ፀሀፊ፡ ዶ/ር ቤንጃሚን ዲን
ተረጓሚ፡ ዶ/ር በቀለ ደቦጭ
ንባብ፡ ምሩቅ ዩሐንስ
ማውጫ
- ምዕራፍ 1. በታምራቱና በመልእክቶቹ ላይ ያረፈው የእግዚአብሔር ማረጋገጫ ፊርማ 00:00
- ምዕራፍ 2. ሞቱ ትንሣኤውን ይቀድማል 00:00
- ምዕራፍ 3. የክርስቶስ ትንሣኤ ቀዳማዊ አስፈላጊነት 00:00
- ምዕራፍ 4. የትንሣኤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንበያና ታሪካዊ ዳራ 00:00
- ምዕራፍ 5. የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ባሕርይ 00:00
- ምዕራፍ 6. ትንሣኤ ሁሉን ቻይነትን መሠረት ያደረገ ነው 00:00
- ምዕራፍ 7. የኢየሱስ ትንሣኤ እውነተኝነት 00:00

ምዕራፍ 1
በታምራቱና በመልእክቶቹ ላይ ያረፈው የእግዚአብሔር ማረጋገጫ ፊርማ
በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙ በርካታ ምንባባት ኢየሱስ ዓርብ ቀን ከሰዓት በኋላ እንደ ሞተ እና እንደተቀበረ ቢያወሱም፣ ከዚያ በኋላ በቀጠለው እሁድ ሌሊት፣ ምናልባትም ርሱ ከተሰቀለ፣ ከሞተና ከተቀበረ ከ36 ሰዓታት በኋላ ከሙታን እንደ ተነሣና አስከሬኑ የነበረበት መቃብር ባዶ እንደሆነ፣ እንዲሁም በአዲስ መልክ እና ባልተለመደ ሁኔታ ኢየሱስ በሚታይ አካላዊ ማንነት ሕያው እንደሆነ ይናገራሉ። ለዚህም ድጋፍ ሊሆን የሚችሉ ታሪካዊ ማስረጃዎች የመጀመሪያው የትንሣኤ የዐይን ምስክሮች ከሆኑ ሰዎች በቀረበው በቂ መረጃ ተጠናቅሮ ቀርቧል። እነዚህ የዐይን ምስክሮች የትንሣኤ አካል ይዞ ከተነሣውና ኢየሱስ እንደሆነ ከመሰከሩት አካል ጋር መነጋገራቸውናን የተቀበረበት መቃብር ባዶ መሆኑን መመልከታቸውን መመስከር ችለዋል።[1]
በቀጥታ ስንመለከተው ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ ታሪክ በከፍተኛ ደረጃ የተገለጠ ተኣምራዊ ክሥተት ሲሆን፣ አስፈላጊነቱና ጥቅሙም እጅግ ከፍ ያለ ነው። ይህም ሊሆን የቻለው በአንድ አገር ወይም አህጉር ብቻ በተወሰነ መልኩ ሳይሆን፣ የክርስቶስን ማንነት የሰው ልጆችን ምንነት፣ የፍጥረታትን ሁሉ ሁኔታ እና የሰማይንና የምድርን አፈጣጠርና የፍጥረቱን ሁሉ ባጠቃለለ መልኩ ትርጉም ሊሰጥ በሚችልበት መንገድ ነበር።
ይህንንም ጉዳይ ስናጠና፣ ከታች እንደምንመለከትው ክርስቶስ ራሱና የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የክርስቶስ ትንሣኤ፣ ክርስቶስ የራሱን መለኮታዊ እና ሰብአዊ ማንነቱንና ያሳካቸውን ተግባራት በሙሉ በትንሣኤው ኀይሉ እንዳረጋገጠ እንደተገነዘቡት ያስረዳናል። አንድ ጸሐፊ እንዳመለከተው፣ የክርስቶስ ትንሣኤ በክርስቶስ ሕይወትና ተግባራቱ ሁሉ ላይ ያረፈ የእግዚአብሔር የማረጋገጫ ፍርማ[2] እና የእምነታችንም የመሠረት ድንጋይ ነው።[3] በተጨማሪም አንድ ሌላ ምሁር እናዳወሳው፣ በዓለም ሁሉ በሚገኙት ሃይማኖቶች ዘንድ የክርስቶስን የሕይወትና የአገልግሎቱን ታሪክ ያረጋገጠ የእግዚአብሔርን ፍርማ የእምነታችን መሠረት አድርጎ የያዘ ዐይነት ታሪክና ክሥተት ፈጽሞ አይገኝም።[4] እንዲሁም ደግሞ ይህ የክርስቶስ ትንሣኤ የትምህርቶቹን እውነተኛነትና የራሱን ማንነት በግልጽ የሚያሳይና የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ የሥራዎቹን ሁሉ ዓላማና ግብ ግልጽ በማድረግ በሞቱ አማካይነት የተረጋገጠልንን የማዳን ሥራውንም በደማቁ ያረጋግጥልናል። ይህንንም እውነት ማወቅና መረዳት ርሱ በሰማይና
በምድር ሁሉ ላይ ያለውን የአገዛዙን ሥልጣን የሚያሳይ ሲሆን፣ የመላለሙ ታሪክ በሚያበቃበት ጊዜም ርሱ በአካል ዳግመኛ በክብር ተገልጦ እንደሚፈርድ የሚያረጋግጥልን ዋስትና ይሆነናል። የክርስቶስ የመስቀል ሞት የዓለም ታሪክ መሠረት እንደሆነ ሁሉ፣ የርሱ ትንሣኤም የዓለም ታሪክ ጽኑ መሠረት ነው።
ይህን እውነት በተመለከተ ብሮተን ኖክስ የተባለ ጸሐፊ፣ እግዚአብሔር የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ፣ ገዢና የበላይ ተቆጣጣሪ፣ እንዲሁም በመግቦቱ ኀይል ደግፎ የያዛቸው አምላክ በመሆኑ ምክንያት፣ ትንሣኤው በፍጥረት ሕይወት ሁሉ ላይ ያለውን የርሱን ሉዓላዊነት በጽኑ መሠረት ላይ ያኖራል። ትንሣኤ ርሱ በኀጢአትና በክፉ ኀይላት ሁሉ ላይ ያለውን ኀይልና ልእልና ስለሚያሳይ ከትንሣኤ ሕይወት ማምለጥ ለማንም ሰው ፈጽሞ አይቻልም። ትንሣኤ የክርስቶስ ስቅላትና ሞት ውጤት ነው። በመሆኑም፣ የክርስቶስ ትንሣኤ እውንነት እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ወደ ፍጻሜና ግብ በማምጣት በጥልቅና በማይናወጥ መሠረት ላይ ለማኖር ያለውን ጥልቅ መሻት በግልጽ ያሳያል። በተጨማሪም፣ እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሙታን በማሥነሣት የሁሉ ፈራጅ አድርጎ በመሾሙ ምክንያት፣ በመጨረሻው ሁላችንም ከሞት ተነሥተን የትንሣኤ አካል በማግኘት በክርስቶስ ፍርድ ፊት እንቀርባለን።[1]
ቁልፍ ምንባባት
መጽሐፍ ቅዱሳችን በአራቱም ወንጌላትና በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የክርስቶስን ትንሣኤ እውንነት የሚይስረግጡልንን በርካት ምንባባት ይዟል። የሚከተሉት ምንባባት ከእነዚህ መጻሕፍት የክርስቶስን ትንሣኤ እውንነት እንደሚይስረግጡ የታመነባቸው ናቸው። እነዚህም፦
- የማቴዎስ ወንጌል 27፥45_28፥20
- የማርቆስ ወንጌል 15፥33-16፥20
- የሉቃስ ወንጌል 23፥44-53
- ዮሐንስ ወንጌል 19፥28-21፥21
- የሐዋሪያት ሥራ 1፥3-9 ናቸው።
በእነዚህ ምንባባት ውስጥ ከተዘረዘሩ የትንሣኤ ትረካዎች በተጨማሪ፣ ሌሎች ሐዋርያት በቃሉ ላይ ያደረጉት ትርጓሜዎችና ተግባራት ለትንሣኤው ምስክርነት ትልቅ ሚና እንዳላቸው የሚካድ አይደለም። ይህም እውነት በአዲስ ኪዳን ውስጥ በሰፊው ተሰራጭቶ ይገኛል።[1] በመሆኑም፣ ከላይ ከተገለጹ ዋና ዋና የትንሣኤ ምንባባት በተጨማሪ የሚከተሉት ምንንባባት የክርስቶስን ትንሣኤ የሚገልጹ ናቸው። እነዚህም፦
- ሐዋሪያት ሥራ 2፥22-32፤ 17፥16-21፡30-32
- ሮሜ 6፥1-14
- 1ኛ ቆሮንቶሰ 15፥1-58
- 2ኛ ቆሮንቶስ 4፥7-5፥10
- ፊልጵስዩስ 2፥9-11
- ቆላስያስ 1፥15-20፤ 3፥1-17
- 1ኛ ተሰሎንቄ 4፥13-18
- ዕብራውያን 13፥20-21
- 1ኛ ጴጥሮስ 1፥3-9
- የዮሐንስ ራእይ 1፥9-18 ናቸው።
ከላይ በሁለት ዘርፍ ዘርዝረን ካቀረብናቸው ምንባባት ባልተናነሰ የክርስቶስን ትንሣኤ ሊያብራሩ የሚችሉ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ይገኛሉ። ለምሳሌ፦
- የዮሐንስ ወንጌል 2፥18-22፤ 10፥14-18፤ 11፥1-44
- የሐዋሪያት ሥራ 3፥13-15፤ 41-4፡8-12፤ 10፥37-43፤ 17፥3፤ 23፥6-8፤ 24፥15-21፤ 25፥13-22፤ 26፥6-8
- ሮሜ 1፥3-4፤ 4፥25፤ 8፥11፡ 34፤ 10፥9፤ 14፥9
- 2ኛ ቆሮንቶስ 5፥14-15፡ 17፤ ገላትያ 1፥1-3
- ኤፌሶን 1፥15-23፤ 2፥14-22፤ 3፥14-19፤ 4፥7-11
- ፊልጵስዩስ 3፥8-11፡ 21
- 1ኛ ተሰሎንቄ 1፥9-10
- 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥1
- 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፥8-10፤ 2፥8-13
- ዕብራውያን 6፥1-3፤ 9፥24-28፤ 12፥1-2፡22-24፤ 3፥18-22
- የዮሐንስ ራዕይ 1፥1-2; 5፥6-14፤ 7፥9-17፤ 11፥15-18፤ 20፥4-6፤ 21፥1-7 እና የመሳሰሉትን መጠቀስ ይቻላል።
ኢየሱስ ከሙታን የተነሣው በቅዱስ ሥላሴ ኀይል ነበር
በ362 ዓ.ም በሰሜን አፍሪካ በአሌክሳንዴሪ በነበረው ጉባዔ ስለተወሰነው ውሳኔ አትናቴዎስ፣ “አንድ ማንነት ሦስት አካላት” የሚል አጭር አረፍተ ነገር ነበር ሐሳቡን የሰጠው።[1] በተመሳሳይ መልኩም ከቀጳዶቂያን አባቶች አንዱ የሆነው ግሪጎሪ ዘእንዚናዝዙ፣ “በሦስት አካላት ራሱን የገለጠው ሥላሴ አንድ አምላክ ነውና፤ ለእኛስ አንድ እግዚአብሔር አለን። በዚህ የሥላሴ ኅብረት አንዱ ከሌላው አያንስም፤ አይበልጥም። ከእርሱ በፊትም ሌላ ማንም አልነበረም፤ ከእርሱ በኋላም ሌላ ማንም አይኖርም። የሥላሴ አካላት በፈቃድና በግብራቸው የማይለያዩና የማይከፋፈሉ ናቸው፤ በኀይልና በሥልጣንም አንዳቸው ከሌላቸው የማይለያዩ ናቸው። ይህ አንድ አምላክ፣ በአካል የማይለያይና የማይከፋፈል ነው። ከእርሱ የወጣው ብርሃን ለሁሉ የሚሆን ነው። ብርሃን ሦስት ዐይነት ባሕርያት ያሉት ቢሆንም፣ ሦስቱም ብርሃናት አንድ ላይ ፍጹም ብርሃን የሆነ አንድ ብርሃን ነው” ብሎ ነበር።[2]
በአጭሩ ለማስቀመጥ፣ የኢየሱስ ትንሣኤ እውን ሊሆን የቻለው በሥላሴ ኀይልና ሥልጣን ነው። በሌላ ቋንቋ፣ የክርስቶስ ትንሣኤ ዋናው ተዋናይ በሦስት አካላት የተገለጠው አንዱ እግዚአብሔር ሲሆን፣ ይህ እውነት በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል። በመሆኑም፣ እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው በቅዱስ ሥላሴ ዕቅድ ስለመሆኑ ከተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት እንረዳለን (ለምሳሌ፦ ሐዋ. 2፥24፤ 3፥15፡ 26፤ 4፥10፤ 5፥30፤ 10፥40፤ 13፥30፡ 33፡ 37፤ 17፥31፤ 26፥8፤ ሮሜ 4፥17፡ 24፤ 8፥11፤ 10፥9 1ኛቆሮ. 6፥14፤ 15፥15፤ 2ኛቆሮ. 1፥9፤ 4፥14 ገላ. 1፥1፤ ቆላ. 2፥12፤ 1ኛተሰ. 1፥10፤ ዕብ. 11፥19)።
እግዚአብሔር አብ የክርስቶስን ትንሣኤ አውጇል
የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የተከናወነው በእያንዳንዱ የሥላሴ አካላት በተናጠል ሳይሆን፣ በሦስቱም የሥላሴ አካላት የጋራ ተሳትፎ ነው። ይህ እውነት ሦስቱም መለኮታዊ አካላት በአንድነት የክርስቶስን ትንሣኤ እውን እንዳደረጉት ማሳያ ነው። ይሁን እንጂ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር አብ ሙታንን እንደሚያስነሣ በመናገሩ ምክንያት (ዮሐ. 5፥21)፣ ኢየሱስን ከሙታን በማንሣት ረገድ እግዚአብሔር አብ ቀዳሚውን ሚና ተጫውቷል ማለት እንችላለን። በተመሳሳይ መልኩም እርሱ በመጨረሻው ዘመን ሙታንን ሁሉ በማስነሣት ቀዳሚውን ሚና ይወጣል። በመጽሐፍ ቅዱሳችን በክርስቶስ ትንሣኤ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የመለኮት ተግባራትም ጭምር እግዚአብሔር አብ ቀዳሚውን ስፍራ ይዞ እናያለን (ገላ. 1፥1)። ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ አማኞች በጻፈው ደብዳቤው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን አሳልፎ የሰጠው ክፉ ከሆነው ከአሁን ዓለም ሊያድነን ሲሆን፣ እርሱን ከሙታን ያስነሣው ደግሞ እግዚአብሔር አብ ትእዛዝና ፈቃድ ስለመሆኑ ገልጧል (ገላ. 1፥1-3)። በተጨማሪም ጳውሎስ ለሮሜ አማኞች በጻፈው ደብዳቤ ክርስቶስ ከሙታን የተነሣው በአብ ክብር እንደሆነ በመግለጽ ይህን ሐሳብ ያጠነክረዋል (ሮሜ 6፥4)። በተመሳሳይ መልኩም ኤፌሶን 1፥17-20 ባለው ክፍል፣ “የክብር አባት የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ይበልጥ እንድታውቁት፣ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ ያለ ማቋረጥ እለምናለሁ። እንዲሁም በእርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩለእኛ ለምናምነውም ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን ኀይሉን እንድታውቁ እጸልያለሁ። ይህም ኀይል እንደ እርሱ ታላቅ ብርታት አሠራር፣ ክርስቶስን ከሙታን ሲያስነሣውና በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው የታየው ነው” ይላል።ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባቱ ፈቃድ ሙሉ ለሙሉ በመታዝዘ ከርሱ የሚጠበቀውን ሁሉ በማሟላቱ ምክንያት አባቱ ደግሞ ይህን ለማድረግ ስለፈቀደ ነው።[1]
እግዚአብሔር አብ ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን በማስነሣት በርሱ ማንነትና በሥራውቹ የፈጸማቸውን ነገሮች ፋይዳና ጥቅማቸው ምን ያህን እንደሆኑ ማረጋገጥ ችሏል። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ሕይወትና ሥራ እንዲሁም በትንሣኤው ከተፈጸመው ሥራ የተነሣ በርሱ ያመኑትን ሁሉ ርሱ ባለበት ሥፍራ አስቀምጧል። ከዚህም የተነሣ በኀጢአታችንን ይቅርታ ስላገኘን በበደላችንና በኀጢአታችን ምክንያት ራሳችንን ልንከስ አይገባም። በደላችንና ኀጢአታችን በሙሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሥራ ተወግዶልን ከርሱ ጋር በትክክለኛው ስፍራ ስለተቀመጥን፣ ፈቃዱን በመታዘዝ ልንኖር ይገባናል። ይህን እውነት ሐዋርያው ጳውሎስ ሮሜ ምዕራፍ 3 እና 4 ላይ፣ በተለይም ደግሞ 3፥21-26 እና 4፥23-25 ባለው ክፍል አስፍሮልናል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከበደሉና ከኀጢአቱ ነጻ አውጥቶ በማጽደቅ ከርሱ ጋራ ትክክለኛ ኅብረት ማድረግ በሚችልበት ስፍራ ላይ አስቀምጧል። ለዚህ አዲስ ኅብረት መሠራት የሆነውን የክርስቶስን ትንሣኤ ሥራ የሠራው ራሱ እግዚአብሔር ነው። እንዲሁም ደግሞ ኀጢአተኛ በሆኑ የሰው ልጆች ለተጠሰው የርሱ ሕግ መፍትሒ በማበጀት በክርስቶስ ኢየሱስ የታደሰውን አዱሱን ሕግ የሰጠን ራሱ እግዚአብሔር ነው።[2]
እግዚአብሔር ወልድ (ኢየሱስ ክርስቶስ) ራሱን ከሙታን ተስነሥቷል
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ልንረዳው የሚገባ ትልቁ እውነት፣ ነገር ሁሉ የርሱ የሆነና ሁሉን ማድረግ የሚችለው እግዚአብሔር ከርሱ የተነገኘውና የተፈጠረው ነገር በሙሉ ብቸኛ ምንጭ (autotheos) መሆኑን ነው። ይህ እውነት በትንሣኤው በተገለጠ ሚናው ሊረጋገጥ ችሏል። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር የድነት ተግባር ሊፈጽም ከእግዚአብሔር አብ ተልኮ ቢመጣም፣ ራሱ ደግሞ አምላክ ነው። በመሆኑም፣ ሁሉን የማድረግ ሥልጣናን ኀይል አለው። ኢየሱስ ርሱ ራሱ ትንሣኤና ሕይወት መሆኑን ገልጧል (ዮሐ. 5፥25)። ይህ የሚያሳየው የርሱን ማንነትና መለኮታዊ ባሕርዩን ነው። እንዲሁም ደግሞ፣ አብ በራሱ ሕይወት እንዳለውና ወልድ ደግሞ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው እንደሰጠው ተናግሯል (ዮሐ. 5፥26)። ይህም ኢየሱስ ልክ እንደ አብ በራሱ ሕይወት ያለው አምላክ መሆኑን ያሳያል (ዮሐ. 1፥4፤ 14፥6፤ 1ዮሐ. 1፥1_2)። ኢየሱስ ክርስቶስ ቢያንስ በሕይወቱና በትንሣኤው ዙሪያ ባውራባቸው ሁለት ጊዜያት እርሱ መላኮታዊ ኀይል፣ ሥልጣንና መብት እንዳለው አውጆ ነበር። በመሆኑም፣ ርሱ ራሱን ከሙታን ማንሣት የሚችልበት መለኮታዊ ኀይል እንዳለው ከዚህ እውነት መረዳት እንችላለን። ለምሳሌ፦ ከፈሪሳውያን ጋር በነበረው ሙግት፣ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስት ቀን መልሼ አነሣዋለሁ” ብሎ ነበር (ዮሐ. 2፥19-21። ይህ ንግግሩ ስለመሆኑ ከማቴዎስ 26፥61 እና ማርቆስ 14፥58፤ 15፥29 ማስረገጥ ይቻላል።
በተመሳሳይ መልኩም፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን (exousian) አለኝ፣ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን (exousian) አለኝ፤ ይህችን ሥልጣን ከአባቴ ተቀበልሁ” እንዳለው፣ ርሱ ሁሉን በፈቃዱ የማኖርም ሆነ የማንሣ፣ ወይም ደግሞ ያለ ማኖርም ሥልጣን በርሱ ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሠረተ አምላክ ነው። ከዚህም የምንረዳው እውነት፣ የክርስቶስ ትንሣኤ የተፈጸመው በቀጥታ በራሱ ዕውቀትና ፈቃድ ሲሆን፣ ይህም ሥራው የርሱን ፍጹም መለኮታዊ ማንነቱን የሚገልጽ ነው። ነፍሱን ለማኖርም ሆነ ለማንሣት፣ እንዲሁም ቤተ መቅደሱን ለመገንባትም ሥልጣን እንዳለው በማውሳቱ ጌታ ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ እያወጀ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ከሙታን በራሱ ኀይል መነሣት የራሱ መለኮታዊ ልዩ ተግባሩ ነው ማለት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ጌታ ኢየሱስ ሥልጣን ሁሉ ከአባቱ እንደተሰጠው ይናገራል። ይህም ነገር ሁሉ ከአባቱ በተሰጠው ሥልጣንና በርሱ ትእዛዝ እንደሚሆን ያጸናል ማለት ነው። ሌላው ልናውቀው የተገባው እውነት፣ ክፉውን ማለትም ሞትን መበቀል በቀዳሚነት የአባቱ ሥራ እንደሆነ ቢናገርም፣ ርሱ ራሱ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ይህን የማድረጉ ተግባር የርሱም ጭምር ነው።
