ ድንቅ የነጻነት መንገድ ነው።
በሞት ላይ በተቃውሞ መዝመት
ሞት እውነተኛና አስፈሪ ቢሆንም፣ ከክርስቶስ ትንሣኤ የተነሣ ኀይልና አስፈሪነቱን አጥቷል። ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ምትክ ሞትን ድል አድርጐ ስለ ተነሣና በሞት ፊት ተስፋ ሊሆኑ ለሚችሉ ነገሮች በሙሉ መሠረት ስለጠላ ከዚህ በኋላ በሞት ፍርሀት ውስጥ ልንኖር አይገባም (1ቆሮ. 15፥18-19፤ 1ጴጥ. 1፥3፡21፤ 3፥21-22)። በሞት ላይ የተገኘው ድል በትንሣኤ ሊታወጅ ችሏል። ሞት ሙሉ ለሙሉ ድል ተነሥቷል፤ በመሆኑም በክርስቶስ መገኘት ውስጥ ሆነን ኢመዋቲ ሕይወት እንኖራለን። ትንሣኤ ጠላቶቻችን የሆኑት ኀጢአት፣ መርገምና ሞት መሸናፋቸውን ያውጃል። በርግጥ ከእነዚህ ኀይላት ጋራ አሁንም እንታገላለን፤ ሆኖም ግን በመሠረታዊነት የተሸነፉ ጠላቶች በመሆናቸው ልንፈራቸው አይገባንም። በምስጋና እንጂ በፍርሀት ሕይወት ውስጥ ልንኖር አይገባም።[38]
አይቀሬ ከሆነው የሞት ፍርሀት በተቃራኒ፣ ቅዱስ አትናቴዎች የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆኑ በሙሉ ሞትን እንዲንቁ፣ በሞት እንዲሳለቁና ሞት ላይ በተቃውሞ በመዝመት በከፍተኛ ተነሣሽነት ወደ ሞት እንዲተሚሙ አሳስቦ ነበር። ትንሣኤ በዚህ ሕይወት ሳለን በጽናት ከምንቋቋማቸው ከሁሉም ዐይነት መከራዎች፣ ማጣት፣ ሕመምና እና ስደት እፎይታ እንደምናገኝ፣ ለከፈልነው ዋጋ ካሣ እንደምሰጠን ተስፋ የሚሰጠን ሲሆን፣ ከዚህ ሁል የምናርፍበትን ተሐድሶም እናገኝበታለን። በተጨማሪም አትናቴዎስ፣ “አዳኙ የራሱን አካል ከሙታን አስነሥቷል። ሞት አስፈሪ ነገር አይደለም፤ በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ ሞትን ከእግራቸው ሥር ረግጠው ይንቁታል። ሞት የዘላለም ሕይወት መንገድ እንጂ መጥፊያቸው እንዳልሆነ ሙሉ ዕውቀት ስላላቸውና በትንሣኤ አማካይነት የማይሞትን የማይበሰብስ አካል እንደሚለብሱ ስለሚያውቁ ክርስቶስን ክደው ከሞት ከማምለጥ ይልቅ ርሱን አምነው መሞትን ይመርጣሉ” ይላል።[39]
የኢየሱስን ዐይነት ሐሳብና ፍቅር ማጐልበት
ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኀይል ማወቅ (ፊልጵ. 3፥10) በአንድ ሐሳብና በአንድ ፍቅር መስማማትን ይጠይቃል (ፊልጵ. 2፥2)። ከአመለካከት፣ ከእሴት፣ ከታማኝነት፣ ከተግባር፣ ከስሜት፣ ከራእይ እና ከጠቅላላው የሕይወት አቅጣጫ አንጻር ሲታይ፣ ይህ ማለት የክርስቶስን ሕይወት ማንጸባረቅና ርሱ የኖረውን ዐይነት ሕይወትና ተመክሮ ደግሞ መኖር ማለት ነው። ጳውሎስ፣ “ጻድቃንና ኀጢአን ከሙታን እንደሚነሡ በእግዚአብሔር ተስፋ አለኝ” ይላል (ሐዋ. 24፥15፡21)። ይህ እውነት ያንጻል፣ ዕውቀት ያስጨብጣል፣ የአንድ ሰው ግላዊና ማኅበራዊ የሕይወት አቅጣጫዎችን በሙሉ የተመለከቱ እምነቶችን፣ ባሕርይና ሥነ ምግባር ያበለጽጋል።[40] በዐደጋ፣ በከባድ የሕይወት ሁኔታ፣ በፈተና እና በስቸጋሪ ውጣውረድ ውስጥ ስንሆን፣ የትንሣኤ ተስፋ በቂና የገደብ የለሽ ብርታት ምንጭ ነው።
በእያንዳንዱ ቀን መሞትና እንደገና መኖር
በተግባራዊ ቋንቋ የዕለት ዕለት የሕይወት ተመክሯችን የሚገለጠው የዐዲስ ሕይወት ኑሮ የሞትና የትንሣኤ ቀመር ተከትሎ የሚፈጸም ነው። ይህም ሥጋን መግደል እና ሕያው መሆን ማለት ነው። በክርስቶስ የመሆን ሕይወት መሞትንና እንደገና መኖርን አንድ ላይ አጣምሮና አዋሕዶ የሚይዝ ነገር ነው። በርግጥ የክርስቶስን ሥቃይ መካፈል ማለት፣ በሞቱ ርሱን መምሰል ማለት እንደሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ ያትታል። ይህም ክርስቶስን በትንሣኤው ለመምሰል የሚደረግ ጥረት ነው (ፊልጵ. 3፥11)። የክርስቶስን ዳግም ምጽአት በመጠበቅ መጨረሻ፣ በክርስቶስ ትንሣኤ ለመካፈል የሚያበቃ ብቸኛው መንገድ፣ የርሱን ሥቃይ ለመካፈልና በሞቱ ርሱን ለመምሰል ፈቃደኛ መሆን ነው።[41]
በመሆኑም የክርስቶስ ትንሣኤ የተቀደሰ ሕይወት መኖር እንድንችል መነቃቃትና ኀይል ይሰጠናል። የክርስቶስ ትንሣኤ ኀይል በአጠገባችንም በውስጣችንም ነው (ገላ. 2፥20)። ክርስቶስን ማእከል ያደረገ መኖር እንድንችል የላቀ ብርታት የሚሰጠንም ይህ ነው። ብራኬል የተሰኘ ጸሐፊ፣ “ራሱን ከትንሣኤ ክርስቶስ ጋራ በእምነት አንድ ካደረገ፣” ይላል ብራኬል፣ “ይህ ሰው ነፍስን ለማንቃት ከክርስቶስ ስለሚፈልቀው ሕይወት ሰጪ መንፈስ በቂ ግንዛቤ ይኖረዋ” ይላል።[42]