በመሆኑም፣ ይህ እውነት የክርስቶስ ትንሣኤ ዋናው ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንደሆነ ይገልጥልናል። ምንም እንኳን ርሱ በሞተበት ወቅት ሥጋና ነፍሱ የተለያዩ ቢመስሉም፣ በመለኮታዊ ህለዌው ግን ርሱን ህልው ካደረገው መለኮታዊ ሕይወት አልተለየም። ስለዚህም፣ በትንሣኤው ወቅት በተደረገው ተሐድሶ ነፍሱ ከትንሣኤ አካሉ ጋራ እንደገና የተዋሐዱ ሲሆን፣ መለኮታዊ አካሉ ነፍሱን ወደ እግዚአብሔር መገኛ ስፍራ፣ ማለትም ወደ ሦስተኛ ሰማይ ልከውታል ማለት ነው።
የክርስቶስ ኢየሱስ ሥጋና ነፍሱ የአንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋና ነፍስ እንደመሆናቸው መጠን፣ ርሱ በሞተበት ወቅት የተለያዩ ቢመስሉም፣ በመለኮታዊ ማንነቱ ግን ሁለቱም ሳይለያዩ እንደነበሩ ማወቅ ይቻላል።
በመሆኑ፣ ኢየሱስ ክርስቶ በመለኮታዊ ኀይሉ የራሱን አካል ከሙታን በማስነሣቱ ምክንያት የርሱ ትንሣኤ በራሱ መለኮታዊ ኀይልና ሥልጣን እንጂ በሌላ የተደረገ እንዳልሆነ መደምደም እንችላለን ማለት ነው። ኢመዋቲ የሆነው መለኮታዊ ማንነቱ መዋቲውን ሰዋዊ አካል ከሙታን በማስነሣቱ ምክንያት፣ ክርስቶስ ከሙታን የተነሣውና ሕያው ሆኖ በመኖር የቀጠለው በራሱ ኀይልና ሥልጣን ነው።[1]
በተጨማሪም የክርስቶስ ሰዋዊው ባሕርዩ፣ በተለይም በራሱ ፍጹም ሰዋዊ መንፈስ ውስጥ የነበረው ኀይል፣ ሙት ሰውነቱን በማንቀሳቅስ ራሱን ከሙታን ያስነሣው ዘንድ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል።[17].[2]
መለኮታዊውንና ሰብአዊ ባሕርያቱን በተመለከተ፣ የክርስቶስ የትንሣኤ ከእግዚአብሔር ወልድ የማዳን ሥራ አንዱና ዋናውን ተደርጎ ሊቆጠር ይገባል፡፡ ምክንያቱም፣ ሌሎችን ከሞት ከማዳኑና ከመታደጉ በፊት፣ ርሱ ራሱ ሌላ አዳኝ የሚያስፈልገው ሳይሆን፣ በራሱ ኀይል ሞትን አሸንፎና ድል አድርጎ የማዳን ኀይሉን መግለጥ ይገባዋል።[3] እንደ በርካታ ምሁራን ገለጻ ከሆነ፣ የመድኃኒታችን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤን ከሌሎች፣ ማለትም በራሳቸው ኀይል የራሳቸውን ትንሣኤ ማግኘት ከማይችሉ ፍጡራን ሁሉ ልዩ የሚያደረገው ይህ ሥራው ነው። የኢየሱስ ትንሣኤ በራሱና በእግዚአብሔር አብ ኀይልና ሥልጣን የሆነ ነው። በመሆኑም፣ የእርሱን ትንሣኤ ከሌሎቹ ትንሣኤ ልዩ የሚያደርገው ይህ እውነት ነው።
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን የኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን አስነሥቶታትል
የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የመንፈስ ቅዱስን ሥራም ጭምር ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ሮሜ 8፥11 ላይ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን እንዳስነሣው ሲያትት (ሮሜ 8፥11)፣ በተመሳሳይ መልኩም ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ሕያው ስለ መሆኑ ያወሳል (1ጴጥ. 3፥18)። መጽሐፍ ቅዱሳችን በበርካታ ስፍራዎች መንፈስ ቅዱስ ለፍጥረታት ሕይወትን የሚሰጥ አምላክ ስለ መሆኑ ይገልጻል። በመሆኑም፣ እነዚህ ነገሮች የሚያጸኑት መንፈስ ቅዱስ ከዚህ በፊት ለተፈጠሩና ለወደፊትም ለሚፈጠሩ ሁሉ ሕይወት የመስጠት ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑን ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ ሮሜ 1፥4 ላይ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ እግዚአብሔር ልጅነቱ የሚገልጠው በቅድስና መንፈስ ከሙታን በመነሣቱ አድርጎ ነው። ሊዮ ሞሪስ የተሰኘ የአዲስ ኪዳን ምሁር፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኀይል የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን በማስነሣት ስለመገለጡ ያትታል (1988፡46)። ከሁሉ በላይ የመንፈስ ቅዱስ ኀይል ሚና የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ በመቃብር ውስጥ ሳለ ከሙታን እንዲነሣ ኀይል በመስጠት ሲሆን፣ ይህ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም እንድጸነስ በማድረግ የጀመረው መለኮታዊ ተግባር የቀጠለበትን እውነት ያመለክታል (ሉቃ. 1፥35)። በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስን አካልና ነፍስ አንድ በማድረግ ትንሣኤ መስጠቱን መረዳት እንችላለን (ጆነስ፣ 164)። መንፈስ ቅዱስ በማርያም ማሕፀን ውስጥ የክርስቶስን መለኮታዊና ሰብአዊ ባሕርያት አንድ አንድ አድርጎ ጽንስ እንዲፈጠር እንዳደረገ ሁሉ፣ ይኸው መንፈስ ቅዱስ በተመሳሳይ መለኮታዊ አሠራሩ ክርስቶስን ከሙታን በማስነሣት ለዘላለም ሕያው እንዳደረገው እንረዳለን።
ማጠቃለያ
ይህን ክፍል፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሣኤ ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገው በእግዚአብሔር አብ የፈጻሚነት ውሳኔ፣ በልጁ ኢየሱስ አካሉ ላይ እንዲካሄድ በፈቀደው ነጻነትና በመንፈስ ቅዱስ ተግባራዊ ኀይል ነው በማለት ማጠቃለል እንችላለን።[4]
ምዕራፍ 2
ሞቱ ትንሣኤውን ይቀድማል
አስደሳች ርግጠኝነት
“እኛን መሆን ማለት ምን ማለት ነው?” ይህን ጥያቄ፣ እንደ ሰው ዘር፣ በእያንዳንዳችን ደረጃ፣ “እኛን መሆን ምን ማለት ነው?” በሚል እና “በኅብረት ደረጃ እኛን መምሰል ማለት ምን ማለት ነው?” በሚል በሁለት መልኩ ማየት እንችላለን።[1]
የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሣኤ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ የነበረው ሕይወቱና አገልግሎቱ ማብቂያ ያገኘበት ክሥተት ስለመሆኑ ከወንጌላት ዘገባ መረዳት እንችላለን። በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ የዚህ እውነት ታሪካዊ ዳራውና ቀጥተኛ ዐውዱ የሰው ልጆች ሁሉ ሞት ሲሆን፣ በተለየ መልኩ ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም እንደምንሞትና በምድር ላይ እንደ ፈሰሰና እንደማይታፈስ ውሃ እንደሆንን ያወሳል (2ሳሙ. 14፥14)። ይህ እውነት የሰው ልጆችን ታሪክና ፍጻሜውን አጠቃልሎ የያዘ ነው። በአጭሩ፣ ሞት ጨካኝና የሰው ልጅ ከቶም ሊያመልጠው የማይችለው ጠላት ስለመሆኑ ከዚህ እውነት እንገነዘባለን። ሞት ማንም የማይወደው ክፉ ጠላት ቢሆንም፣ ማንም በየትኛውም መንገድ ከሞት ማምለጥ አይችልም። እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ሲፈጥር፣ ከእርሱና ከሌሎች ፍጥረታት ጋራ ጥብቅ ኅብረት እያደረገ የደስታ ሕይወት እንዲኖር ነበር። ይሁን እንጂ ሞት ከዚህ ኅብረት የሚገኛውን ደስታ ትርጉም የሚያሳጣ ባላንጣ ነው። በመሆኑም፣ ሞት ልናመልጠው ወይም ልናስወግደው የማንችለው ትልቁ ጠላታችን ነው። እንደ ማንኛውም ሰው ስናስብ ስለሞት ከማሰብና በሞት ፍርሀት ከመዋጥ በስተቀር ከሞት በኋላ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ካለመቻላችንም በተጨማሪ ለዚህ ችግር መፍትሄ ማበጀት የማንችል ደካማ ፍጡራን ነን።
በተለይም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሞት ክፋትና አስደንጋጭነት ከሚያመጣው አሰቃቂ ጭንቀት፣ ሥቃይ፣ ጭካኔና ዐመፀ ሥራው ጋራ ዐብሮ ይነሣል። እነዚህ ሁሉ አስቀያሚ ክሥተቶች በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የማይቋረጥ ታላቅ ፍርሀትና ሥጋት እንደሚፈጥር እውን ነው። የሰው ልጆች በሙሉ ዘወትር ስለ ሞት በሰሙ ቁጥር በታላቅ ድንጋጤ፣ ጭንቀት፣ ተስፋ መቁረጥና መሸበር ውስጥ ይገባሉ።
ለምሳሌ ያህል፣ እጅግ የምንወዳቸውን ማለትም ልጆቻችንን፣ ወላጆቻችንን፣ የቅርብ ወዳጆቻችንን ወይም የሥራ ባልደረቦቻችንን በሞት መነጠቅ እጅግ አሳዛኝ ክሥተት ነው፤ ይህም የጥልቅ ሥቃይና ሐዘን ምንጭ ይሆናል።
አስቸጋሪና አከራካሪው ጉዳይ
በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የሚደርሰው ይህ የሞት አስደንጋጭና አሰቃቂ ባሕርይ፣ ስለ ክርስቶስም ሆነ የሰው ልጆች ሁሉ ትንሣኤ ትልቅ እውነት እንድንማር ያስችለናል። የሞት ጨካኝ ባሕርይ በሰዎች ዘንድ መፍትሒ የሌለው ጉዳይ በመሆኑ፣ ትንሣኤን አከራካሪ ነገር አድርጎታል። ይሁን እንጂ አንድ ትልቅ እውነት ማወቅ አለብን። የክርስቶስ ትንሣኤ እውነተኛ ክሥተት ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ እውነተኛ ክሥተት መሆኑ ደግሞ ስለ ሙታን ትንሣኤ የተሰጠውን ተስፋ እውነተኛ አድርጎታል። በመሆኑም፣ የትንሣኤ ውጤታማ በሆነ መልኩ የሚቀጥል እውነት ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ እውነት ካልሆነ፣ እግዚአብሔር ሞቶ የቀረ አምላክ ስለሚሆን፣ ስለወደፊቱ የሚኖረን ተስፋ ከንቱና ባዶ ይሆንብናል ማለት ነው።
የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ገለጻ እንዳለ የምንቀበል ከሆነና ክርስቶስ ከሙታን የተነሣ እንደሆነ፣ ይህ ዐውዳዊ ፍቺና የፍቺው እውነት ክርስቶስ ኢየሱስን ከፍጥረት ሁሉ በላይ ተወዳዳሪ በማይገኝለት ስፍራ ያስቀምጠዋል። ይህም የሆነበት ምክንያት፣ የክርስቶስ ትንሣኤ በሌላ በማንም ፍጡር፣ በየትኛውም መልኩ ሊደረግ የማይቻል ክሥተት ስለሆነ ነው። ይህ ክሥተት ደግሞ ክርስቶስን ከፍጥረት ሁሉ ፍጹም የተለየ ያደርገዋል። ርሱ ልዩ አምላክ፣ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ጌታ፣ የዓለም ሁሉ መድኀኒት እና የምድር ሁሉ ፈራጅ ነው። “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቷል” የሚለው እውነት በታሪክ የግጭትና የጭቅጭቅ ምንጭ ሆኖ የኖረ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሣኤ ሌሎች አማራጮችን ከቶ የማይቀበልና በብዙ ተግዳሮቶች የተሞላ በመሆኑ ነው።
መጠፋትን መጠባበቅ
ከአውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1543 እስከ 1863 ድረስ የነበረው የሰው ልጅ ዕድሜ ገደብ ከ40 ዐመት በታች ነበረ። እንዲሁም አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዚህ ዘመን ከመቶ ዐሥራ አምስት እጅ ሰው አርባ ዓመት ሳይሞላው ይሞታል። ይህ የሚያሳየው የሰው ልጅ አማካይ የመኖር ዕድሜውን ቢያሻሽልም እንኳን ሞትን ማስቀረት ያለ መቻሉን ነው።
የሰው ዘር በሙሉ በኀጢአት ምክንያት የተረገመና ለሞት የተዳረገ ነው። በመሆኑም ከጥንት ዘመን ጀምሮ እስከ ዘመናዊው ዓለም ድረስ የታወቀው ግልጹ እውነት ሞትን ጨምሮ ነገር ሁሉ መጨረሻና ማብቂያ ያለው መሆኑ ነው። ሞት የሰው ልጆችን የመኖር ተስፋ አቃውሶ የሚያጨልም ኀይል ነው። ለሰው ልጅ ከሞተ በኋላ ተመልሶ በሕይወትን የመኖር ዕድል የለውም። ይህን እውነት የኮርማክ ሚክካርቲ የተሰኘ ጸሐፍ ሐሳብ በሚገባ ይገልጻል፤ ሚክካርቲ፣ “ዋጋ ልተሰጠው የተገባውና ብቸኛው ዓለምህ የሆነው ይህ ሕይወትህ ያበቃለታል፤ ተመልሶን አይመጣም። የጠቅላላው እውነታ እልም ብሎ መጥፋቱ እውን ነው። ይህ ጥፋት እስኪመጣ ድረስ፣ ጠቅላላው ገዥ ሐሳቦች በነበሩበት ይቆያሉ” በማለት ገልጾ ነበር።16
ይህ ጉዳይ ቆም ብሎ በጥሞና ማሰብን የሚጠይቅ ነው። ስለ ሰው ልጆች ዕድሜና ተከትሎት ስለሚመጣው ሞት በጥልቅ ካሰባ በኋላ፣ በእግዚአብሔር የማያምን አንድ ፈላስፋ በሕይወቱ መጨረሻ ላይ በታላቅ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተመልቶ ስለሞት ጫኔና የሰው ልጆች የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር፤
እንደ ብረት የጠነከረው ሌሊት በላዬ ላይ ወርዶብኛል … ከዕንቅልፍ መንቃት እንደማይኖርም ተስፋ ሰጥቷል። ከዚህ በፊት የሰው ሕይወት ትርጉም የለሽነት፣ የማይጨበጠው ብናኝ መሻቱና ጭካኔው በሙሉ፣ በአንድ ሙዚቃ ውስጥ እንደተሰነቀረ አነስተኛ ኮርድ፣ ወይም እጅግ አስገራሚ በሆነው የውብ ከዋክብት ክምችት ውስጥ እንዳለችና በሥነ ምሕዋር ታሪክ አንድ ጊዜ ተከስታ እንደሚትከስም አንዲት ኮከብ በሕይወት ዑደት ውስጥ የተሰነቀረ ትንሽ ነገር መስሎ ይታየኝ ነበር። አጽናፈ ዓለሙ በመላለም ሞት የሚደመደም ቢሆን ምናለበት? ይህ ቢሆን ኖሮ ነገሩ የሥርዐት መናጋት ጉዳይ ብቻ ይሆን ነበር። ይህም አስደናቂ ነገር በሆነ ነበር። ይሁን እንጂ በነፍሴ መስኮት አሻግሬ ስመከለት እነዚህ ነገሮች በሙሉ ባዶ ጨለማና ከንቱ ምናባዊ ቅዥት ወደ መሆን ተቀይረዋል። የከዋክብት ክምር ክሱትነት፣ የከዋክብት ውልደትና ሞት፣ በስሜቴ ዓለም የተፈጠሩና በጥምረት የሚሠሩ ምናባዊ ትርክት ሆነዋል፤ እንዲሁም ስለዚህ ነገር ብዙ የሚያውቁ የሚመስሉ ሌሎችም ጭምር ከእኔ የተሻሉ አይደሉም። የዘመናችን ስነ ፈለክ አስገራሚ በሆነ መልኩ ከተረከልን በተቃራኒ አጽናፈ ዓለሙ ጨለማና ጠባብ ክፍል ነው። በርግጥ ሁሉም እስረኛ ርሱ ካለበት የጨለማ ክፍል ውጪ ያለው ዓለም ነጻና ብሩህ እንደሆነ ያስባል። ይሁን እንጂ መላለሙ በሙሉ እስር ቤት እንደሆነ አሁን ተረድቻለሁ። አሁን በሕይወት ሳለሁ ጨለማው ያለው ውጪ ነው፤ ይሁን እንጂ ሲሞት ጨለማው ከውስጤ ይሆናል። የዚያኔ የምደመምበት ነገር አይኖርም፤ አሻግሬ የማየው ሰፊው አጽናፍ የለም። በሞት ጣር ላይ ሲሆን የመኖር ትግል ውስጥ እገባና ወዲያው ወደ ምንምነት እቀየራልሁ። በእንዲህ ዐይነት ዓለም ውስጥ ሕይወት ለምን ኖረ? ሞትስ?16
ይህም አባባል ትክክል ከሆነ፣ የሰው ልጅ በዚህች ምድር ሳለ፣ ሞት የመጨረሻውን አሻራ ማሳረፉ አይቀሬ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ሞት የሰው ልጆችን ምድራዊ ተስፋ የሚያጨልም አማራጭ የሌለው የመጨረሻው ነገር ነው። በተለይም ደግሞ ሞት እግዚአብሔር የለሾች ከምድር ላይ ፈጽሞ የሚወገዱበት መንገድ ነው። ለኢአማኛን መሞት ማለት ፍጹም ወደሆነው ጽጥታ ውስጥ መግባት ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ህልውናቸው ያበቃል።
በእግዚአብሔር ለማያምኑ ሞት የሕይወት መጨረሻቸው፣ ማለትም የምድር ሕይወት ማብቂያቸው ነው። ይህ እውነት ያልተለመደና ተቀባይነት የሌለው ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ደግሞ በእግዚአብሔር የማያምኑ ሁሉ ይህን በእምነት ብቻ መቀበል የሚቻለውን እውነት ማመን ስለማይችሉ ነው።
በዓለማችን ከሚገኙ ሃይማኖቶች በርካቶቹ የሰው ልጅ ከሞተ በኋላ እንደገና ህልው ሆኖ መኖር ይችላል ብለው የሚያምኑ ናቸው። ለምሳሌ፦ እንደ አርጣጣሊስ ፍልስፍና እና የሂንዱዚም እምነት፣ የሰው ልጆች ዘላለማዊ ፍጡራን ናቸው። በመሆኑም፣ ፍጥረት ጅማሬ የሌለው ሕይወት እንደነበራቸው ሁሉ፣ ፍጻሜ የሌለው ዘላለማዊነት ይኖራቸዋል። ፍጥረታት ፍጻሜ ለሌለው የሕይወት ዐደት የተወሰኑ ናቸው። በተመሳሳይ መልኩም እንደ ፓይታጎራውያን (6ኛው ክፍለ ዘመን) እና የኒቼ (19ኛው ክፍለ ዘመን) አመለካከት ከሆነ፣ የሰው ሕይወት በየትእየሌለነት ዕጣ ፈንታ ውስጥ ሆኖ በዘላለማዊ ዑደት የሚኖር ነው። እንደነዚህ ፈላስፎችና ሃይማኖቶች አስተሳሰብ ከሆነ፣ ይህ አጽናፈ ዓለምና ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ ከጠፉ በኋላ እንደገና ተመልሰው በመከሰት ዐደት ላይ ይሆናሉ እንጂ ፈጽሞ አይጠፉም።
ይሁን እንጂ የይሁዲ እምነት፣ ክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት የሰው ልጆች ከሞት በኋላ ፈጣሪ በወሰነላቸው ሁኔታና ርሱ ባዘጋጀው ስፍራ እንደገና የመኖር ዕድል እንዳላቸው ያምናሉ። በተጨማሪም እነዚህ ሃይማኖቶች የሰው ልጆች ከአምላክ ፍርድ ማምለጥ እንደማይችሉ የሚያስተምሩ ሲሆን፣ በዚህኛው ዓለም ለአምላካቸው በመታዘዝ የኖሩ ሁሉ ደግሞ በሚመጣው ዓለም ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚኖሩ ያስተምራሉ (Van Inwagen, Human Detiny, 246-7)። በዚህ ስፍራ ማወቅ ያለብን እውነት፣ የሚመጣው ሕይወታችን ሁኔታ አሁን ባለን ሕይወት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ነው። ይሁን እንጂ ደግሞ የሚመጣው ሕይወት አሁን ካለው ጋራ ፍጹም ተመሳሳይ ነው ማለት አይደለም። የሚመጣው ሕይወት ፈጽሞ የተለየና የተለወጠ ነው።
ሞት እግዚአብሔር በኀጢአት ላይ ያስተላለፈው ሕጋዊ ፍርድ ነው!