ሁል ጊዜም ቢሆን ነገ አለ
“ይህ ሰው ከራሱ ተነጥሎ ሙሉን ኀይልና ችሎታውን እግዚአብሔርን ማገልገል ላይ ለማዋል የመጀመሪያውን ርምጃ የሚወስበት ይሁን” ይላል ካልቪን።[43] ነገሩ ካልቪን እንዳለውና እንደሚያምነው ከሆነ፣ የክርስትና ሕይወት ይዘትና ማንነቱ የሚወሰነው ራስን በመካድና ከኀጢአትና ራስ ማእከል ካደረገው ሕይወት ራስን ፈጽሞ በማራቅ ለእግዚአብሔር በማስገዛት ነው። ይህ ተግባር መሆን የሚችለው፣ “ሰው በራሱ ለራሱ መኖር አቁሞ ክርስቶስ በርሱ እንዲኖርና እንዲነግሥ ሲፈቅድ ብቻ ነው።”[44] በመሆኑም የክርስቶስ ትንሣኤ የሚያሳየው፣ በእግዚአብሔር እጅ ያለ ሥቃይ፣ ሕመምና ራስን መግዛት ከዚህ ሁሉ ነጻ የሚያወጣና በድል እንድንወጣ የሚያደርግ ትርጒምና አቅጣጫ ያለው ነው፤ ይህ ሁሉ የሚመጣው ደግሞ በሁሉን ቻዩ እግዚአብሔር ኀይልና አሠራር ነው። ስለዚህም የትንሣኤ ኀይል ማለት፣ ሰው ሁል ጊዜም ነገ አለ በሚለው ዕውቀት ላይ የሙጥኝ ማለት መቻል ማለት ነው።
ሐሳቡን በአጭሩ ለማስቀመጥ ያህል፣ አማኞች በአሁኑ ዘመን የሚኖሩት ሕይወት በክርስቶስ ውስጥ የተሰወረ ነው፤ ይህም ሕይወት በመንፈስ ከላይ የተወለደ፣ በመልካም የምስራች ዐዋጅ ቃል የተደገፈ፣ መልካምን ለማድረግ የሚገሠግሥ፣ ለእውነት ለመሞት ፈቃደኛ የሆነ፣ ዐዲሱን ሕይወት የሚኖርና የሙታን ትንሣኤን በተስፋ የሚጠባበቅ ነው።[45]
ለወደፊት ሊመጣ ያለውን መያዝ
ያለ ምንም ጥርጥር የሰው ልጆች ሕይወት ወደፊት ሊመጣ ያለውን ነገር በተስፋ በመጠበቅ የተቃኘ ነው። ነገ በላቀው መልኩ ሊመጣ ስላለው ነገር ያለን እምነት አሁን ያለንበት ሕይወት እንዴት መኖርና በምን መልኩ መመላለስ እንዳለብን ይቃኛል። ስለ ነገ የሚኖረው የተለያየ አመለካከት ዛሬን የምናይበትን መንገድ ይቃኛል። መጨረሻ እንዳለ ማሰብ የአሁንን ኑሮ መልክ ያስይዛል። የሰው ልጆች በሙሉ ስለ ነገ ያላቸው ምልከታ አሁንን እንዴት መኖር እንዳለባቸው ወሳኝ መርህ ይሰጣል። ስለዚህም ይህ እውነት ክርስቶስ ከሞት እንደተነሣ ለሚያምኑ ሁሉ በሁለት መልኩ የሚሠራ ነው። የዚህ ሐሳብ አመክንዮ፣ “እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በተቀመጠበት በላይ ያሉ ነገሮችን እሹ፤ 2አሳባችሁም በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ ነገር ላይ አይሁን” በሚል እውነት ሊገለጥ ይችላል (ቈላ. 3፥1-2)። በተለየ መንገድ አሁን ባለው ሕይወት ዘላለማዊ ሕይወትን መለማመድ እንድሚቻልና ይህንም ከሞት የተነሣውን የክርስቶስን ሕይወት በማጣጣም መኖር እንደሚቻል አጽንዖት ሰጥተው የሚገልጹ በርካታ ምንባባት በዮሐንስ ወንጌ ውስጥ ይገኛሉ (ዮሐ. 3፥36፤ 4፥14፤ 5፥25)።
ትንሣኤ ማለት ክርስቶስና ሕዝቡ ነገን የራሳቸው አድርገዋል ማለት ነው። አሁንና ለወደፊት ሊመጣ ያለው የላቀው ፍጻሜ የክርስቶስ ሲሆን፣ የርሱ የሆኑ ሁሉ ደግሞ ከርሱ ጋራ ይጋሩታል። ዳግመኛ መወለድ ማለት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ምክንያት በሕያው ተስፋ መኖር ማለት ነው (1ጴጥ. 1፥3)። ይህ እውነት የሚያመለክተው ሊመጣ ያለው ዘመን በክርስቶስ ትንሣኤ የተዋጀ እና ዋስትና ያለው መሆኑን ነው። ትንሣኤው ለሚጠፋው ዓለም ሕይወትና አለመጥፋትን አምጥቷል።[46]
በርጋታና በመተማመን ሕመምና ሥቃይን በጽናት ማለፍ
ትንሣኤ ክርስቲያን በመሆናችን ምክንያት የሚመጡ መከራዎችንና ሥቃዮችን የምንረዳበትን ዐውድ ይፈጥርልናል። በአጠቃላይ፣ ይህን እውነት የመጀመሪያው አማኞች ከሆኑ ከሐዋርያት ሕይወትና ተመክሮ መረዳት እንችላለን። ሐዋርያቱን የሞት ፍርሀትና የሕይወት ውጣውረድ ወደ ኋላ እንዳያስቀራቸው የክርስቶስ ትንሣኤ ብርታትና ድፍረት ሆኗቸው ነበር። የክርስቶስ ትንሣኤና ውጤቶቹ በግልም ሆነ በአጽናፈ ዓለም ታሪክ ደረጃ እጅግ ግልጽ ነበር። ይህም ክብር በሞላበትና በማይሞት አካል ከርሱ ጋራ መነሣት ነው።[47]