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ገለጻ ከሆነ፣ ሞት ከእግዚአብሔር ፈቃድና ሐሳብ ውጪ የሆነ ነገር አይደለም። በሌላ አነጋገር፣ ሞት ከእግዚአብሔር ፈቃድ በተቃረነ መልኩ ሊፈጸም የሚችል ነገር አይደለም። እንዲህም ደግሞ ሞት ከተፈጥሮ ሂደት ውጪ ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ገለጻ ከሆነ፣ ሞት ማንኛውም የሰው ልጅ የማያመልጠውና የሁሉም ሕዝቦች ዕጣ ፈንታ ነው። ኀጢአት በእግዚአብሔር ላይ ማመፀ እንደመሆኑ መጠን ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለበት። እግዚአብሔር መልካም አምላክና የሁሉም ነገር ምንጭ ነው። ሕይወት እውነተኛውን ትርጉም የሚያገኘው በርሱ ነው። ባለመታዘዝ በእግዚአብሔር ላይ ፊታችንን ማዞር ማለት ከሕይወት ምንጭና ትርጉም ተፋቶ በሞት እጅ መውደቅ ማለት ነው። ኀጢአት በመሠረታዊነት በየትኛውም መልኩ፣ ማለትም በማኅበረ ሰብዊ፣ አካላዊ፣ እና መንፈሳዊ አንድምታዎችና ግንኙነቶች የሚገልጥ የውድቀት ውጤት ነው። ዘፍጥረት 2፥17 እና ሮሜ 6፥23 ስንመለከተ፣ የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ተላልፎ ቢገኝ፣ ሞት እንደሚመጣበት የተወሰነ ሕግ እንደሆነ እናስተውላለን።
በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ግንኙነት መቋረጥ፣ እንዲሁም በአካልና/በሥጋና በነፍስ መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ስናይ፣ በመልካም ነገሮች ሁሉ መካከል ያለው ግንኙነት መበላሸቱን እናስተውላለን። ይህም በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ የማመፀ ውጤት ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ገለጻ ከሆነ፣ የሰው ልጆች የሕይወት ቀውስ፣ ግልጽም ሆነ ምስጢራዊና አሰቃቂው ሞት ዋናው ሰበብ፣ የሰው ልጅን ዐመፅና ውድቀት ተከትሎ የመጣው የእግዚአብሔር ፍርድ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል። ሞት እግዚአብሔር ኀጢአት ላይ ያስተላለፈው ተገቢና ሕጋዊ ፍርድ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባናል። ሞት ኀጢአተኛ የሰው ልጆች ሁሉ ላይ ያለ ምንም ልዩነት የተላለፈና ማንም ሰው ሊያመልጠው የማይችለው አስደጋጭና አስፈሪ ቅጣትና ፍርድ ነው። ከሰው ልጆች ክፉ ድርጊት የተነሣ ዘርፈ ብዙ አስቀያሚ ውጤቶችንና ቅጣቶችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ሰው ልጆች ይዞ የተገለጠው የጥፋት ኀይል ቢኖር ሞት ነው።
በአንድ መልኩ ሲታይ፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ሞት የሰውን ልጆች ክፋትና ዐመፀ ጥግ የሚያሳይ ሲሆን፣ በሌላ ጎኑ ሲታይ ደግሞ የክርስቶስ መስቀል የሚያሳየው በሰዎች ኀጢአትና ዐመፅ ላይ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፍትሓዊ ፍርድ ነው። በመሆኑም ከሁለቱም አቅጣጫ ሲታይ፣ የክርስቶስ ሞት በእግዚአብሔር ቀዳማዊ ዓላማና ውጥን አማካይነት የተፈጸመ ነገር ነው። ከሐዋርያት ሥራ 4፥28 የምንረዳው የክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀል ሞት በእግዚአብሔር ቀድሞ የታሰበና የታቀደ መሆኑን ነው። በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምኑትን ሰዎች ኀጢአት ከማስወገድ ጋራ በተያያዘ የክርስቶስ ሞት ከዘላለም በእግዚአብሔር የተወሰነ ነው። የክርስቶስ ለኀጢአተኞች መሞት ከዘላለም በእግዚአብሔር ዕውቀት ተደግፎ የታሰባ የተወሰነ ስለመሆኑ ሐዋርያት ሥራ 2፥24 ይገልጽልናል።
የክርስቶስ ትንሣኤ ቀድሞ በግልጽ የተተነበየ ነበር
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዐመፀኞች እጅ ታልፎ እንደሚሰጥ፣ እንደሚሞትና በሦስተኛውም ቀን ከሙታን እንደሚነሣ በተለያዩ መንገዶች አስቀድሞ የተተነበየ ነበር (ማቴ. 12፥39–40፤ 16፥21፤ 17፥9፡22–23፤ 20፥19፤ 26፥32፤ ዮሐ. 2፥19፤ 10፥17–18)። እነዚህ የአዲስ ኪዳን የሕማማቱ የትንቢት ቃላት የተነገሩት ሐዋርያው ጴጥሮስ ማርቆስ 8፥31 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ መሲሕ መሆኑን ካወጀ በኋላ ሲሆን፣ ከዚህ እውነት ጋራ ተመሳሳይ ነገር በመገለጥ ተራራ ላይ የኢየሱስ መልክ ሙሉ ለሙሉ በተለወጠበት ወቅት በድጋሚ ተነግሮ ነበር (ማርቆስ 9፥9)። እነዚህ ምንባባት በሙሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚገረፍ፣ እንደሚሠቃይ፣ ታልፎ እንደሚሰጥና እንደሚሞት አስቀድመው ተናግረዋል (ማር. 9፥31፤ 10፥34)። በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚሞትና እንደሚነሣ ያውቅ ነበር። እንደ ዕብራውያን 12፥2 ገለጻ ከሆነ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ሞት በእግዚአብሔር ዕውቀትና ዕቅድ የተፈጸመ ነገር በመሆኑ ምክንያት ነው በደስታ የተቀበለው። ይህ እውነት መረዳቱ ነበር ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከባዱንና አስጨናቂውን የመስቀል መከራ እንዲታፈሥ ያስቻለው። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቱ በእግዚአብሔር ሙሉ ለሙሉ መደገፉንና ፈቃዱን ለመፈጸም መታዘዙን ያሳያል (ሉቃ. 22፥42)።
የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የሞቱን ትርጉምና ውጤቱን ይገልጻል
አንዳንድ ጉዳዮችን በጥልቀት ከማየታችን በፊት ክርስቶስ ኢየሱስ ለምን እንደሞተና እንደተነሣ እንዲሁም፣ የትንሣኤው ብርሃን የፈነጠቁ ብርሃናትን መመልከት ይጠቅማል። ይህም የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ትርጉምና ከዚያ የተገኙ ትሩፋቶች ምን እንደሆኑ ለማብራራት እንዲያስችለን ነው።
1. ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ትንሣኤው የተናገራቸው ትንቢቶችና፣ በሕማማቱ ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ ያሳሳባቸው ጥብቅ ጉዳዮች ከሞቱ ጋራ የተያያዙ ሲሆኑ፣ ሞቱ ደግሞ በመሥዋዕታዊ ሞቱና ከኀጢአት ቤዝዎት ጋራ የተቆራኘ ነው። ከሁሉ በላይ የክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞትና ትንሣኤው በእግዚአብሔር ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት ያለው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በብዙ ሥቃይና በመከራ እንደሞተ ሁሉ ጠቅላላዎቹ የሰው ልጆች ይሞታሉ። ይሁን እንጂ ደግሞ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የሰው ልጆች ሞት ትርጉም ያለው እንዲሆን አስችሎታል። የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የእውነተኛ ሰው ሞት እንጂ ምትሓታዊ ክሥተት አይደለም። የርሱ ሞትና ትንሣኤ ስለርሱ የተተነበዩ ነገሮች በሙሉ ያለ ምንም መፋለስ ተፈጻሚነት ማግኘታቸውን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ኀጢአተኞችን ለመዋጀት የተደረገ ቤዝዎታዊ ሞት ሲሆን፣ ዋና ዓላማው ኀጢአተኛውን የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋራ እና ርስ በርሳቸው ማስታረቅ ነው። በመሆኑም የርሱ ሞት ከሌሎች የሰው ልጆች ሞት ፈጽሞ የተለየ ነው። ከርሱ ሞትና ትንሣኤ በበደላችንና በኀጢአታችን ጠላቶቹ ከነበርንበት ሕይወት ወጥተን፣ በርሱ የተወደድን ልጆች እንድንሄድ ያስችለናል። ይህም እውነት ደግሞ ልጆች ከመሆን ዐልፈን በርሱ የምንደገፍና ርሱንና የርሱ የሆኑ ወዳጆቻችንን በሙሉ እንድንወድ ያስችለናል። ይህን እውነት ዎርፊልድ የተሰኘ ጸሐፊ፣ “የኢየሱስ ክርስቶስ ሞቱና እኛን የማዳሁ ምስጢር እጅግ አስደናቂ በሆነው በትንሣኤው ላይ የተመሠረተ ነው” በማለት ውብ አድርጎ ገልጾታል። በመሆኑም፣ በክርስቶስ ሞትን አትንሣኤ የሚያምኑ ሁሉ ድነትና የዘላለም ሕይወት አላቸው። ስለዚህም የክርስቶስ ትንሣኤ በርሱ ያመኑ ሁሉ ከርሱ ጋራ እንደሚነሡ ርግጠኛ የሚሆኑበት ምስጢር ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ራሱ ሞትና ትንሣኤ ያስተማራቸው ትንቢቶች በርሱ ሞትና ትንሣኤ አማካይነት ርግጠኛ ከሆኑ፣ በርሱ ላመኑ ሁሉ የተሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ርግጠኛ መሆኖ አይቀሬ ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ እውነተኛና ርግጠኛ ክሥተት ከሆነ፣ በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጆች በሙሉ ከሙታን እንደሚነሡ ርግጥ ነው። ከዚያ ትንሣኤ በኋላ አንዳንዶች ለዘላለም ፍርድ፣ ሌሎች ደግሞ ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚሄዱ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጥልናል። ይህ እውነት ይሆናል ተብሎ የሚታመን ብቻ ሳይሆን፣ ፈጽሞ የማይቀር ርግጠኛ እውነታ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ትንሣኤ በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ የተፈጸመ ክሥተት ነው። በመሆኑም በእኛና በሌሎችም ላይ በርግጠኝነት ይፈጸማል። የሙታን ትንሣኤን በዚህ መልኩ ስንገነዘበው፣ “ትንሣኤ ሊሆን ይችል ይሆናል” ብለን በሐሳብ ደረጃ የምንቀበለው እውነት ሳይሆን፣ ከዘላለም በፊት በእግዚአብሔር የተወሰነና በመጨረሻው ዘመን በርግጠኝነት እውን የሚሆን ክሥተ መሆኑን ርግጠኛ ሆነን ወደማመን እንመጣለን። በተጨማሪም የክርስቶስ ትንሣኤና የእኛ ትንሣኤ ርስ በርሱ የተሳሰረና የማይነጣጠል ነው። በመሆኑም የክርስቶስ ትንሣኤ የሙታን ሁሉ ትንሣኤ በግልጽ የሚያስተዋውቅና አይቀሬነቱን የሚያስረግጥ ነው።
[1] Peter van Inwagen, ‘Human Destiny,’ in William E. Mann ed., The Blackwell Guide to the Philosophy of Religion (Blackwell, 2005), 245.
ምዕራፍ 3
የክርስቶስ ትንሣኤ ቀዳማዊ አስፈላጊነት
የቀዳሚ አስፈላጊነት ጉዳይ
ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ሲታይ፣ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ያለን የከበረ እይታ የተገነነ እንደሆነ የሚታሰብ አይደለም። እንዲሁም ደግሞ የክርስቶስ ትንሣኤ የክርስትና እምነት ብቸኛው መገለጫ ተደርጎ ሊታይ አይገባም። ይሁን እንጂ ደግሞ ከሁሉ በላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ጌትነትና ኀይሉ የተገለጠው በትንሣኤው ነው። በዚህም ምክንያት ነው ዎርፊልድ፣ “ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ሊነገሩ ከተገባቸው ነገሮች ዋናውና ማእከላዊው ጉዳይ ርሱ ከሙታን መነሣቱን የሚያወሳው ዜና መሆን አለበት” ያለው (ዎርፊልድ፣ 536)። ይህ እውነት የሚያሳየው፣ ሐዋርያት ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ያስተማሩት ትምህርት በሙሉ በትክክል በተግባር የተፈጸመ ክሥተት መሆኑን ነው። “ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ሞቶ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ” ከሚለው የሐዋርያት ትምህርት ጎን ለጎን፣ ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ መታየቱን የሚያወሳው እውነት (1ቆሮ. 15፥1_8) ሌላኛው የክርቶስ ኢየሱስ ትንሣኤ እውንነት የሚያስረግጥ ቁልፍ ሐሳብ ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ አንደበታዊ አዋጅ ብቻ ሳይሆን በዐይን ምስክሮች በተግባር የተረጋገጠ ተግባር ነው። ስለ ትንሣኤ ኢየሱስ መመስከር ለክርስቶስ ተከታዮች የርሱ ደቀ መዝሙር የመሆናቸው እውነት መገለጫ ብቻ ሳይሆን፣ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል የመሞላትና ለወንጌል ዐዋጅ ነጋሪነት የመታጠቅ ምልክትም ጭምር ነው (ሐዋ. 1፥22፤ 2፥32፤ 4፥33፤ 10፥41፤ 17፥18)። ይህ እውነት የክርስቶስን ወንጌል በሚገባ ዐውቆ ለሌሎች ለማስተላለፍ እጅግ ወሳኝ ነው (ሮሜ 1፥1_4፤ 1ቆሮ. 15፥1፡12፡14_15፤ 2ጢሞ. 2፥8)።
የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የማይነጣጠሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶች፣ እንዲሁም የወንጌል መሠረትና ማእከል ቢሆኑም፣ ትንሣኤው ግን ቁልፍ ክሥተት ነው። ምክንያቱ ደግሞ ክርስቶስ በሕይወቱን በሞቱ የሠራቸው ነገሮች በሙሉ ግልጽ በሆነ መልኩ የሚታዪቱና በአማኞች ሕይወት ላይ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉት በክርስቶስ የትንሣኤ አካል አማይነት ስለሆነ ነው። በመሆኑም፣ ትንሣኤ የሁሉም ነገር መሠረትና ማእከል ሲሆን፣ የክርስትና እምነት የመሠረት ድንጋይም ጭምር ነው።
ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አዲስ ኪዳን የሚታሰበ ነገር አይደለም፤ በተጨማሪም ትንሣኤ ባይኖር ክርስትና ትርጉም የለሽና ተስፋ ቢስ ሃይማኖት ሆኖ በተቀረ ነበር። የክርስትና እምነት እውነትነትም ሆነ ሐሰትነት የሚረጋገጠው በክርስቶስ ትንሣኤ እውነትነትና ሐሰትነት ላይ ነው (1ቆሮ. 15፥14_18)። ስለዚህም የክርስቶስን ትንሣኤ እውነተኝነት ከሚያስረግጡ ነገሮች አንዱና ዋናው የርሱን ትንሣኤ በዐይን የተመለከቱ ደቀ መዛሙርት ምስክርነት ነው። ይህም እውነት የክርቶስን ትንሣኤ ነገረ መለኮት ትክክለኛነት ብቻ ሳይሆን፣ የክሥተቱን ታሪካዊነትን ጭምር የሚያጸና ነው።
በመሆኑም፣ የክርስቶስ ትንሣኤ ከየትኛም ታሪካዊ ክሥተት በላይ የክርስትና እምነት መሠረትና ማእከል ነው። ይክ ክሥተት በየትኛውም መልኩ ለድርድር ሊቀርብ የማይችል ልዩ አምላካዊ ተአምር ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ ከሰው አእምሮ በላይ የሆነ ተኣምራዊ ክሥተት ሲሆን፣ ከየትኛውም ምድራዊ ክሥተት ጋራ በየትኛውም መንገድ ሊነጻጸር የማይችል ነው።
የታሪካዊ ክሥተትና የልእለ ተፈጥሯዊ ኀይል ጥምረት
1. የክርስቶስን ትንሣኤ ከሁለት ገጽታ አንጻር፣ ማለትም ከታሪካዊ እና ከመለኮታዊ ኀይል ክሥተትነት አንጻር ስናየው ወደር የማይገኝለት እጅግ አስደናቂ ክሥተት ነው። ምንም እንኳን የዓለም ሃይማኖቶች፣ አረማዊ አስተሳሰቦችና አምላክ የለም ባይ ፍልስፍና አራማጆ፣ “ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቷል” የሚለውን እውነት ከመካድም ባሻገር እንደ ቅዥት ቢቆጥሩትም፣ የክርስቶስ ትንሣኤ ግን በታሪካዊ ማስረጃዎች የተደገፈ ክሥተት በመሆኑ ምክንያት በቀላሉ የማይክዱት ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ የማይካድ ታሪካዊ ሀቅ የመሆኑን እውነት ታሪክ ራሱ ይመሰክራል። የክርስቶስ ትንሣኤ ታሪክ በወንጌላት ጸሐፊዎች ምናብ የተፈጠረ ነገር ሳይሆን፣ ጻሐፊዎቹ ታሪኩ በተፈጸመበት ዘመንና ቦታ ሆነው፣ ክሥተቱን በዐይን የተመለከቱ የዐይን ምስክሮች ሲሆን፣ ያዩትን፣ የተመለከቱንና የሰሙትን ነገር አንድ ላይ አጠናቅረው ሊያቀርቡ ችለዋል። ይሁን እንጂ ደግሞ የክርስቶስ ትንሣኤ የተፈጸመው እንደ ማንኛውም ተራ ክሥተት ሆኖ ሳይሆን፣ በቀላሉ ሊገለጽ በማይቻልና ከተፈጥሯዊ መረዳት በላቀ የመለኮት መንገድና አሠረር ነው። ይህ እውነት እንደ እውነተኝነቱ ማግኘት ያለበትና ክርክር የማያሻው የክርስትና እምነት የመሠረት ድንጋይ ነው። በተጨማሪም ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑና ትምህርቶቹም እውነተኛ መሆናቸው የሚጸኑት፣ እንዲሁም የርሱን የትንሣኤ ዜና አንግበው ወደ ዓለም ሁሉ የተላኩ ሰዎች መልእክት እውነተኝነት የሚረጋገጠው በዚህ ነው። ይህ እውነት በክርስቶስ ኢየሱስ ሕይወትና ሥራ የሚያምኑ ሁሉ ሊተማመኑበት የተገባ ጽኑ መሠረት ነው (ዎርፊልድ፣ 543)።
የክርስቶስ ትንሣኤ ለድነት ያለው ፋይዳ
2. የክርስቶስ ትንሣኤ የክርስትናን ትምህርት ከሌሎች ሃይማኖቶች፣ ፍልስፍናዎች፣ ሳይንሳዊ ግኝቶች፣ መንፈሳዊ አስተሳሳቦች ሁሉ በላይ ከፍ አድርጎ የሚያስቀምጥ ክሥተት ነው። በአጭር ቃል ለመግለጽ፣ ከየትኛውም ነገር በላይ የክርስትናን እምነት ከፍ ባለ ስፍራ ላይ የሚያስቀምጠው የእምነቱ ራስ የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ በትንሣኤ አካል ከሙታን መነሣቱ ነው። በመሆኑም የክርስቶስ ትንሣኤ፣ ሕይወቱና ትምህርቱ ተከታዮቹ ወደ ዘላለም ሕይወት መግባት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል (አደን 2፣ 464)። የክርስቶስን ትንሣኤ ልዩና ድንቅ የሚያደረግው ከሰዎች አስተሳሰብ በላይ የሆነ ልእለ ተፈጥሯዊ ክሥተት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በትንሣኤው አማካይነት የተገለጠው ድነትና የዘላለም ሕይወት ነው። የክርስቶስ ኢየሱስን ማንነትና በተመለከተ ይህ እውነት እጅግ አስገራሚ፣ መሠረታዊና ታሪካዊ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ በክርስቶስ ማንነትና ሥር የሚያምኑ ሁሉ ድነትና የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት በዚህ ነው።
የሁሉም ነገር መሠረት የሆነ እውነት
ወደ አዲስ ኪዳን ትምህርት ስንመጣ፣ የክርስቶስ ትንሣኤ የወንጌላት ታሪኮችን በአንድ ላይ የሚያጣምርና ለአዲስ ኪዳን መልእክቶች በሙሉ እውነተኛ ትርጉም የሚሠጥ ክሥተት ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ ርሱን ለማወቅም ሆነ ለሕዝቦች ሁሉ አዳኝነትና ጌትነቱን ለማወጅ መሠረት የሆነ እውነት ነው። የክርስቶስን ትንሣኤ መካድ ወይም ያለመቀበል የአዲስ ኪዳን ትምህርቶችንና የያዟቸውን መልእክቶች በሙሉ ከንቱ ማድረግ ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ ለእምነታችንም ሆነ ለሕይወታችን መሠረታዊና ጠቃሚ ነገር ነው። ርሱ ከሙታን ባይነሣ ኖሮ ሙታን ምንም ተስፋ አይኖራቸውም ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ ክርስቶስ ከሙታን ባይነሣ ኖሮ የክርስትና ትምህርቶች በሙሉ ሐሰት ሆነው በቀሩ፣ የሰው ልጆች በክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋራ እንዲታረቁ የሚደረገው ጥሪም ከንቱ በሆነ ነበር (1ቆሮ. 15፥12–17)። በዚህም ምክንያት ነው ሐዋርያው ጳውሎስ 1ቆሮንቶስ 15፥17 ላይ ስለዚህ እውነት አበክሮ የሚያወሳው። በመሆኑም የክርስቶስ ትንሣኤ በክርስቶስ ደቀ መዛሙት ትምህርት ውስጥ ቁልፍ ስፍራ ይዞ እንመለከታለን (ሐዋ. 1፥22፤ 2፥24–36፤ 3፥13–15፡ 21–26፤ 4፥2፡10–11፤ 5፥30–32፤ 10፥37–40፤ 13፥30–37፤ 17፥18፡30–32፤ 23፥6–10፤ 24፥15፡21፤ 26፥8፡12–18)።