ልክ እንደ እኛው ሁሉ ሐዋርያው ጳውሎስ ከወንጌል ተቃዋሚዎች ባለማቋረጥ የአገልግሎቱ ዕድገት ለማቆምና ለማበላሸት ያደረጉት ጥረት ጭንቀት እንደፈጠረበት ተናግሮ ነበር (ፊልጵ. 2፥25-30)። ክርስቶስ ራሱ ስለ ጭንቀት በተወሰነ መልኩ ተናግሮ ነበር። ይህን በተመለከተ ኢየሱስ ያቀረበው የተሻለው አማራጭ ሊመጣ ስላለው የእግዚአብሔር መንግሥትና ይህ መንግሥት ስለሚያመጠው የከበረ ውጤት የማይጠፋ እምነት እንዲኖረውን የሚያወሳ ነው። በመሆኑም ተከታዮቹን፣ “እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ፤ መንግሥት ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ አላቸው” (ሉቃ. 12፥22-32)። ይህ መንግሥት በፊልጵስዮስ በሚኖሩ አማኞች መካከል ይሠራ ነበር፤ ለጳውሎስ ጭንቀት ተስፋና መፍትሔ የሰጠውም ይህ እውነት ነው (ፊልጵ. 4፥4-7)።
ይህን እውነት በተመለከት ሂለሪ ፖይተርስ የተሰኘ አባት
ዋስትናን በተመለከተ ነፍስ በደስታና በተስፋ ታርፋለች። ሞትን የምትፈራው በጣም በጥቂቱ ነው፤ ሞት የዘላለም ሕይወት ስም ይመስለኛል። አሁን ያለው ይህ ሕይወት ለሕፃን ልጅ ፊደልን መማር፣ ለሕመምተኛ ሰው መድኀኒት መውሰድ፣ ለመርከብ ነጂ መቅዘፊያውን መጨበጥ፣ ለወጣት ልጅ ሙያን መማር፣ ለወደፊት ወታደራዊ አዛዥ የመጀመሪያው ዘመቻ ከባድ እንደሚሆን ሁሉ ለእኛም ትልቅ ሸክምና መከራ ሊሆን ይችላል። አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት አሁን የምንቀበላቸውን መከራና ሥቃዮችን በጽናት ማለት ዘላለማዊ ኢመዋቲነትን መቀበያ የበረከት መንገድ ነው
በማለት ይገልጻል።[48]
ለወንጌል አገልግሎት ራስን መለየት
በ1ኛ ቆሮንቶስ 15 ጳውሎስ የክርስቶስን ትንሣኤ፣ የሙታንን ትንሣኤና አካለ ትንሣኤን በተመለከተ ሦስት ደረጃ ያለውን ሙግት ያቀርባል። ጳውሎስ ሙግቱን የሚዘጋው፣ “ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ” በሚል የማበረታቻ ቃል ነው (1ቆሮ. 15፥58)።
የትንሣኤርን ማስረጃዎች በስፋትና በተቻለን መጠን ጠንካራ በሆኑ ቃላት ከገለጽን በኋላ፣ ይህ አቀራረብ አንድ አማኝ እንደ አማኝነቱ የሚያደርጋቸውን ማንኛቸውንም ነገሮች በውስጡ የያዘ ስለሆነ፣ እግዚአብሔርን የመምሰል ሕይወት ለሚኖሩ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ሊሆን አይችልም (1ቆሮ. 15፥33-34)።[49] ነገር ግን፣ “በጌታ ሥራ” የሚለው ገለጻ ጳውሎስ ከሙሉው የምዕራፉ ጭብጥ በመውጣት በምዕራፉ መግቢያ ላይ ካወሳው የወንጌል ነገር ጋራ የተሳሰረ እውነት ያነሣል (1ቆሮ. 15፥1_2)።
በርግጥ ጳውሎስ በተለያዩ ስፍራዎች፣ “ሥራ” የሚለውን ሐሳብ በቀጥታ የወንጌልን ሥራና አገልግሎት ለማመልከት ይጠቀማል (1ቆሮ. 3፥8፤ 4፥12፤ 16፥16፤ 1ተሰ. 3፥5፤ 2ተሰ. 3፥8፤ 2ቆሮ. 6፥5፤ 10፥15፤ 11፥23)። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ የሚናገረው ነገር ከአካላዊ ትንሣኤ፣ በአሁኑና በመጨረሻው ዘመን ከምንቀዳጀው ድል፣ በመጨረሻም በኀጢአትና ሞት ላይ ስለሚሆነው ድል ጋራ የተያያዘ እውነት ነው። ከክርስቶስ ጋራ ተነሥቶ ዳግም በመወለድ ዐዲስ ፍጥረት የሆነ ሰው ሕይወት ጠንካራ፣ ወጥነት ያለው፣ የተትረፈረፈ፣ በመልካም ሥራ የሚበረታና ዋና ትኩረቱን ታላቁ የወንጌል እውነት ሥራ ላይ ያደረገ ሊሆን ይገባል።
ከአስተምህሯዊ ውሳኔዎች ጋር አበተያያዘ፣ አማኞች ለመሠረታዊ የወንጌል እውነቶች ታማኝ መሆን አላባቸው፤ በእነዚህ ተግባራት ላይ ባላመቋረጥ መሳተፍ ይገባቸዋል። አማኞች አብዛኛውን ጊዜያቸው ማሳለፍ የሚገባቸው ወንጌልን በሚመለከቱ ጒዳዩች ላይ መሆን አለበት፤[50] እነዚህ ተግባራት ምስጋና፣ ወንጌል መመስከር፣ ወንጌል ማወጅና በተቻለ መንገድና መጠን ሁሉ ወንጌል እንዲስፋፋ መሥራት ሊሆኑ ይችላሉ። አማኞች በወንጌል ሥራ ባተሌ እንዲሆኑ ተጠርተዋ፤ ይህም ሥራ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ፣ የኀጢአትን ይቅርታ፣ የአማኞችን አካላዊ ትንሣኤ ማወጅና በመጨረሻም እግዚአብሔር ክርስቶስን እንዳስነሣው ሙታንን ሁሉ እንደሚያስነሣና የመጨረሻው ፍርድ እንደሚሆን፣ እንዲሁም በእምነታቸው ለጸኑ ታማኞች ሁሉ ዋጋ እንዳለ ማወጅን ያጠቃልላል።[51]
ይህም ብቻ አይደለም፤ የክርስቶስ ትንሣኤ ራሱ የወንጌልን አገልግሎት በውጤታማነት እንድንወጣ፣ ፍጹም መታዘዝን እንድናሳይ፣ ከኀጢአትና ከክፉ ኀይላት ጋራ ያለውን ትግል በድል እንድንፈጽም (ኤፌ. 1፥1920) ያስችለን ዘንድ ዐዲስ መንፈሳዊ ኀይል ይሆንልናል። ይህ ወንጌልን የማወጅ ብርታት የሚሆነውና በጠላቶቻችን ላይ ድን እንድንጐናጸፍ የሚያስችለው ዐዲሱ የትንሣኤ ኀይል ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ የተሰጠ ሲሆን፣ የአማኞች ዐዲስ ሕይወት ልዩ መገለጫ ይሆን ዘንድ ዐዲስ ትንሣኤ ባገኙበት ቅጽበት የተሰጣቸው ነው።[52]
ኀብረት፣ የወንጌል ሥራና ተልእኮ
በአራተኛው ወንጌል ውስጥ ሐዋርያት ዓሣ እያጠመዱ ሳለ የትንሣኤው ኢየሱስ በመገለጥ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተከታታይ ውይይቶችን እንዳደረገና በተኣምራዊ መንገድ ዓሣ እንዲጠምዱ እንዳስቻለ ተዘግቧል (ዮሐ. 21፥1-25)። ተኣምራዊው የዓሣ ማጥመድ እውነት ቤተ ክርስቲያን ኀብረትን፣ የወንጌል ምስክርነትንና የወንጌል ተልእኮን ሥራ በብቃት መወጣት ትችል ዘንድ ከትንሣኤው ክርስቶስ ኀይል መለቀቁን ያሳያል (ዮሐ. 21፥1-13)። የትንሣኤ ጌታ ደቀ መዛሙርቱን እስከ ሞት ድረስ እንዲታዘዙ የሚያደርግ ፍጹም ፍቅር የሚጠይቅ ነው (ዮሐ. 21፥15-23)። ይህ እውነት ደግሞ በእምነታቸው ብርቱ እንዲሆኑ የሚያስችል ዐቅምና የወንጌል ሥራ በብቃት እንዲወጡ የሚያስችል ብርታት ከመስጠት የላቀ ነው። የዓሣ በአስገራሚ ቁጥር መያዝ በወንጌል ተልእኮ ውስጥ የተትረፈረፈ ነፍሳት እንደሚያገኙ ተስፋ የሚሰጥ ነው (ዮሐ. 21፥6፡11)። እነዚህ እውነቶች ከገለጽን በኋላ አንድ ማወቅ የሚገባ ቁልፉ ነገር በወንጌል ሥራ ላይ የሚጠበቀውን ውጤት የሚሰጠው የትንሣኤ ጌታ ብቻ እንደሆነ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ ሙታንን ማስነሣት በርሱ ኀይል ብቻ የሚደረግ ነውና። ደቀ መዛሙርቱ በሕይወትና አገልግሎታቸውንና እንዲሁም ክርስቶስን በመከተል መንገድ በየትኛውም ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ቢያልፉ፣ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት በተመለከተ ርግጠኛ የሆነ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጠው የትንሣኤው ጌታ ብቻ ነው (ዮሐ. 21፥19፡21)።
ሁሉን የሚችል ሥልጣን፣ በሁሉ ሥፍራ ዐብሮ የሚገኝ ጌታ
ክርስቶስ ሕያው ከመሆኑ የተነሣ ርሱ ከሕዝቡ ጋራ ነው፤ ሕይወታቸውን በኀይል ያስታጥቃል፣ በድካማቸው ያጽናቸዋል፣ ርሱን ከሙታን ባነሣው ዐይነት ኀይል ያበረታታቸዋል። የትንሣኤው ክርስቶስ ሁሉን የሚችለው ኀይል በእግዚአብሔር መንግሥት ሁሉ ላይ በመሆኑ ምክንያት ኢየሱስ፣ “በሰማይና በምድር” የሚለውን ገለጻ አጣምሮ ሊጠቀም ችሏል፤ ይህ ኀይል ደግሞ፣ በየትኛውም ጊዜ፣ በሁሉም ስፍራና ከመገኘት ማንነቱ ጋራ በቀጣይነት እንድሚኖር ለማመልከት፣ “እኔ ከእናንተ ጋራ ነኝ” ብሏቸዋል። ሐዋርያት እና ተከታዮቻቸው ወደ ዓለም ሁሉ ሕዝቦች በመሄድ ወንጌል እየሰበኩና እያስተማሩ ደቀ መዝሙር ማፍራት እንዲችሉ የሚያበቃው ደግሞ ይህ ከትንሣኤ ጌታ የተሰጠ ኀይልና ሥልጣን ነው (ማቴ. 28፥18-20)።
ዋና ነጥቡ የክርስቶስ ትንሣኤ አሁን ባለው መንፈሳዊ ዓለም መንፈሳዊውን ሥራ መሥራት እንድንችል ያነሣሣናል ያስታጥቀናልም፣ እንዲሁም የትንሣኤ ክርስቶስ ሕይወትና ፈለግ በመከተል ግብረ ገባዊ ሕይወት እንድንኖር ያስችለናል የሚል ነው። ይህ እውነት የዕለት ዕለት እንዲሁም የቅጽበት ቅጽበት ሕይወታችንን በዐዲስ ሰው ማንነት ልክ መኖር የምንችልበትን መለኮታዊ ኀይል ይሰጠናል። ትንሣኤ በውስጣችን ዐዲስ ዐይነት ሕይወት ይፈጥርልናል፤ በመሆኑም አማኞች አሁን ባለው ዓለም ይህን ዐዲሱን ሕይወት በተግባር መኖር ይችላሉ። “የአማኞች ዐይን በትንሣኤ ክርስቶስ ላይ የሚያነጣጥር ከሆነ፣ በልባቸው ውስጥ የክርስቶስ መስቀል በሁሉም ዐይነት ክፋቶች፣ የሥጋ ሥራዎች፣ ኀጢአትና ሰዋዊ ድካም ላይ ድል መቀዳጀት ይችላል።”[53] ይህ መንፈሳዊ ኀይል ከሙታን ከተነሣው ክርስቶስና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ የተቆራኘና የዚያም ውጤት ነው (ሮሜ 1፥4)። ይህ ኀይል አማኞች በመጨረሻው ዘመን ሊሆን ያለውን ትንሣኤ በተስፋ እየተጠባበቁ ሲኖሩ፣ በዚህ ዓለም ያላቸውን ሕይወት በእምነት እንዲኖሩ ያስችላቸዋል (ሮሜ 8፥10-17፤ ፊልጵ. 3፥10)።
[1] Vos, Reformed Dogmatics, 3.5.46; Single-Volume Edition, 581.