በአጠቃላይ መልኩ ስናየው፣ ለቀደሙት ሐዋርያት የክርስቶስ ትንሣኤ ለትምህርታቸውና ለወንጌል አዋጅ መሠረታዊ እውነት ነው። ይህ እውነት ለአማኞች ትልቅ የደስታ ምንጭ ሲሆን፣ ለኢአማንያን ደግሞ ልባቸውን በማሸነፍ ወደ ወንጌል እውነትና ወደ ክርስቶስ ሕይወት የሚያመጣ ነው።
“ለክርስትና እምነት እጅግ መሠረታዊ እውነት ምንድን ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ፣ ሐዋርያቱ አበክረው የጻፉትና የሰበኩት፣ የሐዋርያቱን ስብከትና ትምህርት የተቀበለው አማኝ ማኅበረ ሰበ የተቀበለውና የኖረው እውነት ነው የሚል ነው። ይህ መሠረታዊ እውነት ደግሞ የክርስቶስ ትንሣኤ ነው (Warfare, Selected Shorter Writings, 1:196)። የክርስቶስ ሐዋርያት የጽሑፎቻቸው፣ የትምህርቶቻቸውና የስብከቶቻቸው ቁልፍና ማእከላዊ እውነት የክርስቶስ ትንሣኤ ነበር። የክርስቶስ ትንሣኤ የርሱ ማንነትና ሥራው ትርጉም ያገኘበት፣ እንዲሁም የክርስትና እምነት የታነጸበት መሠረት ነው። ክርስቶስ ራሱ ስለ ትንሣኤው የተናገራቸው ነገሮች ይህን እውነት ያጸናሉ። ለምሳሌ፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማቴዎስ 12፥39–40 እና ዮሐንስ 2፥18–19 ላይ ምልክቶችን እንዲያሳይ በተጠየቀ ጊዜ፣ ደጋግሞ ያስረገጣቸው እውነት የርሱ ትንሣኤ ስለርሱ ማንነትና ሥራ ብቸኛ ማረጋገጫ ተኣምር እንደሆነ ነበር። በመሆኑም፣ የክርስቶስ ትንሣኤ የክርስትናው እምነት አስተማማኝ የመሠረት ድንጋይ ነው። ይህን እውነት ቴዎዶርት የተሰኘ ጸሐፊ፦
ከመሰቀሉና ከመሞቱ በፊት የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮትን ለደቀ መዛሙርቱም ሆነ ለአይሁዶች በግልጽ አልታወቀም ነበር። ርሱ ልክ እንደማንኛውም ሰው ይበላ፣ ይጠጣ፣ ይተኛና ይጸዳዳ ስለነበር ሰዋዊ ጎኑ ብቻ ነበር የታያቸው። የሚያደርጋቸውን ተኣምራቶች አይተው እንኳን መለኮት መሆኑን ሊያምኑ አልቻሉም። ነገር ግን ከሙታን ከተነሣ በኋላ ርሱ አምላክና የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ተገነዘቡ
በማለት ገልጦታል (1998፡11)።
የክርስቶስ ትንሣኤ ርሱ ማን እንደሆነ፣ ምን እንዳስተማረ፣ ምን እንደሠራና አሁን ምን በማድረግ ላይ እንዳለ የምናውቅበትን መሠረታዊ እውነት የጣለ ክሥተት ነው። ርሱ በማንነቱና በሥራው በዓለም ሁሉ ታሪክ ተወዳዳሪና አቻ አልተገኘለትም።
ትንሣኤ ጌታ ከተነሣበት ቅጽበት ጀምሮ በርሱ ላይ የነበሩ ጥርጣሬዎችን በሙሉ አስወግዶ ርግጠኝነትን ያሰፈነ እጅግ አስደናዊ ክሥተት ነው። በዚህም ምክንያት በክርስቶስ ኢየሱስ ማንነትና ሥራ የተገኙ በረከቶችና ትሩፋቶች በሙሉ በግልጽና የማይነቃነቅ መሠረት ላይ ተመሥርተዋል። በተጨማሪም ትንሣኤው የርሱን ማንነት በተመለከተ ሙሉ ሰውና መለኮት የመሆኑን ያረጋገጠ ነው (ሮሜ 1፥3–4)። እንዲሁም እነዚህ ሁኔታዎችና ክሥተቶች በተጨማሪ የርሱ መወለድ፣ ሕይወቱ፣ ሞቱና የወደፊት ግብራቱን በሙሉ በግልጽ ያሳዩናል። የክርስቶስ ትንሣኤ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት ተለይቶ አይታይም። ቃል ሥጋ ነሥቶ የመጣበት ዓላማ ፍጻሜና ግቡን ያገኘው በትንሣኤው ነው።
እግዚአብሔር ስለ ኢየሱስ የተናገረው ወሳኝ ቃል
የክርስቶስ ትንሣኤ በእግዚአብሔር አብ ምስክርነት ቃል የጸና ክሥተት ነው። ያለ ክርስቶስ ትንሣኤ የክርስትና እምነት መሠረት አልባ ሐሰት ሆኖ በቀረ ነበር። የክርስቶስን ትንሣኤ ከሕይወታችን አጠፋነው ማለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶችን በሙሉ ከሕይወታችን አስወገድን ማለት ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ ከሕይወታችን ሊጠፋ የማይቻልና በምንም ሁኔታ ለድርድር የማይቀርብ የእምነታችንና የትምህርቶቻችን ሁሉ ቀልፍ መሠረት ነው።
የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሣኤ ለክርስትናው እምነት በጣም አስፈላጊና እጅግ ተጽእኖ ፋጣሪ ክሥተት ቢሆንም፣ ከየትኛውም ክሥተት በላይ ደግሞ አከራካሪ ነው። ሁሉም ነገር፣ ማለትም የወንጌላት መልእክቶች፣ እጅግ አስደናቂና መሠረታዊ መለኮታዊ መገለጦች፣ እና ሌልችም ነገሮች በሙሉ በርሱ ትንሣኤ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ለምሳሌ፦ የኀጢአት ይቅርታ፣ ከእግዚአብሔር ጋራ የተፈጸመው ዕርቅና ከዓለም መቤዝት በትንሣኤው የተረጋገጡ ነገሮች ናቸው (1ዮሐ. 2፥2)። ሐዋርያው ጳውሎስ ሮሜ 1፥4 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅ ያደገው ትንሣኤው እንደሆነ ሲያወሳ፣ ይህም ርሱ ስለ እኛ ተሠቃይቶ የሞተበት ሞት ውጤት ነው።
የትንሣኤው ወንጌል
ከጠንካራ ታሪካዊ እይታ አንጻር ስናይ የክርስትና እምነት መሠረት የሆኑ ምንጮች ከክርስቶስ ትንሣኤ ጋራ የተቆራኙ ናቸው። በርግጥ እውነታው ይህ ብቻ አይደለም። በመጀመሪያው ዘመን የክርስትና ትወልድ ዘንድ የክርስቶስ አካላዊ ትንሣኤና የትንሣኤው ታሪካዊ ክሥተት እና በታሪክ መጨረሻ ላይ ሊከናወን ያለው የሙታን በሙሉ ትንሣኤ ዓለም አቀፍ ቅቡልነት ያለው እውነት የሆነው ወዲያው ነበር። በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የአይሁዶች እምነት፣ የሙታን ትንሣኤ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ጉዳይ አልነበረም። በመሆኑም፣ በዘመኑ በነበሩ አይሁዶችም ሆነ አረማውያን ዘንድ ስለ ሙታን ትንሣኤ የተለያዩ አመለካከቶች ይንጸባረቁ ነበር። ይሁን እንጂ ከአይሁድም ሆነ አሕዛብ ክርስቶስን በተከተሉ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ዘንድ የሙታን ትንሣኤ በተመለከተ የአመለካከት ልዩነት አልነበረም። በመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን የነበሩ አማኞች የሙታንን ትንሣኤ ለድርድር የማይቀርብ የእምነት መሠረትና የጀርባ አጥንት አድርገው አምነው ነበር። በመሆኑም በዚያ ዘመን ክርስቲያን መሆን ማለት እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን እንዳስነሣው፣ እንዲሁም በመጨረሻው ዘመን ሙታን በሙሉ እንደሚያስነሣ ማመን ነበር።
በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የምናነባቸው ስብከቶች የሚገልጡት እውነት፣ በአረማውያንና በአይሁዶች የስብከት ስልት መካከል ልዩነት መኖሩንና ያም ልዩነት ወደ ግጭት እንደሚመራ ነው። በአንድ መልኩ ሲታይ፣ ከሳዱቃውያን በስተቀር አይሁዶች በሙሉ የሙታን ትንሣኤ ይቀበላሉ፤ እንዲሁም በመጨረሻው ቀን ፍርድ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ክርስቶስ የተባለው መሲሕ በመስቀለ መሰቀሉንና በሦስተኛው ቀን ከሙታን መነሣቱን አይቀበሉም። በመሆኑም ሐዋርያትና ተባባዎቻቸው በአይሁድ ምኩረቦች ሲሰብኩ የመልእክታቸው ዋና ትኩረት የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነበር (ሐዋ. 2፥23፡36፤ 3፥15፤ 5፥30፤ 7፥52)። በርግጥ ከሐዋርያት ስብከት አይሁዶች በጽኑ የተቃወሙትና ለመቀበል አሸፈረኝ ያሉት ክርስቶስ ከሙታን የመነሣቱን እውነት ሳይሆን፣ “እናንተ በዕንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን፣ የአባቶቻችሁ አምላክ ከሙታን አስነሣው” የሚለውን እውነት ነበር (ሐዋ. 5፥30)። በዚህ ስፍራ በመርሕ ደረጃ የምናየው አይሁዶች የሙታን ትንሣኤ መቀበል እንደቸገራቸው ሳይሆን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ የተደረገውንና የርሱን ትንሣኤ ለመቀበል አሸፈረኝ ማለታቸውን ነው (ሐዋ. 4፥2)። በሌላ ጎኑ ደግሞ አሕዛብ የክርስቶስን ትንሣኤም ሆነ የሙታን መነሣት፣ እንዲሁም የመጨረሻውን ፍርድ ሙሉ ለሙሉ አይቀበሉም። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ በግርኮ–ሮማንስ ዐውድ ሲያስተምር ዋና ትኩረቱ የክርስቶስ ትንሣኤ ለኀጢአት ድነትም ሆነ ለመጨረሻው ዘመን የመለኮት ፍርድ ዋና መሠረት መሆኑን አጥብቆ ይናገር ነበር (ሐዋ. 17፥30–32፤ 23፥6፤ 24፥15፡21፤ 25፥19፤ 26፥6፡8፡22–23)።
ከሁሉ በላይ፣ በሐዋርያት የወንጌል ስብከት ውስጥ ወጥ በሆነ መልኩ የሚቀርበውና እንደ ስብከት ማሳሪያ ሆኖ የሚቀርበው እውነት የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነበር (ሐዋ. 2፥32፤ 13፥30–37)። አንዳንድ ጊዜ፣ ስለ ክርስቶስ መሰቀልና ሞት ባይጠቀስም እንኳን፣ የክርስቶስ ትንሣኤ ዜና ብቻውን የስከታቸው ማእከላዊ ሐሳብ ሆኖ ሲቀርብ ይስተዋላል (ሐዋ. 17፥31–32)። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ያሉ ስብከቶችን ስናጠና፣ ዐብይ ርእሰ ጉዳይ ሆኖ የምናገኘው የክርስቶስን ትንሣኤ ፋይዳ ብቻ ሳይሆን፣ የወንጌልን መልእክት አጠቃሎ የያዘ እውነት የያዘ ክሥተት እንደሆነ ጭምር ነው። በተጨማሪም በመጽሐፉና በሐዋርያት ስብከት ውስጥ የክርስቶስ ትንሣኤ የእምነት አነሳሽ ሰበብ እና በእምነት ለሚገኘው ድነት መሠረታዊ መልእክት ሆኖ ይታያል። ሐዋርያው ጵውሎስ ሮሜ 10፥9 ላይ እንደሚያወሰው ሰው የሚድነው ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ በአፉ በመመስከርና እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልቡ በማመን ነው። በመሆኑም ድነት የሚገኘው በግል ሕይወታችን በክርስቶስ በማመን እና በርሱ የትንሣኤው ኀይል በማመን ነው (ፊልጵ. 3፥19)። የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከሆኑት አንዱ የሆነው ተርቱሊያን እንደ ገለጠው ከሆነ፣ የክርስቶስ ትንሣኤ የአማኞች ዋና መተማመኛቸው ነው። “የሙታን ትንሣኤ” ይላል ተርቱሊያን፣ “የአማኞች መተማመኛ ነው። አማኞች የምንሆነው በዚያ ነው። ሙሉ አማኞች የሚያድርገን ይህን እውነት (የእምነት አንቀጽ) ማመን ነው። እግዚአብሔር የገለጠው፣ ነገር ግን መንጋው ሕዝብ አልቀበል ብሎ የሰቀለው እውነት ይህ ነው። ይህን ያደረጉ ሰዎች ይህ እውነት ሞትን የሚቋቋምና ከሞት በኋላ ሕያው የሚሆን አልመሰላቸውም ነበር።”17
የክርስቶስ ስቅላትና ትንሣኤው
ከኀጢአታችን ድነን ነጻ የወጣነው በክርስቶስ ኢየሱስን ማንነትና ሥራው፣ እንዲሁም የመስቀል ላይ ሞቱ አማካይነት እንደሆነ ሁላችንም ልናውቅ ይገባናል። የኀጢአት ዕዳችንን ርሱ በመስቀል ላይ ከፍሎታል። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተው ለዓለም ሁሉ ኀጢአት ነው (1ዮሐ. 2፥2)።
የእግዚአብሔር ክብር፣ መሥዋዕታዊ ፍቅሩና የማዳን ኀይሉ የተገለጠው በክርስቶስ መስቀል ነው። እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ልዩ ፍቅሩን ይገልጥ ዘንድ ውድ የሆነው ልጁ በእኛ ፋንታ ተሠቃይቶ መሞት ነበረበት። የክርስቶስ ሞት የሚገልጥልን እውነት እግዚአብሔር ራሱን ለሞት ዐሳልፎ እስከመስጠት በሚያስችል ፍቅር እኛን መውደዱን ነው።
ከዚህ እውነት የምንረዳው የክርስቶስ ሞት በእግዚአብሔር ዘንድ ትልቅ ትኩረት የተሰጠውና እጅግ አስፈላጊ ነገር መሆኑን ነው። በመሆኑም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር፣ ርሱም እንደተሰቀለ፣ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበር የሚለው (1ቆሮ. 2፥2)። ይህ የሐዋርያው ጳውሎስ ሐሳብ፣ 1ቆሮንቶስ 15፥3–4 ባለው ክፍል ላይ ከተገለጠውና የክርስቶስን ሞትና በሦስተኛው ቀን ከሙታን መነሣት ከሚያስረግጠው እውነት ተለይቶ መታየት የለበትም። የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሣኤ አስፈላጊነቱና ፋይዳው በ1ቆሮንቶስ 15፥1–58 ባለው ክፍል በሚገባ ተብራርቶ ቀርቧል። በተጨማሪም ጳውሎስ በዚሁ መጽሐፍ መጨረሻ የተሰቀለውን ክርስቶስን ከማወቅ ውጪ የሆነ ሌላው እውነት በሙሉ ፋይዳ ቢስ ስለመሆኑ ገልጧል። ስለዚህም ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ማወቅና ለክሥተቱም ዕውቅና መስጠት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው።
በክርስቶስ ሞትና የቤዝዎት ሥራ ላይ ልዩ ትኩረት መሰጠቱ ትንሣኤውን ፋይዳ የሌለው ክሥተት ሊያደርገው አይገባም። የኀጢአት ይቅርታና ከእግዚአብሔር ጋራ ጤናማ ኅብረት መመሥረት በክርስቶስ ሞት አማካይነት ብቻ ሳይሆን በትንሣኤውም ጭምር የሚረጋገጥ ነው። በእግዚአብሔር ፊት ጽድቅ ወይም ጻድቅ ተደርገን የተቆጠርነው በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞትና በትንሣኤው አማካይነት ነው (ሮሜ 4፥25)። ከድኅነታችን ጋራ በተያያዘ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ሁለቱም በእኩል ደረጃ አስፈላጊና በፍጹም የማይነጣጠሉ ናቸው። የክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀሉ ሥራ በሚታወጅበት ጊዜ፣ የትንሣኤው ክብር በሚያስደንቅ መልኩ ይገለጣል። በተመሳሳይ መልኩም የክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀሉ ቃል ሲታወጅ፣ ትንሣኤውን በማወቅ ላይ የተመሠረተ እውነታ አዋጅ ይታወጃል። በአጭሩ የክርስቶስ ሞት ፍቅሩን ሲገልጥ፣ ትንሣኤው ደግሞ ሕይወቱን ይገልጣል ማለት ይቻላል። እንዲሁም ደግሞ ሞቱ ለሕዝቡ ድኅነትን ሲያመጣ፣ ትንሣኤው ሕይወትን አምጥቷል ማለት ይቻላል (Adapting Brakel’s point about Christ’s exaltation, The Christian’s Reasonable Service, 1:625.)።
ይህን እውነት በተመለከተ የ16ኛው ክፍለ ዘመን የተሐድሶ መሪና የነገረ መለኮት ምሁር የሆነው ጆን ካልቪን፦
ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ሞት በምናስብበት ጊዜ፣ በተመሳሳይ መልኩ ማሳብ ያለብን በሞቱ ስለ ተደረገል ነገር ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ ስለ ትንሣኤው በምናስብበት ጊዜ፣ ሞቱንም ደግሞ አንድ ላይ እያሰብን መሆኑ ልንረዳ ይገባናል። ምክንያቱም የክርስቶስ ትንሣኤ በሞት ላይ ድል የመቀዳጀት ክሥተት ብቻ ሳይሆን ሕይወት የመጎናጸፍ ሽልማትም ጭምር ስለሆነ ነው። ይህን እውነት ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “ክርስቶስ ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ሆኗል” በማለት ይገልጣል (1ቆሮ. 15፥17)። በተመሳሳይ መልኩም፣ “የሞተው፣ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፣ ደግሞም ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው”
በማለት ይገልጻል (ካልቪን፣ የክርስትና መሠረታውያን 2.14.13፣ 521)።
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር፣ እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበር” ሲል፣ የክርስቶስን ትንሣኤ ችላ ማለቱ ወይም ማሳነሡ አይደለም። ይልቁንም ይህ እውነት መሲሑና አዳኙ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሰቀለና የኀጢአታችንን ዕዳ ለመክፈል እንደተቀጣ፣ በዚህም ምክንያት ከኀጢአት እስራት ነጻ የሚያወጣ ጌታ እንደሆነ እንሰብካለን ማለቱ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ከተሰቀለውን ከሙታን ከተነሣው፣ እኛንም ሊያድነን ከሚችለው ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ የለም ወይም ሊኖር አይችልም ማለቱ ነው። በርግጥ ደግሞ የመሲሑ የትንሣኤ የሚያሳየው የርሱን የትንሣኤ ኀይል ብቻ ሳይሆን፣ በመስቀል ሞቱ እንዴት ሊያድነን እንደቻለም ጭምር ነው። የሞቱ ፋይዳ በትንሣኤው ተገልጿል ማለት ይቻላል። የክርስቶስ ትንሣኤ ግልጽ ሆኖ የታየው በርሱ ሥቃይና ሞት መሰበክ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል። ይህ አስደናቂ የትንሣኤና የድነት የምስራች የታወጀው በቁጣና በፍርድ መንገድ ብቻ ነው። ይህም ደግሞ የአሰቃቂው ዐመፀና ኀጢአት ውጤት ለሆነው ሞት በተከፈለው ዋጋና ክርስቶስ በሞት ላይ በተቀዳጀው የትንሣኤ ድል የመጣ ነው።
ምዕራፍ 4
የትንሣኤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንበያና ታሪካዊ ዳራ
የክርስቶስ ትንሣኤ ቀድሞ የተተነበየ፣ የተጠቆመና አስፈላጊነቱ የተነገረ ክሥተት ነው
በሉቃስ 24፥26-27 ባለው ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በርሱ ላይ ሊደርስ ስላለው መከራና ሥቃይ፣ እንዲሁም ከዚያ በኋላ ሊሆን ስላለው ክብር ተግባራዊነትና አስፈላጊነት በሙሴ፣ በነቢያትና በመጻሕፍት ሁሉ አስቀድሞ ስለመነገሩ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ተናግሮ ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ በጴንጠ ቆስጤ ዕለት በነበረው ስብከቱ በሐዋርያት ሥራ 2፥31 ላይ፣ በንጉሥ ዳዊት የተነገረው ትንቢታዊ ቃላት የክርስቶስን ትንሣኤ የሚያወሱ እንደነበር በግልጽ ዐውጆ ነበር። ዘማሪው በመዝሙረ ዳዊት 16፥10 ላይ፣ “ነፍሴን በሲዖል አትተዋትምና ቅዱስህም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም” በማለት የተናገረውን ቃል ሐዋርያው ጴጥሮስ ለክርስቶስ ትንሣኤ እንደተነገረ ትንቢት በቀጥታ ወስዶ ተግባራዊ አድርጓል። ጴጥሮስ የክርስቶስ ትንሣኤ የዐይን ምስክር መሆኑን በሚያጸና መልኩ፣ “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስንሣው፣ ለዚህም እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን” ይላል (ሐዋ. 2፥32)። ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ቆሮንቶስ 15፥4 ላይ ስለ ኢየሱስ ሲያወሳ፣ “ስለ ኀጢአታችን ከሞተ በኋላ መጽሐፍ እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ” ይላል። ሐዋርያት ሥራ 13፥32 እና 33 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ በአንጾኪያ በነበረው ስብከቱ፣ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ በብሉይ ኪዳን አባቶች ተስፋ የተሰጡ ሦስት መሲሓዊ ትንቢቶች ስለመፈጸማቸው በግልጽ ተናግሮ ነበር (መዝ. 2፥7 በሐዋ. 13፥33 ላይ ሲገለጽ፤ ኢሳ. 55፥3 በሐዋ. 13፥34 ላይ ተገልጿል፤ እንዲሁም መዝ. 16፥10 በሐዋ. 13፥35 ላይ ተገልጿል)። በሌላ ቋንቋ፣ ምናልባትም እነዚህ ምንባባት ተቀባይነት ያጡና ተሰሚነት ያላገኙ ቢመስሉም፣ በኢየሱስ ክርስቶስና በሐዋርያ ትምርቶች ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንደነበራቸው፣ እንዲሁም ትምህርታቸው ደግሞ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን መሠረት ያደረጉ ስለመሆናቸው አመልካች ናቸው። በእነዚህ የብሉይ ኪዳን ምንባባት ውስጥ፣ በአጠቃላይ በሚያስቢል መልኩ የመሲሑ ሞትና ትንሣኤ በግልጽ ተተንብዮ ይገኛል።
ከሞትና ከመቃብር በኋላ ያለው የሕይወት ብልጭታ
ከመቃብር ወዲያ ስላለው ስላለው ሕይወት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በልዩ ልዩ መንገዶች ገልጸዋል፤ ወይም ጠቁመዋል። የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በአንድ መልኩ ወደ ዐፈርነት መቀየር ሟች የሆኑ የሰው ልጆች መጨረሻቸው እንደሆነ ይገልጻሉ (ዘፍ. 3፥19፤ መዝ. 90፥3)። በሌላ ጎኑ ደግሞ እነዚሁ መጻሕፍት የሰው ልጆች በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ስለመፈጠራቸው ያወሳሉ። ይህም የሰው ልጅ በምድር ላይ የእግዚአብሔር መልክ አንጸባራቂና ልዩ ተወካይ መሆኑን ይገልጻል።
ሞት ተፈጥሯዊ ያልሆነ ነገር ቢሆንም፣ የእግዚአብሔርን ዓላማ ሊያደናፈው አይችልም
ሞት ተፈጥሯዊ ነገር አለመሆኑ ሲታሰብ፣ በድቅድቅ ጨለማ የተዋጠውና በዐመፀኛ ሙታን የተሞላው ሲዖል ጉዳይ መንሣቱ አይቀሬ ነው። ሲዖል የሕይወት ሥርዐት የሌለበት፣ በተስፋ መቁረጥ፣ መርሳትና በጨለማ የተዋጠ ስፍራ ነው። በተጨማሪም የክፉ መናፍስት መኖሪያና ከሰብአዊ ፍጥረት ጋራ ጤናማ ኅብረት ማድረግ የማይቻልበት ስፍራ ነው (ዘፍ. 37፥35፤ ኢዮብ 7፥9፤ 10፥20-22፤ መዝ. 6፥5፤ 88፥10፤ ዕብ. 2፥5)። ከአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት እንደምንረዳው ከሆነ ሲዖል ከእግዚአብሔር መገኘ ውጪ ነው። ለምሳሌ ዘማሪው፣ “በሞት የሚያስብህ የለምና፤ በሲዖል የሚያመሰኝህ ማነው?” ይላል (መዝ. 6፥5)። በተመሳሳይ መልኩም ነቢዩ ኢሳይያስ፣ “እኔ በሕይወት ዘመኔ መካከል ወደ ሲዖል በሮች እገባለሁ፤ የቀረው ዘመኔ ጎደለብኝ አልሁ” (ኢሳ. 38፥10) በማለይ የሲዖልን አስከፊ ገጽታ ይገልጣል። ይሁን እንጂ ደግሞ ጉዳዩን በስፋትና በጥልቀት ስንመረምረው እግዚአብሔር በሲዖል ውስጥም እንደሚገኝና ሲዖል የርሱን ጥልቅ ፈቃድና ዓላማ ሊያደንቅፈው ከቶ እንደማይችል እንገነዘባለን (ኢዮብ 14፥13፤ መዝ. 139፥8፤ አሞ. 9፥2)።
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አደናጋሪና ግራ የሚያጋቡ የሚመስሉ ጥያቄዎችን የሚያነሡ ይመስላሉ። ለምሳሌ፦ መጽሐፍ ኢዮብ፣ “ሰው ይሞትና ይጋደማል፤ ሰውም ነፍሱን ይሰጣል፤ እርሱስ ወዴት አለ?” ይላል (14፥10)። በተጨማሪም፣ “በውኑ ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን?” ይላል (14፥14)። እነዚህ ምንባባት ሰው ከሞት በኋላ ተስፋ የሌለውና ሞት የመጨረሻ ዕጣ ፋንታው እንደሆነ የሚናገሩ ይመስላሉ። ይሁን እንጂ ሞት የሰው ልጅ የመጨረሻ ዕጣ ፋንታ መምሰሉ፣ እንዲሁም የሲዖል ጉዳይ ጥልቅ ምስጢርና ለመቀበል አስቸጋሪ የሆነ ቋጠሮ ነው። ይሁን እንጂ ምንም እንኳን ሲዖል አስፈሪ ነገር ቢመስልም ተስፋ ከሰጠው ከእግዚአብሔር ኀይል በላይ አይደለም። ተስፋ የሰጠው እግዚአብሔር ሕዝቡን በጨለማ መቃብር ውስጥ የማይረሳና ከመቃብር በታች በጨለማ የተዘጉትን እንደገና የሚያስብ አምላክ ነው (ኢዮብ 14፥12-13)። ኢዮብ ንግግሩን ከላይ በተገለጸው ጽልመተኛ ሐሳብ ላይ አያቆምም። ይልቁን፣ “መለወጤ እስከሚመጣ ድረስ የሰልፌን ዘመን ሁሉ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር” በማለት እግዚአብሔርን በተሐድሶ ተስፋ እንደሚጠባበቅ ይናገራል (14፥14)።
ከሞት በተቃራኒ ያለው የእግዚአብሔር መገኘት፣ ኀይሉና ዓላማዎቹ
ሞት ተስፋ አስቆራጭ የመጨረሻው የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታና ጨለማ ይምሰል እንጂ፣ ሞት እያለ እንኳን ተጨባጭ የእግዚአብሔር አብሮነት ከሰው ልጆች ጋራ እንዳለ ግልጽ ነው። በመሆኑም ከጨለማውና ከተስፋ መቁረጡ ባሻገር በእግዚአብሔር መገኘትና በኀይሉ ተማምነን ተስፋ ልናደርግ ይገባናል (መዝ. 23፥4፤ 39፥4-7፤ 49፥13-15፤ 73፥24፤ 139፥7-8)። ከመጀመሪያው ጀምሮ ያሉትን ታሪኮች ስንመለከት፣ መጽሐፍ ቅዱስ የአብርሃምን፣ የእስማኤልን፣ የይስሐቅን፣ የያዕቆብና የኢዮብን ወዘተርፈ ሞት ወደ ቅዱሳን አባቶቻቸው እንደመሰብሰብና መከማቸት አድርጎ ይቆጥራል (ዘፍ. 25፥8፡17፤ 35፥29፤ 49፥29፡33)። የሐና መዝሙርን ስናነብ እግዚአብሔር በሞትና በሕይወት ላይ ሥልጣን እንዳለው፣ ሐናም በዚህ አምላክ እንደምትተማመን እናነባለን። ይህን እምነቷንም፣ “እግዚአብሔር ይገድላል፣ ያድናልም፤ ወደ ሲዖል ያወርዳል፣ ያወጣልም” በማለት ተገልጣለች (1ሳሙ. 2፥6)።
በዚህ ስፍራ ላይ የሁለት ሰዎችን፣ ማለትም የሄኖክና የኤልያስን ታሪክ ማስታወስ ይጠቅመናል። እነዚህ ሁለቱ ሰዎች በእግዚአብሔር ፍላጎት፣ ለርሱ ዓላማ ሞትን ሳይቀምሱ ከምድራዊ ሕይወት ወደ እግዚአብሔር ዘላለማዊ መገኘ የተወሰዱ ስለመሆኑ ተገልጧል (ዘፍ. 5፥24፤ 2ነገ. 2፥11)። እነዚህ ሰዎች ሞትን ሳያዩ መወሰዳቸው በምን ምክንያት እንደሆነ አልተገለጸም። ነገር ግን ዕብራውያን 11፥5 መሠረት የእነዚህ ሰዎች በእግዚአብሔር ፈቃድ ሞትን ሳያዩ ወደርሱ መገኛ መወሰድ ወደ ዘላለም ሕይወት መግባት አድርጎ ማሰብ ይቻላል።
በተጨማሪም 1ነገሥት 17፥17-22፤ 2ነገሥት 4፥18-37 እና 13፥20-21 ላይ ሦስት ዐይነት ሰዎችን እናያለን። እነዚህ ሦስት ሰዎች የባልቴቲቱ ሴት ልጅ፣ የሱናማይቷ ልጅ እና በኤልሳዕ መቃብር ላይ ተጥሎ ከሞት የተነሣው ሞዓባዊው ሰው ናቸው። እነዚህ ሰዎች እንደ ሄኖክና ኤልያስ ሞትን ሳያዩ ወደ እግዚአብሔር መገኛ የተወሰዱ ሳይሆኑ፣ ከሞት የተነሡ ናቸው። የእነዚህ ሰዎች ታሪክ ከሙታን ትንሣኤ ጋራ ተመሳሳይና ስለ ትንሣኤ የሚያወሱ ናቸው። የእነዚህ ሰዎች ታሪክ እግዚአብሔር በሞትና በሕይወት ላይ ሥልጣን እንዳለው የሚያወሱ ናቸው። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳችን ከኤልያስና ለኤልሳዕ ታሪክ በተጨማሪ ሙታንን የማስነሣት፣ ለምጻሞችን የመፈወስ፣ መልካም የምስራችን የመስበክ፣ ድኾችን የመመገብ እና የመሳሳሉ ተግባራት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተከናወኑ ይዘግባል። እነዚህ ነገሮች በሙሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ 11፤5 ላይ የተጠቀሱ ተአምራቶችንና አገልግሎቱን እንድናስታውስ መንገድ ይጠርጉልናል። በኤልያስና በኤልሳዕ የተደረጉ ሙታንን የማስነሣት ሥራ በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጆች ሁሉ ዕጣ ፈንታ የሙታን ትንሣኤ ስለመሆኑ አመልካች ነው (ብሩስ ዋልኬ፣ 2007፡967)። አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ዐይነት የብሉይ ኪዳን የትንሣኤ ምንባባትን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ጋራ አስተያይተው ይረዳሉ። እነዚህ ሰዎች በብሉይ ኪዳን ሞትን ድል የነሡ እንደ ይስሐቅ፣ ዮሴፍና ሳምሶን (መሳ. 16)፣ እንዲሁም ዳንኤልና ጓደኞቹ (ዳን. 3 እና 6) የመሳሰሉ ናቸው። በተጨማሪም የብሉይ ኪዳን የመሥዋዕት ሥርዐቶች ማለትም የፍየሎች (ዘሌ. 16) እና የወፎች (ዘሌ. 14፥4-7)፣ እና የመሥዋዕት ዕቃዎች (ዘኀ. 17) በሞት ውስጥ ስለሚገለጠው የሕይወት ምሳሌነት ማብራሪያ የሚሰጡ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወት ከሞት በማምለጥ ሳይሆን በሞት በኩል የሚመጣ ስለመሆኑ አስረግጦ ይነግረናል።
ከእግዚአብሔር ጋራ የማይቋረጥ ኀብረት
ከወድቀት፣ ከብዙ መከራና ከሞት በኋላ ታላቅና አስደናቂ ድል እንዳለ ከብሉይ ኪዳን ምንባባት ጭምር እንረዳለን (መዝ. 22)። “ከሞት በኋላ ሕይወት አለ” የሚለው ትምህርት በእግዚአብሔር ፈጣሪነት፣ ታዳጊነትና አዳኝነት ላይ የተመሠረተ እውነት ሲሆን፣ ይህ የእግዚአብሔር ታማኝነት ደግሞ ለእስራኤል ሕዝብ ብቻ የተገለጠ ሳይሆን፣ ርሱ ለፈጠራቸው ፍጥረታት በሙሉ የተስፋ ኪዳን ነው። በሌላ ቋንቋ፣ እግዚአብሔር ፍጥረታትን በመፍጠሩም ሆነ፣ የኪዳኑን ሓብ በክርስቶስ ኢየሱስ እንደገና በመፍጠሩ ታማኝነቱን ገልጧል ማለት ይቻላል። በተጨማሪም በመለኮታዊም ሆነ ሰብኣዊ ማንነት መካከል ያለው ግንኙነት በሞት ምክንያት የሚቋረጥ አይደለም። ይህም የእግዚአብሔር ታማኝነት መገለጫ ነው። ከጅማሬው የፈጠረንም ሆነ፣ ከሞት ያዳነን ርሱ ራሱ ነውና። በዘመናቸው ሁሉ ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር የሰጡና ርሱን በታማኝነት በማገልገል የኖሩ ሁሉ ወደ ተትረፈረፈ የዘላለም ሕይወት ይገባሉ (መዝ. 139፥7-12፡14)። እግዚአብሔር በመፍጠርና በቃል ኪዳን የገለጠው የቃል ኪዳን እውነት ከራሱ የፍቅርና የታማኝነት ኀይል የመነጨ በመሆኑ፣ በእነዚህ እውነቶች የተገለጠውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ሞትን ጨምሮ ሁሉም ዐይነት ተገዳዳሪ ኀይላት በመገርሰስ ውጥኑ ከግብ እንዲደር ያደርጋል (ኤን. ቲ. ራይት 2003፡127)። እግዚአብሔር ራሱን ከሕዝቡ ጋራ በአንድ የቃል ኪዳን ውል ውስጥ ማስተሳሰሩ ግልጽ ነው። በመሆኑም፣ ሕዝቡ በሚያልፍበት የሕይወት ውጣውረድ በሙሉ፣ በሕይወታቸውም ሆነ በሞታቸው እነርሱ ለራሳቸው ከሚያስቡት በላይ፣ የቃል ኪዳን አምላክ የሆነው ርሱ በታማኝነቱ አብዝቶ ያስብላቸዋል፤ ይደግፋቸዋልም። እግዚአብሔር ሰዎችን ከሲኦል ለማዳንና አካላዊ ትንሣኤ ለመስጠት የወጠነውን ውጥንና ተስፋ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው፣ ርሱ ሕዝቡን ከምርኮ ምድር በመመለስ የተሐድሶ ለማምጣት የወጠነበትን የቃል ኪዳን ታማኝነት ስንመለከት ነው። በርግጥ ይህ እውነት ለሰው ልጆች ትልቅ ትርጉም ሊኖረው የተገባ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን አንዳንዶች ወደ ዘላለም ሕይወት ሲገቡ፣ ሌሎች ደግሞ ወደ ዘላለም ፍርድ እንደሚሄዱ ይነግረናል (ዳን. 12፥2፤ በተጨማሪም ኢዮብ 19፥25-27፤ መዝ. 16፥19-11፤ 49፥15፤ ኢሳ. 25፥6-8፤ 26፥14፡18-19፤ ሕዝ. 37፥1-14፤ ሆሴ. 6፥1-2 ይመለከቱ)።
የመጨረሻው ድነት፦ ብሔራዊ ተሐድሶና የእያንዳንዱ ሰው ትንሣኤ
ሐዋርያው ጳውሎስ 1ቆሮንቶስ 15፥54_55 ባለው ክፍል፣ የሙታን ትንሣኤ ርግጠኝነትን ለማጽናት ሁለት ቁልፍ ምንባባትን ከሆሴዕና ከኢሳይያስ ይጠቅሳል። ከሆሴዕ የተጠቀሰው ምንባብ፣ መቃብር ኀይል እታደጋቸዋለሁ፤ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፤ መቅሠፍትህ የት አለ? መቃብር ሆይ፤ ማጥፋትህ የት አለ?” የሚል ሲሆን (13፥14)፣ ከኢይሳይያስ የተጠቀሰው ምንባብ ደግሞ፣ “ሞትን ለዘላለም ይውጣል” የሚል ነው (25፥8)። በዚህ ሂዳት ሐዋርያው በታሪክ ሞት ህልውናው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያከትምና ትንሣኤ እንደሚሆን ይገልጣል። እነዚህ ከሆሴዕና ከኢሳያስ የተጠቀሱ ምንባባት ከምርኮ በኋላ ሊሆን ስላለው የእስራኤል ብሔራዊ ተሐድሶ የሚያወሱ ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህን ምንባባት ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ጋራ አያይዘን ስናነባቸው፣ የእስራኤልን ሕዝብ ከምርኮ መመለስና ብሔራዊ ተሐድሶ በተጨማሪ ለጠቅላላው የሰው ልጆች የትንሣኤ ተስፋ ያዘለ እውነት እናገኛለን (ኢሳ. 26፥19፤ ሕዝ. 37፥11)። በተጨማሪም ኢሳይያስ፣ “ነገር ግን ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፤ በድናቸውም ይነሣል። እናንት በዐፈር ውስጥ የምትኖሩ፣ ተነሡ፤ በደስታም ዘምሩ። ጠልህ እንደ ንጋት ጠል ነው፤ ምድር ሙታንን ትወልዳለች” ይላል (26፥19)። እነዚህ ምንባባት የሚገልጡት የሙታን ትንሣኤ የሰው ልጆች በሙሉ የመጨረሻው ዕጣ ፈንታ እንደሆነ ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ በተለይም ብሉይ ኪዳን የሚገልጥልን እውነት ከሙታን ትንሣኤ በኋላ እግዚአብሔርን የሚፈሩት ወደ ዘላለም ሕይወት፣ ዐመፀኞችና ኀጢአተኞች ደግሞ ወደ ዘላለም ሞት እንደሚሄዱ ነው።
ለዚህ እውነት ግልጽ ማስረጃ የምናገኘው ከትንቢተ ዳንኤል ነው። ዳንኤል፦
በዚያን ዘመን ስለ ሕዝብህ የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል። መንግሥታት ከተመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የመከራ ጊዜ ይሆናል። ነገር ግን በዚያን ጊዜ ስማቸው በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ ይድናሉ። በምድር ዐፈር ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነቃሉ፤ አንዳንዶቹ ለዘላለም ሕይወት፣ ሌሎቹም ለውርደትና ለዘላለም ጕስቍልና ይነሣሉ። ጥበበኞች እንደ ሰማይ ጸዳል፣ ብዙዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ
ይላል (12፥1-3)።
በተጨማሪም ዘማሪው በተለያዩ ምንባባት ውስጥ እግዚአብሔር በመጨረሻው ዘመን የቃል ኪዳን ሕዝቡን ከሞት እንደሚያድንና እንደሚታደግ ይናገራል (19፥14፤ 25፥22፤ 31፥5፤ 34፥22፤ 103፥4)። እንዲሁም ደግሞ ኢዮብ ከሞት በኋላ ስላለው ትንሣኤና ሕይወት፣ የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፣ በመጨረሻም በምድር ላይ እንደሚቆም ዐውቃለሁ። ቈዳዬ ቢጠፋም፣ ከሥጋዬ ብለይም፣ እግዚአብሔርን አየዋለሁ፤ ሌላ ሳይሆን እኔው በገዛ ዐይኔ፣ እኔ ራሴ አየዋለሁ፤ ልቤ በውስጤ ምንኛ በጉጉት ዛለ” በማለት ይናገራል (19፥25-27)።
በአጠቃላይ መልኩ ስናየው፣ በብሉይ ኪዳን ላለው የቃል ኪዳን ሕዝብ የተሰጠው ጽኑ ተስፋ፣ ከአምላካቸው ጋራ ያለውን ኀብረት በሞት ምክንያት ፈጽሞ ሊወገድ እንደማይችል የሚያመለክት ነው። ይህን እውነት በተመለከተ እጅግ አስገራሚ አስደናቂ ነገር በመጽሐፍ ሳሙኤል ላይ፣ “እግዚአብሔር ይገድላል፣ ያድናልም፤ ወደ መቃብር ያወርዳል፤ ያወጣልም” በሚል ተገልጧል (1ሳሙ. 2፥6)። ይህ እውነት በአእምሮ ለመረዳት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ያለ ምንም ማመንታት ልንቀበለው የተገባ ሊሆን ያለ ርግጠኛ ነገር ነው። ምክንያቱን ይህን ተስፋ እውን የሚያደርገው ሁሉን ቻዩ፣ ጠቢቡን፣ ኀያሉና በሞትና በሕይወት ላይ ሥልጣን ያለው እግዚአብሔር በመሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን ሞት ሰዎች ወደ ዘላለም ቤታቸው የሚሄዱበት መንገድ ስለመሆኑ ይገልጣል (መክ. 12፥5 እና 7)።
ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የምንረዳው እውነት፣ በየትኛውም ዐይነት አስቸጋሪ የሕይወት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ ሕዝቡን የሚታደግ አምላክ በመሆኑ ምክንያት እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በእምነትና በተስፋ ጸንተን መጋፈጥ እንዳለብን ነው። በመጨረሻም፣ ሁላችንም ልንገነዘበው የተገባ እውነት፣ ከዚህ ጉዳይ ላይ ያነሣናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት በሙሉ የሚያወሱት በመጨረሻው ዘመን ለሰው ልጆች በሙሉ አካላዊ ትንሣኤ እንደሚያገኙ ነው።
ሄኖክ፣ አብርሃምና ኤልያስ፦ ትንሣኤና ንጥቀት
ከአዲስ ኪዳን የምንረዳው አንድ እውነት፣ ቢያንስ ከአብርሃም ጀምሮ ያሉ አማኞች እግዚአብሔር ሙታንን የማስነሣት ኀይልና ሥልጣን እንዳለው ያምኑ እንደነበር ነው። ስለዚህ ጉዳይ ማርቲን ሉተር፦
ስለ ሙታን ትንሣኤ የሚያወሳው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት በልባችን የታተመ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ የብሉይ ኪዳን አማኞች ጭምር ስለ ሞት ብቻ ሳይሆን፣ ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት በትዕግሥት የተደገፈ መረዳት ስለ ነበራቸው ነው። እነዚህ የብሉይ ኪዳን አማኞች ስለ ሙታን ትንሣኤ የነበራቸው እምነት በሚገባ ተገልጦ ያለው በአዲስ ኪዳን ነው። ይሁን እንጂ እነርሱ ራሳቸው በዘመናቸው ስለ ሙታን ትንሣኤ በግልጽ መረዳታቸውን ከእነዚህ የአዲስ ኪዳን ምንባባት መረዳት እንችላለ። እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እግዚአብሔር የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ እንዳልሆነ ገልጾ ነበር (ማቴ. 22፥32)። ስለዚህ በእግዚአብሔር ላይ ተስፋቸውን የጣሉ የቀደሙት የእምነት አባቶች በሙሉ ያለ ምንም ጥርጥር በሙታን ትንሣኤ ያምኑ ነበር
በማለት ተናግሮ ነበር (Concordia, 1965:116)።
ዘፍጥረት 5፥24 ሄኖክ ሞትን ሳያይ እንደ ተወሰደ ይናገራል። ታሪኩን ትልቅ ትኩረት ሰጥተን ስናየው ከአብርሃም በፊት የኖረው ይህ ሰው በፈርሀ እግዚአብሔርና በእምነት እንደተመላለሰ እንገነዘባለን። ይህ እምነቱ ደግሞ ሞትን ሳያይ ወደ እግዚአብሔር እንዲወሰድ አስቻለው። የሄኖክን ታሪክ የዕብራውያን ጸሐፊ ሲዘግብ፣ “ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ከዚህ ዓለም ተወሰደ፤ እግዚአብሔር ስለ ወሰደውም አልተገኘም፤ ከመወሰዱ በፊት እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና” በሚል ገልጦአል (11፥5)። እግዚአብሔር ወሰደው የሚለው ቃል በዕብራይስጡ የሚለው ሲሆን፣ በ2ነገሥት 2፥3 እና 5 አልያስ ሞትን ሳያይ የተነጠቀበትን ክሥተት ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል። በመሆኑም ሁለቱም፣ ማለትም የሄኖክም ሆነ የኤልያስ ታሪክ አንድ ዐይነት ናቸው (Bruce Waltke, Zondervan, 2002:115)። ስለዚህም ሄኖክና ኤልያስ ሁለቱም በእግዚአብሔር ተኣምራዊ መንገድ ሳይሞቱ በአካል እያሉ ወደ ሰማያዊ ስፍራ ተወስደዋል ማለት ነው።
የጌታ ባሪያ
ከትንቢተ ኢሳይያስ 53፥9-12 እንደምንገነዘበው ከሆነ፣ ከታማኙ የጌታ ባሪያ ሥቃይ፣ መከራና ሞትና በርሱ ከማመን የተነሣ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይሆናል። ይህ አገልጋይ ልክ እንደሙሴ አዲሱን ዘፀአት የሚያደርግ አዳኝ ነቢይ ሆኖ ሕዝቡን ይሰበስባል (ዘዳ. 18፥15)። እንዲሁም ደግሞ እንደ ንጉሥ ዳዊት ሆኖ ሕዝቡን በጽድቅ የሚመራ እረኛ ይሆናል (ሕዝ. 34፥23-24፤ 37፥24-25)።
ይህ የጌታ አገልጋይ ከሥቃይ፣ ከሐዘንና የሞት መርዝ ካለበት ኀጢአት፣ ደስታና ርካታ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ሰላም፣ ወደ ሁለንታናዊ ብልጽግናና በራሱ ማንነትና ህልውና ውስጥ ወደሚገኝ አንድነት በርካቶችን ያመጣቸዋል። የኢሳይያስ ትንቢት፣ “ነፍሱን የኀጢአት መሥዋዕት ቢያደርገው እንኳን ዘሩን ያያል፤ ዕድሜውም ይረዝማል” በማለት ስለ ባሪያው አስደናቂ የማዳን ሥራ ይናገራል (53፥10)።
በዚህ ምንባብ ውስጥ ስለ ዕድሜ መርዘም የተገለጠው ሐሳብ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ለ20 ጊዜያት በልዩ ልዩ መልክ የተጠቀሰ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ከምድራዊ ዕድሜ መርዘም ጋራ ተያይዞ ቀርቧል (ዘዳ. 4፥40)። ይሁን እንጂ በዚህ የኢሳይያስ ምንባብ እና እንዲሁም ምናልባትም በመዝሙር 23፥6 ላይ ሐሳቡ ከምድራዊው ዕድሜ ዐልፎ ሰው ከሞተ በኋላ ሊኖረው ስለሚችል ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚያወሳ መገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም ምንባቡ ውስጥ ነቢዩ የሚያወሳው የጌታ ባሪያ ዕድሜ ከሞት በኋላም እንደሚቀጥል ነው።