[2] Vos, Reformed Dogmatics, 3.5.48; Single-Volume Edition, 584; slightly amended.
[3] The term is appropriate, since ‘supersede’ can mean ‘take over from,’ but if read as ‘displace’ or ‘overthrow,’ it would be inaccurate regarding Jesus’ resurrection. Having said this, a stronger meaning is not inaccurate for our resurrection, given Paul’s radical comparison concerning our bodies pre and post resurrection in 1 Corinthians 15. There is much more continuity in Christ’s body, pre and post resurrection, than ours.
[4] Letham, The Work of Christ, 220-221; slightly amended.
[5] Torrance, Space, Time, and Resurrection, 36-37.
[6] Torrance, Space, Time, and Resurrection, 35.
[7] Calvin, Institutes, 3.25.3; 990.
[8] Oden, Systematic Theology, 2:474.
[9] Doyle, Eschatology, 27.
[10] John Murray, Redemption: Accomplished and Applied (Eerdmans, 1955; The Banner of Truth Trust, 1961), 175.
[11] E.g., Augustine, The City of God against the Pagans, 22.20; trans. R. W. Dyson (Cambridge University Press, 1150-52.
[12] Bray, God is Love, 509.
[13] Paul Helm, The Last Things (The Banner of Truth Trust, 1989), 52-53.
[14] Doyle, Eschatology, 27.
[15] Torrance, Space, Time, and Resurrection, 34.
[16] Calvin, Institutes, 3.25.3; 991 [emphasis supplied].
[17] Calvin, Institutes, 3.25.3; 990.
[18] Warfield, The Person and Work of Christ, 545, slightly amended; Warfield, Selected Shorter Writings, 1:201.
[19] Vos, Reformed Dogmatics, 3.5.48; Single-Volume Edition, 585.
[20] Calvin, Institutes, 3.25.3; 991.
[21] Jones, Knowing Christ, 168.
[22] Helm, The Last Things, 50-51.
[23] Cyril of Alexandria, Fragment 317; ACC Matthew, ed. Simonetti, 307.
[24] Bavinck, Our Reasonable Faith, 368.
[25] Calvin, Institutes, 2.14.13; 522.
[26] Bavinck, Our Reasonable Faith, 371.
[27] Torrance, Space, Time, and Resurrection, 34-35.
[28] Vos, Reformed Dogmatics, 3.5.48; Single-Volume Edition, 585.
[29] Doyle, Eschatology, 27.
[30] Oliver O’Donovan, Resurrection and Moral Order, 13.
[31] Murray, Redemption, 163.
[32] Murray, Redemption, 48-49.
[33] Bavinck, Our Reasonable Faith, 370.
[34] Bavinck, Our Reasonable Faith, 371.
[35] Hilary of Poitiers, The Trinity, 9.13; NPNF, 2.9:159.
[36] Warfield, The Person and Work of Christ, 546.
[37] Brakel, The Christian’s Reasonable Faith, 1:632; slightly amended.
[38] Barth, Dogmatics in Outline, 114; slightly amended.
[39] Athanasius, On the Incarnation, 27; ed. St. Vladimir’s, 57.
[40] An extensive treatment of how resurrection-based hope changes all of life in every regard is Timothy Keller, Hope in Times of Suffering (Hodder & Stoughton, 2021), 83-216.
[41] Doyle, Eschatology, 27.
[42] Brakel, The Christian’s Reasonable Service, 1:634.
[43] Calvin, Institutes, 3.7.1; 690.
[44] Calvin, Institutes, 3.7.1; 689-90; 689-701.
[45] Oden, Systematic Theology, 2:482.
[46] Warfield, The Person and Work of Christ, 543.
[47] Hilary of Poitiers, The Trinity, 1.13; NPNF, 2.9:44.
[48] Hilary of Poitiers, The Trinity, 1.14; NPNF, 2.9:44.
[49] Gordon Fee, The First Epistle to the Corinthians (Eerdmans, 1987 [Revised edition, 2014]), 808.
[50] Fee, The First Epistle to the Corinthians, 808.
[51] Gerald Bray ed., Ancient Christian Commentary on Scripture. New Testament VII. 1-2 Corinthians (Routledge, 2012 [Orig. 1999]), 184.
[52] Grudem, Systematic Theology, 2nd edition, 755-56.
[53] Calvin, Institutes, 3.10.6; 719.