በመጨረሻም ፍትሕ ከሞት ይልቃል
በዚህ ስፍራ ትክክለኛና ቀና ስለሆነው ፍርድ ጋራ የተያያዘ ሐሳብ መሰንዘር እንችላለን። ብሩስ ዋልኬ የተሰኘ ምሁር፣ “በመጨረሻም ፍትሕ ይረጋገጣል” ብሎ ነበር (ምሳ. 3፥31-35፤ 16፥4-5)፤ ጻድቁ ሰው ይሞታል (ምሳ. 1፥10-19)፣ ይሁን እንጂ ደግሞ ከሞት መዳንና ከመቃብር መውጣትም ይሆንለታል፤ በመጨረሻው ዘመን ከሞት በላይ የሆነ ሕይወትም ያገኛል።
በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔርን ለሚወዱት ጻድቃን በረከትና ሽልማት ሲሆን፣ ለክፉዎችና ዐመፀኞች ግን ቅጣትና ፍርድ ይሆናል። በሌላ አባባል ብሩስ ዋልኬ እንዳለው፣ የመጨረሻው ፍርድ በሰው ልጆች ላይ የሚሆነው እነርሱ ከተለማመዱበትና ከሚያውቁት ስፍራና አገዛዝ ውጪ ስለ ስፍራው ማስረጃ ሊያቀርቡ በማይችሉበት ሁኔታ ነው (ገጽ. 910)። መጽሐፍ ቅዱስ በጻድቅ ሰው መንገድ ላይ ሕይወት እንዳለና በጎዳናዋ ሞት እንደሌላ ይናገራል (ምሳ. 12፥28)። በተመሳሳይ መልኩም ዘማሪው፣ “እግዚአብሔር ነፍሴን ከሲኦል እጅ ይቤዣታል” ይላል (49፥15)። ሞት ድምፁን አውጥቶ ቃል የማያሰማበት መጨረሻ ይመጣል፤ ምክንያቱ ቅዱስ ቃሉ እንደሚነግረን ሞት በሕይወት ይዋጣልና (ዘፍ. 4፥24፤ 2ነገ. 2፥1፤ መዝ. 49፥15፤ 73፥23፤ ኢሳ. 14፥13_15)።[1]
የመጽሐፈ ምሳሌ ጽሐፊ፣ ጻድቃን የሕይወት ሽልማት እንደሚያገኙ (12፥28) እና ከሞት አምልጠው በእግዚአብሔር በመታመን በርሱ ዘንድ መሸሸጊያ እንደሚያገኙ ይናገራል (14፥32)። የጻድቃን ተስፋቸው ከክፉዎችና ከጠማሞች በተቅራኒ የዘላለም ደስታ እንደሆነም ያረጋግጣል (23፥17-18፤ 11፥17፤ 12፥28፤ 24፥19-20)።
ከሌሎች የብሉይ ኪዳን ምንባባት፣ ማለትም ከኢዮብ 19፥25-27፤ ከመዝሙረዳዊት 49፥15 እና 73፥23-24፤ ከኢሳይያስ 14፥13-15 እና ከዳንኤል 12፥2 በተቃራኒ በመጽሐፈ ምሳሌ የምንመለከተው የሙታን ትንሣኤ ትምህርት ሳይሆን፣ አለመሞትን ነው። ምሳሌ 15፥24 ከታች፣ ከሲዖል ሕይወት አምልጦ ስለመወሰድ ይናገራል። ምንባቡን ቃል በቃል ስንረዳው፣ “ታችኛው መቃብር” በመባል ከሚያወቀው ክፍል (š e )ôl) ወደ ላይ መንቀሳቀስ ማለት ሲሆን፣ ይህም እግዚአብሔርን የሚወዱ ጻድቃን መጨረሻቸው በእግዚአብሔር በአምላካቸው ፊት በክብር መታየት መሆኑን ነው። በዚህም መሠረት ደኅንነት ማለት ከሞትና ከመቃብር አምልጦ ዋስትናው በተጠበቀ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ መገኘት ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም ያለፈ ነው። ሞት ሕይወትን የሚውጥ ኀይል ሳይሆን፣ ሞት ራሱ በእግዚአብሔር የተዋጠ ነገር ነው። እግዚአብሔርን የመፍራትና በጽድቅ የመኖር ሽልማቱ፣ በሞት ሊበላሽ የማይችል የተትረፈረፈ ሕይወት ነው።
ኢየሱስ በምድር በነበረበት ወቅት አካላዊ የሙታን ትንሣኤ እንደሚኖር በስፋት ይነገር ነበር
በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን በነበሩ አይሁዶች ዘንድ ትንሣኤ እንዳለ ይታመን የነበር ሲሆን፣ የሙታን ትንሣኤ በበርካታ የአይሁድ ሥነ ጽሑፎች ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። በዚህም ምክንያት በርካታ አይሁዶች በዓለም መጨረሻ ላይ ለሙታን ሁሉ አጠቃላይ ትንሣኤ እንደሚኖር ያምኑ ነበር (ዮሐ. 5፥29፤ 11፥24)። ምንም እንኳን ሰዱቃውያን በሙታን ትንሣኤ የማያምኑ ቢሆኑም፣ ፈርሳውያን ግን በሙታን ትንሣኤ ያምኑ ነበር (ሐዋ. 23፥6-8)። የሰዱቃውያን በሙታን ትንሣኤ ያለማመን በመቃወም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ኀይልና ሥልጣን የሙታን ትንሣኤ እንደሚሆን፣
የምትስቱት እኮ ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ስለማታውቁ ነው! ሙታን በሚነሡበት ጊዜ እንደ ሰማይ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም። ስለ ሙታን መነሣት ግን፣ በሙሴ መጽሐፍ ይኸውም ስለ ቍጥቋጦው በተነገረው ክፍል፣ እግዚአብሔር ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ያለውን አላነበባችሁምን? እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ ስለዚህ እጅግ ተሳስታችኋል
በማለት አስረግጦ አስምሮ ነበር (ማር. 12፥25-27፤ በተጨማሪም ዘፀ. 3፥6 ይመልከቱ)።
ወንጌላዊ ሉቃስ ደግሞ ሰዎች ከሞት በኋላ ስለሚሆንላቸው ትንኤና ይወት የዚህ ዓለም ልጆች ከተባሉት ትንሳኤም ከማይሆንላቸው ጋር በማነጻጸር ትንሣኤ ስለሚሆንላቸው ሰዎች በግልጽ ሲዘግብ እንመለከታለን (ሉቃስ 12፡25-27) ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሙታን ትንሣኤና የዘላለም ሕይወት ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋራ ካላቸው ኀብረት አንጻር የተቃኘ ስለመሆኑ አስተምሯል (ሉቃ. 20፥38)። ምንባቡ በግልጽ፣ “ሁሉም በርሱ ሕያዋን ናቸው” ይላል። በዚህም ምክንያት ነው፣ አር. ኢ. ኦ. ዋይት የተሰኘ ጸሐፊ፣ “በእግዚአብሔር ዘንድ ሞት የለም፤ ይህም ትንሣኤ ስላለ ነው” በማለት የሚሞግተው (2017፡745)።
ከሁሉ በላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማቴዎስ 19፥16፤ ማርቆስ 10፥17 እና ሉቃስ 18፥18 ላይ ከባለጠጋው ጎልማሳ ጋራ ስለ ዘላለም ሕይወት በተነጋገረበት ወቅት የዘላለም ሕይወትን ጒዳይ ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋራ የተቆራኘ ስለ መሆኑና ከሞት በኋላ ረጅም ዘመን መኖር እንዳላ አውስቶ ነበር።
በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሃነምን ክፋት ጠቅሶ በተናገረበት ትምህርቱ፣ የሙታን ትንሣኤ የሚሆነው የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ በሲዖል ውስጥ ተጥሎ የዘላለም ፍርድ ለመቀበልም ጭምር እንደሆነ አጥብቆ በማስጠንቀቅ አስተምሯል (ማር. 9፥43፡45፡47፤ ሉቃ. 12፥5)። ይህ የጌታችን ትምህርት ዓላማው እግዚአብሔርን በመታዘዝና ትእዛዛቱን በመጠበቅ ለጽኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወትና ሽልማት እንደሚጠብቃቸው፣ ርሱን ለማይታዘዙ ዐመፀኞች ግን የዘላለም ሥቃይና ቅጥዐት እንደሚጠብቃቸው ማሳየት ነው (ማቴ. 12፥35-37፤ 13፥24-30፡36-43፤ 24፥40-51፤ 25፥30-36፤ ሉቃ. 12፥41-46፤ 17፥34-37)። በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ትንሣኤ በኋላ ለጻድቃን ስለሚሆነው አስደናቂና ታላቅ ነገር ለደቀ መዛሙርቱ ያስተምራቸው ነበር (ሉቃ. 14፥7-14)። እንዲሁም የአልዓዘርና የባለጠጋው ሰው ምሳሌ የሙታን ትንሣኤ ትምህርት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው (ሉቃ. 16፥19-31)።
ኢየሱስ ስለ ሙታን ትንሣኤ ያስተማረበት አስደናቂ ሁኔታዎች
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሌሎች ጒዳዮች ካስተማራቸው ጋር ሲነጻጻር ስለ ትንሣኤ ያስተማረበት ዐውድ ሰፊ ሲሆን፣ የሠራቸው ተኣምራቶችም ተከታትዮቹ በርሱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ ያስተማራቸውን ሁኔታዎች እንደሚከተለው ማስቀመጥ ይቻላል፦
- በርካታ ሰዎች ባሉበት ሁኔታ በኀይልና በሥልጣን ያደረጋቸው ድንቅ ሥራዎች። ለምሳሌ፦ ብዙ ዐይነት ሰዎችን ያጠቃለለ የፈውስ አገልግሎት፣ ከአጋንንት እሥራት ነጻ የማውጣት ተግባርና፣ በተፈጥሮ ላይ የገለጣቸው ተኣምራቶች (የአየር ሁኔታ መለወጥ፣ በጥቂት ምግብ በርካታ ሰዎችን መመገብና የመሳሰሉ ተግባራት)።
- በሞትና በሕይወት ላይ የተገለጠው ኀይልና ሥልጣኑ። ለምሳሌ፦ የኢያኢሮስን ልጅ (ማር. 5፥21-43)፣ ባል የሞተባትን ባልቴት ልጅ (ሉቃ. 7፥11-17) እና አልዓዘርን (ዮሐ. 11፥1-44) ከሙታን ማሰነሣት። እነዚህ ተግባራት ርሱ በሞት ላይ ሥልጣን እንዳለው የሚያስረግጡ ናቸው።
እነዚህ ከላይ የተገለጹ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ርሱ መሲሕ እንደሆነ ለተጠየቀው ጥያቄ የሰጠውም ምላሽ የሚያጸኑ ናቸው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥያቄውን፣ “ዕውሮች ያያሉ፤ ዐንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም የምሥራች እየተሰበከ ነው፤” ማለት ነበር የመለሰው (ማቴ. 11፥5)። የዚህ ታሪክ ዋና ነጥቡ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው ልጆች አካል ላይ በሥልጣኑ ያደረጋቸው ነገሮች የትንሣኤውን እውነተኝነት በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው። ይህን እውነት ዊልያም ሼድ የተባለ ጸሐፊ፣ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ‘ተነሥና ዐልጋህን ተሸክመህ ሂድ’ ማለቱ ርሱ ሞተው በመቃብር ውስጥ ያሉትን ሰዎች በኀይልን በሥልጣኑ፣ ‘ንቁና ውጡ’ ብሎ ማዘዝ እንደሚችል ማሳያ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በሽተኞችን ከፈወሰና ጎዶሎ አካልን ሙሉ ማድረግ ከቻለ፣ ሙታንንም አስነሥቶ ሙሉና ፍጹም ማንነት እንዲያገኙ ማድረግ ከቻለ፣ እንዲሁ በትንሣኤ ኀይል የበለጠ ተኣምር ማድረግ ይችላል” በማለት ገልጾ ነበር (2003፡868)።
- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማርቆስ 8፥31፤ 10፥34 (በተጨማሪም ሆሴ. 6፥2፤ ዘፍ. 22፥4፤ 42፥17-18፤ ኢሳ. 2፥16፤ ዮናስ 2፥1 ይመልከቱ) ስለ ጠቅላላው ሙታን ትንሣኤ በተመለከተ ያስተማረው ትምህርት፣ በቀጥታ ከሦስት ቀናት በኋላ ሊሆን ስላለው የራሱ ትንሣኤ ከተናገረው ጋራ አንድ ላይ መሄድ የሚችል ብቻ ሳይሆን፣ የሙታን ትንሣኤ ርግጠኛና አይቀሬ የመሆኑን እውነት የሚይታስረግጥ ነው።
- በመገለጥ ተራራ ላይ የተገለጠው አስደናቂ ክብሩ፣ ከብዙ ዓመታት በፊት የሞቱትን ሙሴንና ኤልያስን የሚያሳስበን ሲሆን፣ በማቴዎስ 7፥1-13 ደግሞ ክሥተቱ ከኢየሱስ ትንሣኤ ጋራ በቀጥታ ተቆራኝቶ ቀርቧል። በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመገለጥ ተራራ ላይ ወደፊት ሊከሰት ስላለው ትንሣኤ ተናግሮ ነበር። ይህን እውነት የምንገነዘበው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ርሱ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ ደቀ መዛሙርትን አጠንቅቋቸው ስለ ነበር ነው (ማር. 9፥9)።
- የእግዚአብሔርን መንግሥት ትምህርቶስ ስናጠና፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መክበርና ከፍ ማለት (ማር. 12፥1-11) እና የርሱ በደመና ሆኖ በታላቅ ክብር መገለጥ (ማር. 13፥26፤ 14፥62) ትንሣኤውን የሚያወሱ እውነቶች ሆነው እናገኛቸዋለን። ይህን እውነት የምንረዳው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሞቱና ትንሣኤውና እንዲሁም ስለ ሕማማቱ በተናገረባቸው ወቅቶች ለደቀ መዛሙርቱ፣ “ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ” በማለቱ ምክንያት ነው (ማር. 14፥28)።
ይህን ክፍል ለማጠቃለል ያህል፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በፊት ያስተማራቸው ትምህርቶች በሙሉ በትንሣኤር ዙሪያ የሚያውጠነጥኑ ናቸው። እነዚህ ትምህርቶች፣ የእግዚአብሔርን የመፍጠርና የማደስ ተግባራቱን የሚያወሱ ናቸው።
[1] Waltke, Old Testament Theology, 229
ምዕራፍ 5
የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ባሕርይ
አዲስ የታሪክ ክሥተት ነው
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ፣ ግልጽ ያልሆነ ስውር ምስጢር ወይም በንግግር ደረጃ ብቻ ሊገለጽ የሚቻል ነገር ሳይሆን፣ በእውን የተደረገ አካላዊና ታሪካዊ ሀቅ ነው። ከታች እንደምንመለከተው፣ ትንሣኤው በተግባር የተከናወነ፣ በበርካቶች በስፋት የተመሰከረ፣ ለብዙዎች ፊት ለፊት የታየና እውነት ስለ መሆኑ የተረጋገጠ ክሥተት ነው (1ቆሮ. 15፥5-8)። የክርስቶስ ትንሣኤ ከታሪካዊ እውንነቱም በላይ፣ የርሱን መለኮታዊ ኀይል ከወቅታዊው ታሪካዊ ክሥተት ጋራ አቆራኝቶ የሚያሳይ ነው። ይህ ማለት ግን አንዳንዶች እንደሚያስቡት የክርስቶስን የትንሣኤ ቀን በርግጠኝነት መናገር እንችላለን ማለት አይደለም። አንዳንዶች ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን የተነሣው በአውሮፓውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 5, 33 ዓ.ም በዕለተ እሁድ እንደሆነ ያትታሉ (Crossway, 2012:593)። ይሁን እንጂ አንድ ማወቅ ያለብን እውነት፣ የክርስቶስ ትንሣኤ የተከናወነው ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋራ በተቃረነ መልኩ ሳይሆን፣ ከሌሎች ድርጊቶችና ክሥተቶች ጋራ በተቆራኘ መልኩ መሆኑን ነው።
ይህ ማለት ግን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ካለፉት ታሪኮች ጋራ ብቻ የተሳሰረ ነው ማለት አይደለም። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ፣ ከሌሎች ክሥተቶች ሁሉ የተለየ ብቸኛና ወሳኝ ክሥተት ሲሆን፣ ለሌሎች ታሪኮችና ለፍጥረት ሁሉ ወሳኝ ቅርጽ ሊሰጥ የሚችል ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ በታሪክ ውስጥ በጊዜና በስፍራ የተከናወነ ክሥተት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ትንሣኤው ዘላለማዊ ጒዳይ አጠቃልሎ የያዘና አዳዲስ እውነቶችን የሚገልጥ ነው። በመሆኑም፣ የክርስቶስ ትንሣኤ የተለመዱ ታሪካዊ ክሥተቶችን በሙሉ አጠቃልሎ የያዘ ነው ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ደግሞ ቶረንስ የተሰኘ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዳተተው፣ “የክርስቶስ ትንሣኤ ለየት ያለ የታሪክ ክሥተት ነው። የትንሣኤው እውነትና አስፈላጊነቱ እየቀነሰ ወደ መቃብር እንደሚወርድ ነገር፣ ተስፋው እየደበዘዘ ሳይሆን፣ ይልቁን እየጨመረና ከፍ እያለ የሚቀጥል ሆኖ ታይቷል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ኖረው ካለፉ ሁሉ በላይ ሆኖ ሕያው ነው እንጂ፣ ሟች ሆኖ በመቃብር ውስጥ የለም። ይህ የትንሣኤ ኢየሱስ አሁን ያለና ወደፊትም የሚመጣ፣ በመገለጡም ደግሞ ሕይወት መኖሩን የሚያረጋግጥል ጌታ ነው (ቶራንስ፣ 88-89)።
በመጽሐፍ ቅዱሳን ውስጥ በርካታ የትንሣኤ ታሪኮች ተዘግበዋል። ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ከእነዚህ የትንሣኤ ታሪኮች ጋራ ስናስተያይ፣ የርሱ ትንሣኤ ልዩና ብቸኛ ክሥተት ስለመሆኑ እንገነዘባለን። ለምሳሌ፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ያስነሣቸው እንደ አልዓዘር ያሉ ሰዎች ተመልሰው ሞተዋል። ከእነዚህ ሁሉ በተቃራኒ ግን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ በሰማያት በአባቱ ቀኝ ያለ፣ ስለ እኛ የምማልድልንና የምጸልይልን ሕያው ሊቀ ካህናችን ርሱ ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳችን አስረግጦ ይነግረናል (ዕብ. 7፥25)። ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ ሕያውና ለዘላለም የሚኖር ጌታ ነው። በመንፈሱ አማካይነት በተከታዮቹና በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ በመኖር ይቀጥላል (ሮሜ 8፥11)። በመሆኑም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ታሪካዊና ብቸኛ ክሥተት ነው።
በሁሉም አቅጣጫ ከፍጥረት ሁሉ በኩር መሆኑ
ከተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት እንደምንረዳው (ለምሳሌ፦ ሐዋ. 26፥23፣ ራእ. 1፥5፤ ሮሜ 8፥29፤ ቆላ. 1፥15፤ 1ቆሮ. 15፥20 እና ቆላ. 1፥18) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሁሉም ዐይነት መንገዶች ዳግመኛ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጆች በሆኑ ወንድሞቹም ሆነ በፍጥረታት ኹሉ ላይ በኩር ወይም የመጀመሪያ ስለመሆኑ እንገነዘባለን። ከሁሉ ባላይ ግን ትንሣኤውን በተመለከተ የኢየሱስ ክርስቶስ በኩርነት በሁለት የተለያየ መልኩ ልንመለከት እንችላለን፦ 1) ኢየሱስ ክርስቶስ ከጊዜ በፊት የነበረ ከመሆኑ እውነት አንጻር ሲሆን፣ 2) ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍጥረት ሁሉ በፊት፣ ማለትም በማንነቱ ሞትን ድል የነሣ በመሆኑ ምክንያት በመለኮታዊ ማንነትና በደረጃው ከሙታን በኩር ከመሆን እውነት አንጻር ነው።[1]
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በኩር እንደሆነ የሚያወሳው አስተሳሰብ ርሱ የምድር ነገሥታት ሁሉ ገዢ እንደሆነ እና የማይለወጠው ባሕርይ ያለው ባለሥልጣን እንደሆነ ከሚያወሳው እውነት ጋራ ተጣጥሞ የሚሄድ ነው (ራእ. 1፥5)። ክርስቶስ በታሪክ ሞትን አሻንፎ በተነሣ ብቸኛው ነው። እንዲሁም ርሱ በኀይል፣ በሥልጣን፣ በማዕረግና በልዕልና ተወዳዳሪ የሌለው ብቸኛ የበላይ አምላክ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን፣ ርሱ ከሙታን ከተነሣ በኋላ፣ የሞትና የሲኦልን ቁልፍ በእጁ ይዞ ለዘላለም የሚኖር አምላክ ነው (ራእ. 1፥8)። ስለዚህም ርሱ ተወዳዳሪና አቻ የሌለው አምላክ_ሰው ነው። ርሱ መለኮቱና ሰብእናው ተጣምረው አንድ ላይ ያሉ ጌታ ሆኖ ለዘላለም ይኖራል።
የክርስቶስ መክበር የመጀመሪያውና ግልጽ ደረጃ
አምላክ ሥጋ ከሆነ በኋላ የሆኑ ነገሮች በሙሉ፣ ማለትም ልደቱ፣ አገልግሎቱ፣ ሞቱና መቀበሩ ጭምር ርሱ ከሰማይ ወደ ምድር ዝቅ እያለ መውረዱን የሚያመለክቱ ድርጊቶች ነበሩ። ሞቱ የዝቅታው ጥልቀት መጨረሻ ነበር። “ከሰማይ ወደ ምድር ወረደ” (ዮሐ. 6፥41፡51 እና 58)። ይሁን እንጂ ሞቱን ተከትሎ ወዲያው ትንሣኤ ሆነ። ከትንሣኤው በኋላ ወደ አባቱ እቅፍ፣ ወደ ትክክለኛው የክብር ስፍራው ተመለሰ (ዮሐ. 20፥17)። ይህም ርሱ በመሲሓዊ ሥልጣኑ ከፍ ብሎ ወደ ነበረበት ስፍራ መመለሱን አመልካች ነው (መዝ. 110፥1፤ ማር. 12፥36፤ ሐዋ. 2፥34፤ ዕብ. 1፥13፤ 1ጴጥ. 3፥22)። የክርስቶስ ክብር ወይም የርሱ ከፍ ከፍ ማለት የሚከተሉ ነገሮችን ያጠቃልላል፦ 1) ሞትን ድል በመንሣት ትንሣኤ ማግኘቱን፤ 2) ወደ ሰማይ ማረጒን፤ 3) በሰማዩ ስፍራ በአባቶ ቀኝ በክብር ተቀምጦ መንገሡን፤ 4) በሕዝቡ ላይ መንፈሱን ማፍሰሱን፤ 5) ቀጣይነት ባለው መልኩ (ባለማቋረጥ) ስለ እኛ የሚያማልድ መሆኑን፤ እና 6) በታላቅ ክብር ዳግመኛ የሚመጣ መሆኑን። በተጨማሪም የክርስቶስን ዝቅ ማለትና መክበሩን በተመለከተ፣ በመለኮታዊውና በሰብአዊ ባሕርያቱ መካከል ልዩነት እንዳለ እናስተውላለን። ይህን እውነት በተመለከተ ቶማስ ብራኬል የተሰኘ ጸሐፊ የሚከተለውን ብሎ ነበር፦