ምዕራፍ 10
የኢየሱስ ትንሣኤ ውጤቶች
የታሪክ መጨረሻ ጅማሬ
የክርስቶስ ቤዝዎት ሥራ፣ ትምህርቱ፣ ፈውሱ፣ መከራው፣ ሞቱና ትንሣኤው ፍጻሜ የሚያገኝበት ጊዜ አለ። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ሥራ ቀጣይነት ላይ ግራ የሚያጋባ ነገር ሊኖር አይገባም፤ “ሁሌም ቢሆን ተደናቂው የአማኞች እምነት ዋና ግቡ ሕያውና ንጉሡ ኢየሱስ ነው።[1] ከሞት የተነሣው የትንሣኤው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣ “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜም ከእናንተ ጋራ ነኝ” ነበር ያላቸው (ማቴ. 28፥20)።
በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የነበሩ ፍልስጢኤማውያን አይሁዶች በታሪክ የሙታን ትንሣኤ በታሪክ ሂደት ከመጨረሻው ዘመን በፊት ይሆናል የሚል እምነት አልነበራቸውም። እነርሱ የሚችሉትንና የሚያውቁትን ድምዳሜዎችን በሙሉ አንድ ላይ አምጥተው ለማብራራት ቢሞክሩ የሚደርሱበት እውነት ትንሣኤ በእግዚአብሔር ኀይል ብቻ የሚከናወን ተግባር እንደሆነ የሚያትት ይሆናል። ክሥተቱን እነርሱ በጥበባቸውና በኀይላቸው እውን ሊያደርጒት አይችሉም። በመሆኑም ኢየሱስ ከሙታን በተነሣበት ጊዜ የሆነውን ክሥተት እግዚአብሔር ታሪክን ከፍጻሜ አምጥቶት እየዘጋ እንደሆነ አድርገው ቆጥረውት ነበር። እንዲህ ያሰቡበት ምክንያት የሚመጡ ዘመናት የሙታን ትንሣኤ የሚጀምርበት ነው በማለት ስላመኑ ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ ከተፈጸመ መጨረሻው ቀርቧል ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር ልዩ በሆነ መንገድ ተስፋ የሰጠው ተመጨረሻ ዘመን ከተጠበቀው ጊዜ ቀድሞ መከሠት ጀምሯል ማለት ነው። የሙታን ትንሣኤ ጀምሯል።
የእግዚአብሔርን መንግሥት በተመለከተም ተመሳሳይ ዕቅድ አለ። የመጥምቁ ዮሐንስና የኢየሱስ ክርስቶስ የአደባባይ አገልግሎት የእግዚአብሔር መንግሥት እንደቀረበ በማመልከት ነበር የጀመረው (ማቴ. 3፥2፤ 4፥17)። ከዚህ ጋራ ተያይዞ ግልጽ የሆነው እውነት የእግዚአብሔር መንግሥት ደረጃ በደረጃ ሙላቱን እያገኘ ሄዶ በመጨረሻም በዓለም ታሪክ ፍጻሜ ዘላለማዊ መንግሥት ሲመጣ ይጠቃለላል የሚል ነው (ራእ. 11፥15)። የክርስቶስ ትንሣኤ ቀድሞውኑ የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል የሚል አስተሳሰብ ይዞ ለነበረው ማኀበረ ሰብ፣ ይህን አቋሙን የሚያጸናለት ማስረጃ ሆኖ ሊገኝ ችሏል። የክርስቶስ ትንሣኤ የእግዚአብሔር መንግሥት ዓላማዎች ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ምልክት የሚሰጥ ነበር። ከትንሣኤው ክርስቶስ መገለጥ ጋራ ተያይዞ፣ ለረጅም ዘመን ይጠበቅ የነበረው አጽናፋዊው የመሲሑ ትንቢት በቅርቡ እንደሚጀምር የተገለጠ ሲሆን፣ ነገሩ ከተጠበቀው ቀድሞ በቃልና በትንቢት መልክ ሳይሆን፣ በተግባርና በእውነት ታየ።[2] በትንሣኤው መሠረት ጽድቅና ሰላምን ያለበት የሰዎች አገዛዝ ታድሶ ጀምሯል … እንዲሁም የክርስቶስ ሰማያዊ አገዛዝ በግልጽ ተጀምሯል፣ ተቀባይነት አግኝቷል፣ ሕያው እውነታ ሆኗል ማለት እንችላለን።[3]
የመጨረሻ ውጤት ማስጀመር
የክርስቲስ ትንሣኤ በአሁኑና በመጨረሻው ዘመን መካከል ውጥረት እንዲፈጠርና የፍጻሜ ዘመን እንዲጀመር ማድረግ የቻለ ክሥተት ነው። በወንጌላት የተዘገቡና ከትንሣኤው በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ያደረጋቸው የተለያዩ ስብሰባዎች በእግዚአብሔር በሰው መካከል እንዲኖር የታቀደውና እግዚአብሔር በሰዎች መካከል የሚኖርበት ፍጹም ኀብረት (ራእ. 21፥3) ጅማሬ ያበርሰረ እንደነበር የሚያወሱ ናቸው። እግዚአብሔር ክርስቶስን በሞት በማስነሣት የዐዲስ ፍጥረት እውነታን ሥራውን እንዲጀምር በማድረግ፣ በርሱ አማካይነት ሁሉም ነገር ተሐድሶ፣ እንደ ገና መፈጠርና ዕርቅ የሚያገኝበትን መንገደ ዘረጋ። ይህን እውነት ቶራንስ፣
በታሪክ ውስጥ የተከሠተው የክርስቶስ ትንሣኤ የኢየሱስ ቀጣይነት ያለው የሙሉ ህላዌ ታሪካዊ አካል ነው፤ የድነትን እውነት ከፍጻሜ ለማምጣት ያስችል ዘንድ ትንሣኤ ከጠፊው ዓለም በተቃራኒ የሆነ የዐዲስ ፍጥረት ጅማሮ ነው። በሌላ መልኩ ዐዲሱን ዓለምና የሁሉንም ነገር ዐዲስ ሥራኣት በሙላት ለማምጣት በሞትና በመበስበስ ላይ የተላለፈ የመጨረሻው ፍርድ ነው
በማለት ይገልጻል።[4]
ስለዚህም በክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ዘላለማዊው ዘመን በአሁኑ ዘመን መካከል ላይ ሰንጥቆ ገብቷል። በትንሣኤ አማካይነት በታሪክ መጨረሻ ሊሆን ያለውና በመላው ፍጥረተ ዓለም ላይ እንደሚሆን የሚጠበቀው የተሐድሶ ሥርዐት በታሪክ ጒዞ አጋማሽ ላይ ጣልቃ ገብቶ አሁን በድንግዝግዝ በምናየው መልኩ ተገልጧል (1ቆሮ. 13፥12)። “የክርስቶስ ትንሣኤ መላው አጽናፈ ዓለም ወይም ሰማይና ምድር የሚታሱበትንና ሙሉ ለሙሉ ዐዲስ የሆነውን ዘመን ጅማሬ አውጇል፤ ወይም ደግሞ ያ የሚጠበቀው ዘመን ጀምሯል፤ በክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት በአሮጌው ዘመን ውስጥ ዐዲሱ ዘመን ሰብሮ ጣልቃ ገብቷል”[5]
ዐዲስ ዘመን፣ ዐዲስ ጊዜ፣ ዐዲስ ሁኔታ
ከሦስተኛው ቀን በኋላ ከተከናወነው ትንሣኤ የተነሣ የድኅረ ትንሣኤው ኢየሱስ የዐዲስ ዘመን ሕይወት መኖር በመጀመሩ፣ ሕይወትና አኗኗርን እንደ ዐዲስ የሚቃኘው የዐዲስ ዓለም ጅማሬ የሆነው የዐዲስ ጊዜና ዐዲስ ሁኔታ ጀማሮም ተበሰረ።[6] በክርስቶስ ትንሣኤ የስሜት ገደብ ያኖረው መጋረጃ ተነሥቶ፣ በዘላለም ጒዞ ላይ የነበሩ የሰው ልጆች በሙሉ የሌላውን ዓለም እውነታ መለማመድ ቻሉ።[7] የአሁኑ ዓለም በበርካታ ዐይነት ክፋቶች ተለይቶ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ከክርስቶስ ትንሣኤ የተነሣ የመጪው ዘመን ኀይል በክፋት ወደ ተሞላው ወደ አሁኑ ዓለም ሰንጥቆ ስለገባ፣ ክርስቶስ ከሙታን በኩር ሆኖ ሊነሣ ችሏል።[8] የክርስቶስ ትንሣኤ ኀያሉ የእግዚአብሔር ውጥን በተግባር ሲገለጥ ምን እንደሚመስል ማሳያ ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት በሚመጣው ዘላለም ውስጥ ሊሠራ ያለውን ዕቅድ በዚህኛው ዓለም በጥቂቱም ቢሆን መግለጥ ችሏል።[9]
የታሪክ እጥፋትና መሽከርከሪያ
ስለዚህም የክርስቶስ ትንሣኤ የአጽናፈ ዓለሙና የፍጥረት ታሪክ የሚሽከረከርበት ቁልፍ እጥብ ነው ማለት እንችላለን። ይህም የሆነበት ምክንያት እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠውና አጽናፈ ዓለሙ ከክፋት ሙሉ ለሙሉ ነጻ ወጥቶ የዐዲስ ፍጥረት ሥርዐት የሚመሠረትበት ዘመን መምጣቱን ስለሚያሳይ ነው። ክርስቶስ በታሪክ አጋማሽ ላይ ከሙታን መነሣቱ፣ የመጨረሻው ዘመን መጀመሩን ማሳያ ነው። ይህም የዐዲስ ፍጥረት ጅማሬ መሆኑንና በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ ምድር መውረዱን የሚጠቁም ነው። በክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ዐዲስ ፍጥረት ጀምሯል፤ በመሆኑም አሁን እንኳን ቢሆን በክርስቶስ የሆነ ማንኛውም ሰው ዐዲስ ፍጥረት ነው (2ቆሮ. 5፥17)። በመሆኑም የክርስቶስ ትንሣኤና የርሱን ትንሣኤ ተከትሎ ለእኛ የተሰጠው የትንሣኤ ተስፋ፣ ጠቅላላው ዓለም እንደሚታደስ ከተሰጠው ተስፋ ጋራ የተቆራኘ ነው (ሮሜ 8፤1825)። የአማኝ ግለ ሰቦች ዐዲስ ሰውነት የምጀምረው በዐዲስ ልደት አማካይነት በሚገኝ መንፈሳዊ ትንሣኤ ነው። ይህ ዐዲስ ፍጥረት ፍጹም ሙላቱን የሚያገኘው ሰማይ፣ ምድርና ሁሉም ነገር በሚታደሱበት በመጨረሻው ዘመን በአካላዊ ትንሣኤ ነው (ራእ. 21፥1፡5)። በክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በሙሉ የወጠነው ዐዲስ ሕይወት እውን ሊሆን ችሏል። በተጨማሪም በእግዚአብሔር ተስፋ የተሰጠው የመጨረሻው ዘመን በይፋ ጀምሯል። ኢየሱስ ሕያው ከመሆኑ የተነሣ ትንሣኤ ያለፈ፣ የአሁንና የወደፊት ክሥተት ነው።[10] “የክርስቶስ ትንሣኤ … ዘላለማዊ ነው። ከክርስቶስ ትንሣኤ የተነሣ አማኞች ትንሣኤና ዳግም ልደት ያገኙ ሲሆን፣ በሰማይና በምድር ላይም ድል ተቀዳጅተዋል።[11]
ክርስቶስና ፍርድ
የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት የተለያዩ ነጥቦች ላይ ትንሣኤና ፍርድ ተቆራኝተው ቀርበዋል (ሉቃ. 14፥14፤ 2ቆሮ. 5፥1-10፤ ዕብ. 11፥35)። ሞትና ትንሣኤ በቁርኝት የቀረቡት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ አይደለም፤ “ፍርድ ማለት ሥልጣንን በተግባር መጠቀም እንደመሆኑ መጠን፣ የክርስቶስ ትንሣኤ ፍርድ ለመኖሩ እውነት ማረጋገጫ መሠረት የሚጥል ነው። የሁሉ ጌታ የሆነው ኢየሱስ፣ በሁሉ ላይ ፈራጀ ነው።”[12] ኢየሱስ እኛን ወኪሎ ከሞት ተነሥቷል፤ በተጨማሪም ርሱ የተነሣው ፋራጃችን ሆኖም ጭምር ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ የሚያመለክተው፣ ርሱ በእግዚአብሔር የተሾመ ፈራጅ መሆኑን ነው (ሐዋ. 10፥42፤ 17፥31)። በመላለሙና በነዋሪዎቿ፣ በሕያዋንና በሙታን ሁሉ ላይ ለመጨረሻው ዘመን የመፍረድ ሥልጣን የተሰጠው ለትንሣኤው ክርስቶስ ነው።
ከዚህ አንጻር ስንመለከት የሙታን ትንሣኤ አጽናፋዊ ዐውድ ያለው ነው። ከፍጥረት ጅማሬ አንሥቶ እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ድረስ የሞቱ ሰዎች በሙሉ ይነሣሉ። በዚህ ሁኔታ ሞትን ተከትሎ፣ የሞቱት በሙሉ፣ ታላቅም ሆነ ታናሽ በታላቁ ነጭ ዙፋን ላይ ወደ ተቀመጠው ፈራጅ ፊት ይቀርባሉ (ራእ. 20፥11-12)።