ክርስቶስ መለኮት እንደመሆኑ መጠን፣ ርሱ በሥጋው መከራን ሲቀበል መለኮታዊ ባሕርዩ አልተሠቃየም ነበር። ርሱ ቀድሞውኑም የከበረ መለኮት እንደ መሆኑ መጠን ከሙታን ተነሥቶ መክበሩ መለኮቱን አይመለከትም ነበር። ርሱ በባሕዩ እጅግ ምጡቅና የከበረ፣ አይለወጤ አምላክ እንደሆነ ነበር። ይሁን እንጂ ሥጋ በነሣ ጊዜ በሥጋ ውስንነት ውስጥ ተቀብቦ ዝቅ ያለው የመለኮት ባሕርይ፣ በትንሣኤው ክብር ከፍ ባለ ቀድሞ የነበረውን ክብሩን ገለጠ። በርግጥ በትንሣኤ ከፍ ብሎ የከበረው የተዋረደው ሥጋዊ ባሕርዩ ነበር።[2]
በእምነት ዐይን ሲታይ የክርስቶስ ምድራዊ ተግባራቱ ታላቁን ክብሩንና ዝቅ ያለበትን ውርደቱን አንድ ላይ አቅርቧል (ጄርሚ አር. ትርት 2017፡842)። እንዲሁም ደግሞ በትሕትና የተሞላውና መሥዋዕትነት የሚያስከፍል የአገልጋይነት ልቡናው የክርስቶስን ክብር የሞላበት አሁናዊ ሥልጣኑንና በምድር ሁሉ ላይ የነበረውን ሉዓላዊ አገዛዙን መግለጡ እውን ነው (ዮሐ. 1፥14፤ 12፥23-33፤ ራእ. 5፥5-6)። በዮሐንስ ቋንቋ የኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሰው በእንጨት ላይ ተሰቅሎ መሞቱ የሚያሳየው፣ ርሱ ከፍ ብሎ መክበሩን ነው (ዮሐ. 3፥14፤ 8፥28፤ 12፥32-33)። ይህም ርሱ ክብርና ድል የተቀዳጀው በውርደትና በሽንፈት ዐልፎ እንደሆነ ነው። በሌላ አነጋገር የእግዚአብሔር የዘላለም መንግሥቱ የተመሠረተው፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የመዋጀት፣ ወይም ውድ ነፍሱን ሳይሳሳ በመስጠት ባገለገለበት የመሥዋዕትነት አገልግሎቱ ነው ማለት ይቻላል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ምንም እንኳን ስውር ድል ቢመልስም፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ትንሣኤ የተገኘው ድል በሞት ላይ የትገኘ ድል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። በመሆኑም፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መነሣት ርሱ ዘላለማዊና ሰማይና ምድርን የሚገዛ ንጉሥ መሆኑን የሚገልጥ ክሥተት እንደሆነ መደምደም ይቻላል። በርግጥ ትንሣኤው በመስቀል ላይ ሥቃይና መሥዋዕታዊ የውርደት ሞት ወደ አስገራሚ ሰማያዊ ክብር የመሻገሩን ድል የሚያበስርም ጭምር ነው።
ይህን እውነት ጀርሚ የተሰኘ ጸሐፊ፣ “የክርስቶስ ትንሣኤና ርገቱ ከውርደትና ዝቅ ከማለት ወደ ክብር የተሸጋገረበት ነው በማለት እንደገለጠው እንዲሁ ነው። በመሆኑም፣ ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ፣ አሁን በኀጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ ሆኖ ራሱን ለመሥዋዕት አያቀርብም (ሮሜ 8፥3፤ ዕብ. 9፥26)። የክርስቶስ ኢየሱስ የትንሣኤ ክብሩ ነጻብራቅ ድንግዝግዝ ሳይሆን፣ በሚያስደንቅ ሁኔት ግልጥና ድንቅ ብርሃን ሆኖ የሚታይ ነበር (ራእ. 1፥10_18)። በፍጥረት ሁሉ ፊት እንደመሥዋዕት በግ ሆኖ የታረደው ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ልጅ፣ አሁን በትንሣኤው የአዲስ ፍጥረት ራስ ሆኖ ከእግዚአብሔር ጋራ በመንገሥ እየተመለከና እየተወደሰ ይኖራል” (2017፡842)።
በመሆኑም የክርስቶስ ትንሣኤ፣ የርሱ ታላቅ ክብር መግለጥ የመጀመሪያው ሂደት ሲሆን፣ የርሱን አምላክና ሰው ሆኖ መገለጡ፣ ወደ ሰማይ ያረገው የክብር ርገቱ፣ እንዲሁም በአብ ቀኝ መቀመጡ፣ መላእክት፣ ሥልጣናትና ኀይላት ሁሉ የሚገዙለትና የሚታዘዙለት ጌታና ንጉሥ ያደርገዋል (1ጴጥ. 3፥21-22)። ለክርስቶስ ትንሣኤ ትልቅ ትርጒም የሚሰጠው ይህ ታላቅ ሥራው ነው። ርሱ ዳግመኛ ተመልሶ ላይ ሞት ሞቶ ከሙታን ተነሥቷል። በዚህም ምክንያት ርሱ የእግዚአብሔር ልጅ፣ መሲሕና አዳኝ ጌታ ብቻ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ልዩ ልእልና የተላበሰ ባለግርማ አምላክ ሆኖ በእግዚአብሔር ሕዝብ ልብ ውስጥ ለዘላለም ነግሦ ይኖራል (ሕዝ. 37፥25፤ ዮሐ. 12፥34)።
በእግዚአብሔር ታላቅ ኀይል የክርስቶስ ኢየሱስ መቃብር ኮፈኑ መነሣት
የክርስቶስ ኢየሱስን ትንሣኤ በተመለከተ፣ ርሱ ከሙታን ስለ መነሣቱ እንጂ እንዴትና በምን ዐይነት መንገድ እንደተነሣ መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ትኲረት ሰጥቶ አያብራራም። ይሁን እንጂ፣ መቃብሩ ባዶ ሆኖ ከመገኘቱና አስከሬኑ ካለመገኘቱ የተነሣ፣ ይህ ባዶ መቃብር ራሱ ለክርስቶስ መነሣት ዋና ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል። በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ በትክክል መሞቱ ተረጋግጦ ነበር። ከዚያ በኋላ ነበር የተቀበረው። ነገር ግን ይህ የሞተው የኢየሱስ ክርስቶስ ሰውነት በፍጥነት ተሓድሶ አግኝቶ በትንሣኤ ሊነሣ ችሏል። በሌላ አነጋገር ክርስቶስ ከሙታን የተነሣው የሞተው አካሉ በተሓድሶ ነቅቶ ሕይወት በማግኘቱ ነበር ማለት ይቻላል።
በመሆኑም ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ስንናገር መጠቀ፣ ያለብን ተገቢ ቃላት anabiōskomai እና anazaō የሚሉ ናቸው። እነዚህ ቃላት አንድ የሞት ነገር ከሞተበት እንደገና ወደ ሕይወት መመለስን የሚገልጡ ናቸው። በተጨማሪም anastasis እና exanastasis የሚሉ ቃላት፣ “ትንሣኤ” የሚለው ትርጒም በቀጥታ ያመለክታሉ። እንዲሁም ደግሞanhistēmi የሚለው ቃል እንደገና መቆም ወይም መነሣት፣ እንዲሁም ከተጋደሙበት ብድግ ማለትን የሚያመለክት ቃል ነው። በመጨረሻ፣ egeirō የሚለው ቃል፣ “መንቃት” የሚል ትርጒም ስላለው ትንሣኤውን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል። ከእነዚህ የተለያዩ ቃላት የክርስቶስን ትንሣኤ ለማመልከት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ቃላት anhistēmi እና egeiro የሚሉት ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ እነዚህ ሁለቱ ቃላት ወደ ላይ ከፍ ማለትን ወይም መነሣትን የሚያመለክቱ ስለሆኑ ነው።
የክርስቶስ ትንሣኤ በታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ የታጀበ ነበር። ከመቃብሩ ላይ ድንጋዩን የሚያንከበልል ድንጋይ በመቃብሩ ላይ ተቀምጦ ታይቶ ነበር (ማቴ. 28፥1_2)። ልዩ በሆነ ሁኔታ የከሠተው የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የክርስቶስ ኢየሱስን መለኮታዊ ማንነት እና በሚቃወሙት ላይ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ቁጣ ነው። በተመሳሳይ ወቅት የታየው የመላእክት መገለጥ የሚያሳየው የክርስቶስን ታላቅነት፣ ቅድስናውን፣ ደስታውንና አስደናቂ ድሉን ነበር (ብራከል 1፡627)። የመቃብሩ ጠባቂዎች በታላቅ ድንጋጤ፣ ፍርሀትና መሸበር መሞላታቸው የተገለጠው የእግዚአብሔር መለኮታዊ ክብርና ኀይል እጅግ ታላቅ መሆኑን አመልካች ነበር (ማቴ. 28፥4)። ይሁን እንጂ ክርስቶስ ሕያው ሆኖ ከመቃብር የተነሣው በእነዚህ ክሥተቶችና ድርጊቶች አማካይነት አይደለም። የክርስቶስ ትንሣኤ የእነዚህ ነገሮች ጥገኛ አይደለም። የመሬት መንቀጥቀጥና የድንጋዩ መንከባለል የክርስቶስ ኢየሱስ አስከሬን መቃብሩ ውስጥ ያለመኖሩን ማሳያ ናቸው። በተጨማሪም የመላእክት መታየት በስፍራው የተገኙ ጠባቂዎችና ወደ መቃብሩ የመጡ ሴቶች የትንሣኤ ዐይን ምስክር መሆን ይችሉ ዘንድ ለማስቻል የትንሣኤውን እውንነት ማብሰር ነበር። በሌላ አነጋገር የመሬት መንቀጥቀጥና የመላእክቱ መታየት፣ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት፣ ማንኛውንም ዐይነት እንቅፋት የማስወገድ ኀይልና ሥልጣን እንዳለው ነው። የክርስቶስን ትንሣኤ ተከትሎ ከተከሠተው የመሬት መንቀጥቀጥ የተነሣ (ማቴ. 27፥51)፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ በምን ዐይነት ሁኔታ ከሙታን ሊንሣ ቻለ?” የሚል ጥያቄ መቀስቀሱ አይቀሬ ነው። ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ሊሆን የሚችል እውነት፣ “በብርታቱ ጒልበት” የሚል ነው ያለው (ኤፌ. 1፥20። የክርስቶስ ትንሣኤ በብርታቱ ጒልበት ነው። በተጨማሪም እግዚአብሔር ወሰንና ገደብ የሌለው የትንሣኤ ኀይል ነው (ፊልጵ. 3፥10 እና 21)። እግዚአብሔር የሞት ኀይልና ውጊያ ሰብሮ ክርስቶስን አስነሥቶታል፤ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለም (ሐዋ. 22፥4)። ክርስቶስ ኢየሱስ ከመቃብር እንዲነሣ ያደረገው የትንሣኤው ኀይል፣ በተለይም ሞትንና መበስበስን፣ እንዲሁም የዲያብሎስን ውጊያ እንዲሸነፍ ያደረገው የእግዚአብሔር ኀይል እጅግ ታላቅ ነው። በአጭር ቃል ለመግለጽ የልርስቶስ ትንሣኤ ተወዳዳሪና አምሳያ የማይገኝለት የእግዚአብሔር ኀይል መገለጡን የሚያሳይ ነው።
ሰዋዊ ሞትን መቀበልበስና ሕይወትን ፍጹም ማድረግ
የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሣኤ ባሕርይ በግልጽ የታየው በራሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው። ነገሩ ለእኛ በግልጽ ባይታይም፣ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ወዲያው የገባው ወደ እግዚአብሔር ህልውና እና ቅዱሳን መላእክት ወደሚገኙበት ስፍራ ነው። ይህ ያልተለመደና እንግዳ ክሥተት ነው። የክርስቶስ ኢየሱስ የእርገት ክብር በቀዳሚነት የተገለጠው በመገለጥ ተራራ ላይ ኢየሱስ ከሙሴና ኤልያስ ጋራ በነበረበት ጊዜ ነበር (ማቴ. 17፥3-4)። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ትንሣኤ በግልጽና በጥልቀት የሚያሳየን፣ በትንሣኤ አማካይነት የሚገለጠውን የሰው ልጅ ክብር ነው። በመሆኑም ከኢየሱስ ትንሣኤ ጋራ ይህ ሟት የሆነው አካል አዲስ፣ ሕያውና ዘላለማዊ ሆኖ ይለወጣል።
ከክርስቶስ ትንሣኤ የተነሣ፣ ይህ ደካማና ሟች የሆነው ሰውነታችን ወደ ዐዲስና ዘላለማዊ የትንሣኤ አካልነት የመለወጥ ተስፋ አግኝቷል። በዚህ ክሥተት ላይ ተመሥርተን መጥቀስ ያለብን አንድ እውነት፣ በክርስቶስ ኢየሱስ አማካይነት ይህን ሕይወት የተካፈሉ አማኞች ዋና መገለጫ ባሕርያቸው፣ በእውነተኛ የመንፈስ ትስስር ተጣምሮ እግዚአብሔር አብን በፍቅርና በአንድነት ማገልግለ እንዳለባቸው ነው። በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በማመናችን ምክንያት ልዩ ወደ ሆነው ዐዲስ የፍቅርና የአንድነት ሕይወት መጥተናል፤ በእውነተኛ ኅብረት ርሱን ወደምናገለግልበት አንድነት ተጠቃልለናል። እውነተኛና ፍጹም የሆነው ማንነታችን ይህ ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ ተቀብሮ ከሙታን መነሣቱን አራቱና ወንጌላትና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ይነግሩናል። እነዚህ መጻሕፍት የሚሰጡት ምስክርነት ርሱ የእውነትም ሞቶና ተቀብሮ ከሙታን መነሣቱን እንጂ፣ ራሱን ስቶ ከነበረበት ሁኔታ መንቃቱን አይደለም። በተጨማሪም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በባሕርዩ ፍጹም ልዩ ነው። ርሱ እንደ አልዓዘር፣ እንደ ኢያእሮስ ሴት ልጅና እንደሌሎች ሰዎች ጥቂት ዘመን ኖሮ ተመልሶ ለመሞትና ሊበሰብስ ከሙታን አልተነሣም። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነትም ሆነ፣ በነቢያት ማለትም በኤልያስና ኤልሳዕ አማካይነት ከሙታን የተነሡ ሁሉ፣ እንዲሁም በጌታን ትንሣኤ ወቅት ከሙታን ተነሡ የተባሉ ሰዎችም ሆነ (ማቴ. 27፥52-53)፣ በሐዋርያት አገልግሎት ከሙታን የተነሡ (ሐዋ. 9፥36-43፤ 20፥712)፣ የክርስቶስን ዐይነት ትንሣኤ አግኝተው ወደ ማይሞቱበትና ለዘላለም በሕይወት ወደሚኖሩበት ክብር አልገቡም። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ሰዎች በሙሉ ትንሣኤያቸው ጊዜያዊ ስለ ነበር ሁለት ዐይነት ሞት ነበር የሞቱት። አልዓዘርም ሆነ ሌሎች ጊዜያዊ ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች፣ ነፍሳቸው የተመለሰችው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ድካም ወደ ማያውቀው ፍጹም የትንሣኤ አካል አይደለም። እነዚህ ሰዎች ቀድሞውኑ ወደ ነበረው ደካማ ሥጋነት በመመለሳቸው ምክንያት ሥጋቸው ለፈተና፣ ለሥቃይ፣ ለኀጢአትና የአእምሮ መታወክ የተጋለጠ ነበር። በመጨረሻም ተመልሰው መሞታቸው ደግሞ አይቀሬ ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ፣ ቀድሞ በሥጋው ወራት ወደ ነበረበት የሕይወት ሁኔታ አልተመለሰም ነበር። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ወደ ሕይወት የተመለሰበትን ሁኔታ በተመለከተ ጌሪ ሃበርማስ የተሰኘ የዐዲስ ኪዳን ምሁር የማርቆስ ወንጌል 16፥12ን ጠቅሶ እንዳብራራው ከሆነ፣ ይህ የክርስቶስ የትንሣኤ አካል አካላዊ ብቻ ሳይሆን፣ ከተለመደው የተለየ ዐዲስና መንፈሳዊም ጭምር ነበር (ጌሪ ሃቤርማስ፣ 2017፡743)።
በአልዓዘርና በሌሎች ትንሣኤ ባገኙ ሰዎች እንዳየነው ከሆነ፣ ይህ ከሞት ወደ ሕይወት የተመለሰው ጊዜያዊው አካል ተመልሶ መሞቱ አይቀሬ ነው። የክርስቶስ ኢየሱስ ዐይነቱ ትንሣኤ ሁለት ሂደቶች ያሉት ነው፤ የመጀመሪያው የሞት መሸነፍ ሲሆን፣ ሁለተኛው የማይሞት ዐዲስ ሕይወት ማግኘት ነው። በሌላ አነጋገር በመጀመሪያ፣ ከሙታን መነሣት ማለት ከሞት እሥራት ነጻ መውጣት ሲሆን፣ ሁለተኛው መንፈሳዊና ዐዲስ ሕይወት በማግኘት በሞት ላይ መሰልጠን ማለት ነው። ይህን እውነት ቶራንስ የተሰኘ ምሁር፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ በተነሣበት ዐይነት ትንሣኤ መነሣት ማለት፣ ትንሣኤውን ያገኘው ሰው ዐዲስ ምርት ሆኖ የሚገለጥበት ዐዲስ ክሥተት ነው” በማለት ይገልጣል (ገጽ. 86)። በመሆኑም ትንሣኤ ማለት የነፍስ ወደ ሥጋ የመመለስ ተራ ክሥተት ሳይሆን፣ ለደካማውና ሟች ሥጋ ሙሉ ፈውስ ማግኘትና ከፍ ማለትም ጭምር ነው። ትንሣኤ የሰው ልጆች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ወደ ዐዲስና መልካም ሥርዐት የሚገቡብት ዐዲስ የሕይወት ዘይቤ ነው (ገጽ. 86)።
የአካልና የነፍስ ዘላለማዊ ዳግም ውህደት
የሰው ልጆች በሙሉ የሥጋና የነፍስ ሥሪት ሆነው እንደመፈጠራቸው መጠን፣ አካላዊና መንፈሳዊ ትንሣኤ የማይነጣጠሉና ርስ በርሳቸው የተሳሰሩ ናቸው። በመሆኑም ትንሣኤ መንፈሳዊ ብቻ ከሆነ በሞት ላይ የተገኘው ድል ከፍል ሆኖ ይቀራል። ይህ ማለት ደግሞ መሸነፍ እንጂ ድል አይደለም። በዚህ ሂደት በጣም አስፈላጊ የሆነው ሥጋ ሙት ሆኖ መቅረቱ ነው (ባቭንክ፣ 368)። በቁሳዊው ሥጋ ላይ የተገለጠው የክርስቶስ ትንሣኤ በኀጢአት ላይ የተገለጠው የክርስቶስ ኢየሱስ ኀይና ሥልጣን በቁሳዊው ዓለም ሁሉ ፊት ግልጽ ሆኖ እንዲታይ አድርጓል። ቁሳዊውን ማንነት ያዘው የክርስቶስ ኢየሱስ አካላዊ ትንሣኤ፣ ኢቁሳዊ የሆነው የሰው ነፍስ ቋሚና ዘላለማዊ ስለ መሆኑ እውነት ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ነው። ይህ እውነት የምያስረግጥልን፣ በትንሣኤ የታደሰው የክርስቶስ ኢየሱስ የትንሣኤ አካል በዐይን የሚታይና የሚዳሰስ መሆኑን ነው። ስለዚህም ትንሣኤን በተመለከተ፣ የሥጋና የነፍስ ትንሣኤ በማለት ለያይቶ ለመረዳት መጣር በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው። ያለ አካላዊ ትንሣኤ መንፈሳዊ ትንሣኤ ሊሆን ይችላል በማለት ልናስብ ፈጽሞ አይገባም (ተርቱሊያን፣ 3፡573)። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ሥጋና ነፍስን ያካተተ፣ ቋሚና የሙሉ ማንነት ተሓድሶ እንጂ አንዱን ከሌላው በነጠለ መንገድ የሚገለጥ አይደለም። ይሁን እንጂ ደግሞ አንድ ማወቅ ያለብን ነገር ለመንፈሳዊ ትንሣኤን ተጨባጭ ያደረገው ትንሣኤ በሚታይ አካላዊ መልክ መከናወኑ ነው።
የጥንት ግሪኮችና ሮማውያን ፍልስፍና የሰው ነፍስ ዘላለማዊ እንደሆነ ቢታመንም፣ ከሞት በኋላ የሰው አካል/ሥጋ በየትኛውም መልኩ በመኖር እንደሚቀጥል አያምኑም ነበር። የዐዲስ ኪዳን ጻሓፍት የብሉይ ኪዳን ምንባባትን እየጠቀሱ ሰዎች በአካል፣ በሥጋና በመንፈሳዊ እውነታዎች ከሙታን እንደሚነሡ እንደሚያምኑ የሚያወሱ እውነታዎችን እናገኛለን። አካላዊ የክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጆች ሁሉ ለኀጢአት፣ ከሞትን የዘላለም ፍርድ የመዳንና የመታደግ ሙሉ ተስፋ እንዳላቸው የሚያስረግጥ ነው። በሌላ ቋንቋ ሰዎች በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ፣ በርሱ አማካይነት ከተፈጸመው ሥራ የተነሣ ሥጋቸውና ነፍሳቸው በሙላት ይድናል ማለት ነው። ቅዱስ አውግስጢኖስ ይህን እውነት፣ የክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጆች መላው ማንነት በሁሉም አቅጣጫ እንደሚያድግ የሚያሳይ ሲሆን፣ ያ ዕድገት ደግሞ በሥጋና በነፍስ ወደ ፍጹምነት ወደሚያድግበት ሕይወት የሚመራ ነው” በማለት ይገልጣል። በመሆኑም ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ተነሣበት ዐይነት ትንሣኤ ስናወራ፣ በሥጋና በነፍስ መካከል ልዩነትን እንዳለ በማመላከት እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባናል።
ሞት የሰዎችን ሥጋና ነፍስ የሚለያይ ክሥተት መሆኑ እውን ነው። በዚህም ምክንያት በመጀመሪያ ደረጃ፣ በዚህ በኀጢአት በተያዘና በእግዚአብሔር ቁጣ በተሞላ ዓለም ውስጥ በሥጋ ስንኖር ሞት ሥጋና ነፍስን የሚለያይ የመጨረሻው ኀይል እንደሆነ እናውቃለን። ይሁን እንጂ በትንሣኤ አማካይነት ሞት ሙሉ ለሙሉ ይወገዳል። በተጨማሪም ሞት ብቻ ሳይሆን፣ ኀጢአትና ከኀጢአት ጋራ ተያይዘው የሚፈጠሩ የትኛውም ዐይነት ስሕተቶችና ድካሞችም ጭምር ተወግደው የትንሣኤን አካል ያገኘው ሰው ድካም የሌለበትና ፍጹም ይሆናል። በዚህም ምክንያት የትንሣኤ አካል ያገኙ ሰዎች በማንነታቸው በሙላት ለእግዚአብሔር ክብር መኖር የሚችሉበትን ሕይወት ያገኛሉ። በሁለተኛ ደረጃ፣ የሞት መወገድ ለሰው ልጆች አካል ቋሚና ቀጣይነት ያለው ፍጹምነት ይሰጣል። በዚህም ምክንያት በሰው ልጅ ማንነት ውስጥ ያለው አንድ ላይ ተጣጥሞ ለእግዚአብሔር ክብር እንዳይኖሩ ያደረጉ ነገሮች በሙሉ ይወገዳሉ። በተጨማሪም ሕመም፣ ሥቃይ፣ ድካም የመሳሰሉና የሰው ልጆችን ሕይወት ያናወጡና አንድ ላይ ተባብረውን አተጣጥመው የላቀ ዐቅም በመገንባት ፍጥረተ ዐለሙ ያወኩ ነገሮች በሙሉ ይወገዳሉ።
ይህ ታላቅ ትንሣኤ በአራት በተለያዩ መንገዶች ተገልጧል። እነዚህም ዘላለማዊ፣ የከበረ ወይም የተሟላ፣ ኀይልና መንፈሳዊ መንፈሳዊ ናቸው (1ቆሮ. 15፥42-44)። የመጀመሪያው፣ የድኅረ ትንሣኤው ሰውነት/አካል ሙሉ በሙሉ በተለጣጭ ነገር ባሕይር (plasticity) ሊገለጥ የሚችል ነው። ይህ አካል ሙሉ ለሙሉ ከመንፈስ በታች የሆነ ነው (1ቆሮ. 14፥44)። ሁለተኛ ይህ የትንሣኤ አካል የተንቀሳቃሽ ነገር ባሕርይ ያለው (agility) ነው። በመሆኑም ይህ አካል በኀይል የተመላና ተንቀሳቃሽ ነው (1ቆሮ. 15፥43)። ሦስተኛው ይህ የትንሣኤ አካል ኢሓማሚ (impassible) ነው። በመሆኑም ይህ አካል ሥቃይና ሕመም የማያጠቃው ነው (1ቆሮ. 15፥42፡52)። አራተኛ ይህ የትንሣኤ አካል አንጻባራቂ (luminosity) ነው። በመሆኑም ይህ አካል እንደ ፀሓይ ያበራል (ማቴ. 13፥43)።[3] እነዚህ ባሕርያት የትንሣኤ አካል የሥጋና የነፍስ ፍጹምነት ያገኘ መሆኑን የሚያመለክቱ ሲሆኑ፣ በተመሳሳይ መልኩም የሰው ልጆች ከአሮጌው ማንነት ወደ ዐዲስ ፍጥረት እንደሚለወጡም የሚያሳዩ ናቸው።