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚመጣው ሰዓት በተመለከተ፣ “እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዐይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሯል። 29ቀኝ ዐይንህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል” በማለት ተናግሮ ነበር (ማቴ. 5፥28-29)። በዚህ ሁሉ መካከል ግን መልካም በሚያደርጒ እና ክፉ በሚያደርጒ መካከል ልዩነት ይሆናል። በመጨረሻው ዘመን የሕይወት ትንሣኤ ማግኘትና ለፍርድ በትንሣኤ መነሣት ተጓዳኝ እውነቶች ናቸው (ዮሐ. 5፥19-24)፤ በመጨረሻ ዘመን አካላዊ ትንሣኤ የሚያገኙ ሁሉ ወደ ዘላለም ሕይወት ወይም ወደ ዘላለም ቅጣት ይሄዳሉ (ዮሐ. 5፥25-30)። በሁለቱም ላይ የሚፈርደው ደግሞ ኢየሱስ ራሱ ነው። ኢየሱስን በተመለከተ የሚዘመር ጥንታዊ መዝሙር ነበር። ይህ መዝሙር ኢየሱስን፣ “የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ልጅ” በማለት ይጠራዋል። በዚያ መዝሙር ውስጥ፣ “የሞትን ኀይል ድል በነሣህ ጊዜ፣ ባንተ ለሚያምኑ ሁሉ የሰማዩን መንግሥት ደጆች ከፈትህ። በአባትህ ክብር በቀኙ ተቀመጥህ። ፈራጃችን ሆነህ እንደምትመጣ እናምናለን” የሚሉ ስንኞች ይገኛሉ።[13]
የመጀመሪያው ትንሣኤና ሁለተኛው ሞት
በርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ከሙታን እንደሚያነሣ ኢየሱስ ለሦስት ጊዜያት ደጋግሞ ተናግሯል (ዮሐ. 6፥40፡44፡54)። በተጨማሪም በሌላ ስፍራ በርሱ የሚያምኑ ሁሉ እንደማይሞቱ ተናግሯል (ዮሐ. 11፥25-26)፤ እንዲሁም ደግሞ በርሱ ለሚያምኑት ቋሚ ስፍራ እንደሚያዘጋጅም ተናግሯል (ዮሐ. 14፥2_3)። በክርስቶስ ሕያው የሆኑ ሁሉ በመጨረሻም የፍርድ ቀን በዳኛውና አዳኙ ክርስቶስ ፊት ይቆማሉ፤ ከፍርዱም በኋላ ለዘላለም ወደሚኖሩበት ሁኔታ ይዘልቃሉ። በክርስቶስ ያመኑት አስቀድመው ይነሣሉ (1ተሰ. 4፥16)፤ አስቀድመ የሚነሡት ከርሱ ጋራ ለመንገሥ ነው (ራእ. 20፥4_6)። በሌላ መልኩ ደግሞ ከክርስቶስ ውጪ የሆኑ ኢአማንያን ወደ ክርስቶስ የሚመጡት ለፍርድ ብቻ ነው፤ ከዚያም ፍርዳቸውን ተቀብለው ወደ ሁለተኛው ሞት ይሄዳሉ (ራእ. 2፥11፤ 20፥6፡14፤ 21፥8)። የማይቀለበስ ፍርድ በመቀበል ከጌታ ፊትና ከኀይሉ ክብር ተወግደው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ (2ተሰ. 1፥9)። ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “በማይቀበለኝና ቃሌን በሚያቃልል ላይ የሚፈርድበት አለ፤ የተናገርሁት ቃል ራሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል፤” ብሏል (ዮሐ. 12፥48)።
ቀኑ ተወስኗል
በሐዋርያት ስብከት ውስጥ የክርስቶስ ትንሣኤ በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ የመለኮት ፍርድ ከሚሰጥበት ቀን ጋራ ተያይዞ ተወስቷል። ጴጥሮስ፣ “እግዚአብሔር ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን አስነሣው፤ እንዲታይም አደረገው፤ … ለሕዝቡ እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታንም ላይ እንዲፈርድ እግዚአብሔር የሾመው እርሱ መሆኑን እንድንመሰክር እርሱ ራሱ አዘዘን” በማለት ይናፈራል (ሐዋ. 10፥40፡42)። ትንሣኤ በመጨረሻው ዘመን በፍጥረት ማለትም በሕያዋንና በሙታን ሁሉ ላይ ሊመጣ ያለው ፍርድ አይቀሬ የመሆኑን እውነት ያጸናል። ያ ፍርድ ደግሞ በክርስቶስ አማካይነት የሚሰጥ ነው። ጳውሎስ በአቴና አደባባይ ለተሰበሰቡ ሰዎች፣ “በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን ወስኗልና፤ እርሱንም ከሙታን በማስነሣቱ ለሰዎች ሁሉ ይህን አረጋግጧል” በማለት ዐውጆ ነበር (ሐዋ. 17፥31)።
የላቀን የእግዚአብሔር ፈቃድ መተግበር
በሌላ መልኩ፣ የትንሣኤ ወንጌል ከሙታን በተነሣው ጌታ ኢየሱስ አምኖ የኀጢአት ይቅርታን በማግኘት ከመጨረሻው ፍርድ ስለመዳን ይናገራል።[14] ይህም ኀጢአት፣ ቊጣና ሞት ባለበት ዓለም ውስጥ የማይናወጥ እምነት፣ ዋስትና፣ ማጽናናት፣ ብርታት እና ደስታ የሚሰጥ እውነት ነው።
[1] Warfield, The Person and Work of Christ, 541.
[2] Oden, Systematic Theology, 2:458.
[3] Michael Horton, Pilgrim Theology: Core Doctrine for Christian Disciples (Zondervan, 2011), 216-17.
[4] Torrance, Space, Time, and Resurrection, 86.
[5] Torrance, Space, Time, and Resurrection, 31.
[6] Barth, Dogmatics in Outline, 113.
[7] Warfield, Selected Shorter Writings, 1:198.
[8] Horton, Pilgrim Theology, 221.
[9] Horton, Pilgrim Theology, 218.
[10] Paul Beasley-Murray, The Message of the Resurrection (IVP, 2000), 17.
[11] Bavinck, Our Reasonable Faith, 371.
[12] Knox, Selected Works, 3:30-31.
[13] ‘You, O God, we praise’ [Latin, Te Deum laudamus].
[14] Knox, Selected Works, 1, 60.
Copyright © 2022 by Benjamin T. F. Dean