የክርስቶስ ኢየሱስ የራሱን ሰውነት ድንቅ በሆነ መልኩ የመጀመሪያውን መሆን ይችል ዘንድ ማደስ መቻሉ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቃብሩ በተነሣበት ወቅት የራሱን ሙሉ አካላዊ ሰውነት እውነተኛና ፍጹም ወደ ሆነው የራሱ ማንነት የተለወጠበት ቅጽበት ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በተነሣበት ቅጽበት ወደ ዐዲስ ሕይወት እንደተለወጠና በሰማያት በአባቱ ቀኝ በክብር እንደተቀመጥ እናውቃለን። ከዚህ እውነት የምንረዳው ኢየሱስ የገዛ አካሉን በትንሣኤ አማካይነት እንደገና በማደስ ወደ ሰማያዊው የዘላለም ሕይወት መመለሱን ነው። የክርስቶስ ኢየሱስ የትንሣኤ አካሉ በተጨባጭ የሚታይ እንደሆነ ግልጽ ነው። ከሙታን የተነሣው እውነተኛው የኢየሱስ ሥጋው/አካሉ ነው። ወንጌላት፣ ትንሣኤ ያገኘው የክርስቶስ አካል ሙሉ ለሙሉ የታደሰና የተለወጠ ፍጹምና ሙሉእ መሆኑን ነው።
ከዚህ አንጻር ስንረዳ ትንሣኤ ማለት እንደገና መንቃት ወይም ህያው መሆን ማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ትንሣኤን ከፍጥረታዊ አካል (sōma psychikon) ወደ መንፈሳዊ አካል (sōma pneumatikon) መለወጥ እንደሆነ አድርጎ ይገልጻል (1ቆሮ. 15፥35-50)። ይሁን እንጂ የትንሣኤ አካል ማለት ቁሳዊ ያልሆነ፣ ማለትም ያልተፈጠረ ነው ማለት አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ የትንሣኤን አካል ያልተፈጠረና መንፈስ ብቻ አድርጎ አይገልጽም። ጳውሎስ የትንሣኤን አካል ይህ የተፈጠረ ሥጋ/አካል የማይሞትና የማይበሰብስ ሆኖ የተነሣ እንደሆነ ይገልጻል (1ቆሮ. 15፥35-50)።
ዶይለ የተሰኘ ጸሐፊ እንደገለጠው ከሆነ፣ ከሙታን የሚነሣው አካል ለመበስበስ፣ ለድካም፣ ለኀጢአት፣ ወይም ለክፉ ምኞች፣ እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋራ በጠላትነት ለመቆም ታልፎ የማይሰጥ ነው (ገጽ. 48)። ይህ ቁሳዊና የሚታየው አካላችን የመንፈሳዊው አካል ተቃራኒ ቢመስልም፣ መሠረታዊው ችግር ቁሳዊ ሥጋ ወይም አካል መሆን አይደለም። ተፈጥሯዊው ቁሳዊ አካልም ሆነ መንፈሳዊው አካል የተፈጠረና የሚኖረው በእግዚአብሔር ነው። የቁሳዊው አካል መሠረታዊና ዋናው ችግር ከኀጢአት ቁጥጥር በታች መሆኑ ነው።
የክርስቶስ አካላዊ ትንሣኤ ሦስት መገለጫዎች
የክርስቶስ ኢየሱስ የትንሣኤው አካል ምን ይመስል ነበር? የትንሣኤ ኢየሱስ የዐይን ምስክር ከነበሩ የወንጌላት ጻሐፊዎች የምንረዳው፣ የክርስቶስ የትንሣኤ አካል በግልጽ የሚታይ፣ የሚነካና የሚዳሰስ መሆኑን ነው (ማቴ. 28፥9፤ ዮሐ. 20፥27)። በተጨማሪም ሰዎች በትክክል የሚያውቁትና ልዩ ስሜትም የሚፈጥር ነበር። የትንሣኤውን ኢየሱስ የተመለከቱ ሰዎች ክርስቶስ ከትንሣኤው በፊት ከነበረው ይልቅ ከትንሣኤ በኋላ የመደነቅ ስሜት የሚፈጥር ሆኖ ተገልጧል። ከትንሣኤው በፊት ኢየሱስን የሚያውቁ ሰዎች ከትንሣኤው በኋላ ሲመለከቱት በመደነቅና በፍርሀት ተውጠው ወደቀው ሰግደውለት ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ለተከታዮቹ በተለየ መልኩ ነበር የተገለጠላቸው (ማር. 16፥12፤ ባቪንክ፣ 367)። እንዲሁም ደግሞ ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ የነበረው ግልጠቱ ከትንሣኤ በፊት ከነበረው የተለየ ነበር (ሉቃ. 24፥31፤ ዮሐ. 20፥15፡19፤ 21፥7)። አንዳንድ ጊዜ በሚታይ አካል ሲገለጥ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ይሰወር ነበር። አንዳንድ ጊዜ ተከታዮቹ ሲያስተውሉት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ አያስተውሉትም ነበር።
የክርስቶስ የትንሣኤ አካል በሦስት ዋና ዋና ገጽታዎች ተገልጦ ነበር
- ኢመዋቲነት
የክርስቶስ ኢየሱስ አካል ከሙታን የተነሣው ዳግመኛ የማይሞት ሆኖ ነው። ቮስ የተሰኘ የነገረ መለኮት አጥኚ እንደተተው፣ በኀጢአት ምክንያት የተጎሳቆለው፣ ነገር ግን ኀጢአት ያላጎደፈው የክርስቶስ አካላዊ ማንነት በማይሞትና ለዘላለም በሚኖር አካል ከሙታን ተነሥቷል (ቮስ፣ 583)። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በተነሣው አካሉ ሕያው ሆኖ ለዘላለም ይኖራል። በሌላ አነጋገር፣ ይህ የክርስቶስ ኢየሱስ የትንሣኤ አካል በየትኛውም መልኩ ሆነ በምንም ዐይነት መንገድ የሚምትና የሚበሰብስ አይደለም (ሐዋ. 13፥34)። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን እውነት፣ “ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቷልና፣ ዳግመኛ እንደማይሞት እናውቃለን፤ ሞት ከእንግዲህ በእርሱ ላይ ጕልበት አይኖረውም” በማለት አጽንቷል (ሮሜ 6፥9)። በተጨማሪም ጳውሎስ፣ “ታዲያ የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፣ እንዲሁም ከሞት የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እኛ ይማልዳል” ይላል (ሮሜ 8፥34)።
በዚህ መንገድ ስንረዳ የክርስቶስ ትንሣኤ በርግጠኝነት የሞቱ ተቃራኒ የሆነ እውነት ያሳያል ማለት ነው። በተጨማሪም ትንሣኤው አጠቃላይ ሰብአዊ ተሓድሶ ያካተተ ነው። አጠቀላይ ሰብአዊ ተሓድሶ ሲባል አካላዊና መንፈሳዊውን፣ ውጫዊና ውስጣዊውን እንዲሁም ከመሞቱ በፊትም ሆነ በኋላ ያለውን ከሞት ነጻ የሆነ ማንነቱን የሚያተቃልልና ዘላለማዊነት ያለው ሕይወት ማለት ነው። ስለዚህም ነው ዋርፊልድ የተሰኘ ጽሐፊ ይህን እውነት፣ የሞተውና ከሙታን የተነሣው ክርስቶስ ፍጹም ሰብአዊነቱ ለዘላለም እንደሚኖር የሚገልጠው ትምህርት በክርስትና አስተምህሮ ውስጥ መሠረታዊውን ስፍራ ሊይዝ የተገባ ነው በማለት የሚገልጠው (ገጽ. 544)።
የትንሣኤ ኢየሱስ አካል ኢመዋቲ የመሆኑን እውነት ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “ም” በማለት ይገልጣል (1ጢሞ. 6፥16)። በተጨማሪም ጳውሎስ የአማኞች ትንሣኤ ከክርስቶስ ትንሣኤ ጋራ ተመሳሳይ እንደሆነ ይገልጣል (1ቆሮ. 15፥53-54)። በመሆኑም አማኞችም ጭምር ልክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ የማይሞትና የማይበሰብስ አካል ይዘው ይነሣሉ። በመሆኑም ትንሣኤ ማለት ከሞት ኀይልና ቁጥጥር ውጪ መሆን ማለት ነው።
- ልእለ ኀያልነት
ክርስቶስ በትንሣኤው እጅግ የላቀ ችሎታ አግኝቷል። ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ ጌታና ንጉሥ ሆኖ አሁን መታየት ይችላል። በርግጥ ርሱ በግልጽ የሚዳሰስ፣ የሚሰማና የሚናገር ሆኖ ተገልጧል። ሥጋና አጥንት፣ እጅና እግር፣ ምላስና ጥርስ፣ አንገትና እግር ያለው ሙሉ ሰው ሲሆን፣ የምግብ ፍላጎትና የዕውቀት ዐቅም እንዲሁም የራሱ ፈቃድ ያለው ሰው ሆኖ ተገልጦ ነበር (ሉቃ. 24፥39-43)። እንዲሁም ከሌልች ጋራ የነበረው ግንኙነት ግልጽና የተለመደው ዐይነት ነው። በሚያደርጋቸው ነገሮች በሙሉ እንደ ሰው ተንቀሳቅሷል፤ የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ እሳት አንድዶ ምግብ የሚያበስል፣ የሚቀመጥና የሚራመድ ሰው ነበር። ስለዚህም ተከታዮቹ ከሞት ከተነሣው ኢየሱስ ጋራ ጥሩ የሚሆነ ተግባቦትና ኀብረት ያደርጒ ነበር።
ይሁን እንጂ ደግሞ የክርስቶስ የትንሣኤ አካል፣ በባሕርዩ ከትንሣኤው በፊት ከነበረው አካል ይለይ ነበር። ይህ የትንሣኤ አካል በተለያዩ አደጋዎች፣ ወይም በበሽታ ወይም በተፈጥሯዊ መንገድ ሞቶ ከሙታን የነቃ፣ ወይም ያገገመ ሳይሆን፣ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ከቶ የማይይዘው ሆኖ የተነሣና የሞትን ኀይል የተሻገረ አካል ነው።
ይህ ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ በጊዜው የዐይን ምስክር ሆነው የተመለከቱና ከርሱ ጋራ ኀብረት ያደረጒ ሁሉ በሚያቁት መልኩ በተገለጠበት ሁኔታ በመኖር የሚቀጥል ነው። አንቶን ቲሰልተን የተሰኘ ምሁር ይህን እውነት፣ “ከሌሎቻችን ሁሉ የተለየና የሚቃረን ባሕርይ ያለው ነው” በማለት ገልጦ ነበር (2015፡394)። የዐይን ምስክር የሆኑ የወንጌላት ጻሐፊዎች እንደገለጡልን ከሆነ፣ የክርስቶስ የትንሣኤው አካል ለሰዎች ፊት ለፊት የሚታይ ቢሆንም፣ ወዲያው ደግሞ ከዐይናቸው ፊት የሚሰወር ነበር (ማቴ. 28፥9፤ ሉቃ. 24፥31 3ና 36)። በተጨማሪም የትንሣኤ ክርስቶስ አዲስና እንግዳ ሰው ሳይሆን፣ ከዚህ በፊት የሚያውቁት ሁሉ የሚለዩትና የሚያስተውሉት ነበር (ሉቃ. 24፥16፤ ዮሐ. 20፥14)። እንዲሁም ደግሞ ይህ የትንሣኤ አካል በግልጽ ሥሠራ ታይቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ በፍርሀት ተወጠው ደጆችን ዘግተው በተቀመጡበት በተዘጋ ቤት ዐልፎ በመግባት ሰላምን አውጆላቸው ነበር (ዮሐ. 20፥19)። ስለዚህም ይህ የትንሣኤ አካል ከትንሣኤ በፊት እንደነበረው አካል ቁሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊ አካል ነው። ይህ አዲሱ መንፈሳዊ አካል ደግሞ በልዩ ኀይል፣ ችሎታና ሥልጣን ታላላቅ ድንቆችን ሠርቷል። የክርስቶስ ኢየሱስ የትንሣኤ አካል በየትኛውም መልኩ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ ነበር (ባቪንክ፣ 367-371)።
ይህ የክርስቶስ ትንሣኤ የፈረሰውን ዳግመኛ ከመገንባትና ጠጋግኖ ከመሥራት ያለፈ እውነት የያዘ ሲሆን፣ በጥልቀትም ሆነ በስፋት የሰዎችን የሚታይና የማይታይ ማንነት ባጠቃለለ መልኩ ሕይወትን ለእግዚአብሔር መንግሥት ተስማሚ የሚያደርግ ፍጹማዊ የሕይወት ለውጥ ነው። ይህ የሚታየው አካል በመኖር ይቀጥላል። ነገር ግን ይህ አካል በመኖር የሚቀጥለው አሁን ባለው መልኩ ሳይሆን፣ ልንግምተውም ሆነ ልናስበው በማይቻል መልኩ ነው (1ቆሮ. 15፥51-52)። ይህ ዐይነቱ የትንሣኤ አካል፣ በእግዚአብሔር መንፈስ የተመላና ታላቅ ችሎታና ዐቅም ያለው ነው። ለምሳሌ፦ ኢየሱስና ጴጥሮስ በውሃ ላይ መራመድ ችለዋል (ማቴ. 14፥29)። በተመሳሳይ መልኩም፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ በእቶኑ እሳት ውስጥ ቢጣሉም እሳቱ ሊጎዳቸው አልቻለም ነበር (ዳን. 3)። የእግዚአብሔር እጅ ከርሱ ጋራ ስለ ነበረች፣ ኤልያስ በሰረገላ ተቀምጦ ከሚነዳው አክአብ በላቀ ፍጥነት ሊሮጥ ችሏል (1ነገ. 18፤46)። ሙሴ ለስምንት ሳምንታት ያህል ያለ ምግብና ውሃ ሊቆይ ችሏል (ዘፀ. 34፥28)። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ቋንቋ፣ ትንሣኤ ማለት ከእግዚአብሔር የሚሰጠውን ኀይል ተቀብሎ በዐዲስ የእግዚአብሔር ፍጥረት ዓለም ውስጥ ተስማሚ እንዲሆንና አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ ሕይወት ማለት ነው።
- ልዩ ግላዊ ማንነት
ኢየሱስ ከሙታን በተነሣበት ወቅት የራሱን ማንነት እንደ ልዩ ግለሰብ የተገነዘበበይ ሁኔታ ነበር። በትንሣኤው ጊዜ ለመረዳት አስቸጋሪና ግራ የሚያጋባ ሁኔታ አተስተውሎ ነበር። የክርስቶስ የትንሣኤ አካል የቀድሞው ዐይነት አልነበረም። የላቀ ክብር ያለውና የማይሞት አካል ሆኖ ነበር የተነሣው። ይሁን እንጂ ደግሞ ሌላ አካል ሳይሆን፣ የቀድሞው አካል ራሱ ነበር። በሌላ አነጋገር የትንሣኤ አካል የቀድሞው ራሱ ቢሆን፣ ሌላ ዐይነት ነበር። የትንሣኤው ኢየሱስ ራሱ የቀድሞው እንደሆነ ለተከታዮቹ በተገለጡ ጊዜያት ተረጋግጦ ነበር። የትንሣኤው ማንነት ከቀደመው ማንነቱ ጋራ ሙሉ ለሙሉ አንድ እንደሆነ መናገር ባይቻልም፣ የትንሣኤ አካል ይዞ በክብር የተነሣው ግን የቀደመው ማንነቱ ራሱ ነው። አሮጌው ማንነት የተገለጠው በዐዲስ የትንሣኤ አካል ነው። አሮጌው ማንነት በተለወጠ ዐዲስ ፍጥረት መልክ ተገለጠ እንጂ ሙሉ ለሙሉ ተደምስሶ አልጠፋም። ከሙታን የተነሣው የቀደመው የሞተው አካሉ እንጂ ሌላ አልነበረም።
የትንሣኤው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በታየ ጊዜ፣ “እኔ ራሴ እንደሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ” በማለት ተናግሮ ነበር (ሉቃ. 24፥39_40)። ይህም እውነት የትንሣኤው ኢየሱስ ከትንሣኤ በፊት የነበረው ራሱ እንደሆነ ያረጋግጣል። ከሙታን የተነሣው አካል የቀድሞው እንደሆነ በእጆቹና በእግሮቹ የተነበሩ ምልክቶችና ጠባሳዎች ያረጋግጣሉ (ዮሐ. 20፥20፡27)።
በዚህ ጒዳይ ላይ የነገረ መለኮት ምሁሩ ዋይን ግሩደም፣ “ከከባድ የመስቀል ላይ ሥቃይና ግርፋቱ የተነሣ በክርስቶስ ሰውነት ላይ የደረሱ ቁስሎች በሙሉ ድነዋል። ነገር ግን በእጁ፣ በእግሩና በጎኑ የነበሩ ጠባሳዎች ግን ለእኛ የሞቱ ምስክር መሆን ይችሉ ዘንድ ጠባሳ ሆነው ቀርተዋል” የሚል ድንቅ ሐሳብ ይሰነዝራል (2020፡757 n. 11)። ኢየሱስ በትንሣኤው የከበረውና በኀይል ከፍ ከፍ ያለው በዚያ በቀደመው አካሉ ነው። ርሱ፣ በዚያ አካሉ ከነፍሱ ጋራ በአንድነት ሕያው ሊሆን ችሏል። በሌላ አነጋገር የተለወጠና የከበረ አካል ሆኖ ከሙታን የተነሣው ከማሪያው የተገኘው የቀድሞው አካል ራሱ እንጂ ሌላ አይደለም። ይህን እውነት ቮስ፣ “ክርስቶስ ከትንሣኤው በፊት የሞትን ዘር በውስጡ የተሸከመ ደካማ ሥጋ ነበር። በተቃራኒው ግን ከትንሣኤው በኋላ፣ ሰብአዊው ባሕርይ መንፈሳዊውን ተካፍሏል። በሌላ አነጋገር፣ ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ሙሉ ለሙሉ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሉል። በዚህም ምክንያት የትንሣኤ አካል የማይሞትና የማይበሰብስ ዘላለማዊ ሊሆን ችሏል። ከሞቱ በፊት በአካሉ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ብዙ መከራ የተቀበለ ቢሆንም፣ ከትንሣኤው በኋላ ግን ክብርና ማእረግን ተጎናጽፏል። በመሆኑም ቊሳዊና ወይም አካላዊ መባሉ ባይቀርም፣ ሥጋና ደም መባሉ ግን ቀርቷል” በማለት ይገልጣል።
[1] Thomas Schreiner, New Testament Theology (Baker, 2008), 427.
[2] Brakel, The Christian’s Reasonable Service, 1:625.
[3] Oden, Systematic Theolgy, 2:481-82
ምዕራፍ 6
ትንሳኤ ሁሉን ቻይነትን መሰረት ያደረገ ነው
የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በርሱ በማመን የሚገኝ ድነት እውነት ማእከላዊ ስፍራ ይይዛል
የክርስቶስ ትንሣኤ የእምነታችንን ቁልፍ ስፍራ ይይዛል። በክርስቶስ ትንሣኤ ሞት ማመናችን በእግዚአብሔር መታመናችንና በርሱ መተማመናችንን የሚያረጋግጥ ልዩ መገለጫ ነው። ያለ ክርስቶስ ትንሣኤ ክርስቲያናዊ ትምህርቶች ምንነትና ትርጒም አይኖራቸውም። ክርስቶስንም ሆነ የአማኝን ተስፋ ያለ ኢየሱስ አካላዊ ትንሣኤ ለማወጅ መጣር፣ የእምነትን መሠረታዊ እውነት ወደ ሚንድ ደረጃ የሚያደርስ ነገር ነው (1ቆሮ. 15፥12-13፤ 47-49)። የክርስቶስ ወንጌል የሞቱና የትንሣኤው ወንጌል ነው። ምክንያቱ ደግሞ የክርስቶስ ወንጌል ከሰው ልጆች ሁሉ ጋራ የተቆራኘ ስለሆነ ነው። በተመሳሳይ አመክንዮ ተከትለን በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የሰለጠነው ኀጢአትና ሞት የአዳም ኀጢአትና ሞት ውጤት እንደሆነ መሟገት እንችላለን (1ቆሮ. 15፥17-23፤ 47-49)። በመሆኑም የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ወንጌል የሆነው የክርስቶስ ወንጌል፣ ከሰው ልጆች ሁሉ ትንሣኤ ጋራ በቀጥታ የተገናኘ ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ የወንጌል ማእከላዊ እውነት ብቻ ሳይሆን፣ የክርስቶስ ትንሣኤ ጒዳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ውስጥ ትልቁን ስፍራ ይይዛል። ይህ የሆነበት ምክንያት ሰዎች ከኀጢአታቸው በንስሓ ተመልሰው ድነት የሚያገኙት መሠረታዊ እውነት የክርስቶስ ትንሣኤ ስለሆነ ነው (ሮሜ 10፥9)።
የክርስቶስ ኢየሱስን ሞትና ትንሣኤ ለማመን አስቸጋሪ ሁኔታዎች
የክርስቶስ ትንሣኤ ማለት እስከ ሞት ድረስ ቆስሎና ተጎድቶ የነበረው ሰውነቱ ወይም ሬሳ ወደ ቀደመው ሕይወት መመለስ ማለት አይደለም። ወይም ደግሞ ሞቶና በስብሶ ከጥቅም ውጪ የሆነው የእኛ ሰውነት እንደገና ወደ ሕያውነት ይመለሳል ማለትም አይደለም። የትንሣኤን እውነት ለመቀበል አስቸጋሪ ካደረጒ ነገሮች አንዱ በከፍል ከዕለት ዕለት የሕይወታችን ተመክሮ እጅጒን የላቀ መሆኑ ሲሆን፣ በከፍል ደግሞ በታሪክ ውስጥ አሁን እኛ ካለንበት ዘመን እጅግ ርቆ ከረጅም ዘመን በፊት የተከናወነ ክሥተት መሆኑ ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ የተከናወነ ጊዜ ማናችንም በዚያ አልነበርንም። በተጨማሪም በዓለም ፍጻሜ ሊሆን ስላለው አጠቃላይ የሙታን ትንሣኤ ምልክት ሊሆን የሚችል ነገር አልታየም ነበር። ስለዚህም ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስፈላጊነት አጋኖ መናገር ከባድ ጒዳይ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ስያስተምር አንዳንዶች ቢያምኑበትም ሌሎች ግን ይቃወሙት ነበር (ሐዋ. 17፥18፡30-32)። በመሆኑም ከክርስቶስ ትንሣኤ፣ እንዲሁም ሙታን በአካል እንደሚነሡ ከምናምነው ከእኛ የእምነት አቋም ጋራ ተያይዞ የሚነሣው ጥያቄ ሞት ግልጽ በሆነ ሁኔታ በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው ከመሆኑ ጋራ የሚቆራኝ ነው። ሞት ማንም ሊያስቆመው ወይም ሊያስወግደው የማይችል ኀይል ነው። በተጨማሪም የሞት ሰው በየትኛውም መልኩ ተጠጋግኖ ሕያው ሊሆን አይችልም። የትኛውም ሰው ያለውን ዐቅም በሙሉ ተጠቅሞም ሆነ፣ ንብረትና ሀብት በሙሉ ከፍሎ ሞን ሊያስቆም ወይም የሞቱ ቀጠሮውን ሊያስለውጥ አይችልም። ስለዚህም የሰዎች ከሙታን የመነሣት ጒዳይ ከተጨባጭ የሰዎች ተመክሮ ጋራ የሚጋጭ ይመስላል። ለሰው ልጆች ሞት እጅግ አሳዛኝ፣ አስጨናቂና በርካቶችን ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። በተጨማሪም ሞትን ተከትሎ የሚመጣው መበስበስ ከባድ የውስጥና የልብ ስብራት የሚያስከትል ክሥተት ነው። ማርቲን ሉተር፣ “ዓለም ሁሉ በሞት ተጠራርጎ ሲወሰድ ዐይኖቻችን ያያሉ” በማለት ገልጾ ነበር (2፡493)።
በጥንትም ሆነ በአሁኑ ዘመን ያሉ በርካታ ሃይማኖቶች በአንድም ሆነ በሌላ መልክ ከሞት በኋላ ሕይወት እንደሚኖር ይጠብቃሉ ወይም ተስፋ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ የእነዚህ ሃይማኖቶች እምነት ሥጋ ሳይሆን ነፍስ እንደማትሞትና ለዘላለም እንደሚትኖር የሚያወሳ ነው። እንደ ነዚህ ሃይማኖቶች እምነት ከሆነ ሥጋ ሞቶና በስብሶ ሲቀር ነፍስ ወይም መንፈስ ለዘላለም በመኖር ትቀጥላለች። ለምሳሌ፦ የጥንታዊ ግሪክ ፍልስፍና ኢመዋቲነትን የመንፈስ ከሥጋ መለቀቅ አድርጎ ይገነዘብ ነበር። እንዲሁም የጥንት ይሁዲ እምነትም ሆነ የእስልምና እምነት ከሞት በኋላ ቀጥላል በማለት የሚያኑትን ሕይወት እንደ አካላዊ ሙታን ትንሣኤ ወይም ከኀጢአትና ከርኩሰት መዳን ወይም ነጻ መውጣት አድርገው ይረዳሉ።
ዋይት እንደተባለ ጸሐፊ ገለጻ ከሆነ፣ አብዛኞቹ የዘመናችን ሰዎች ከሙታን ትንሣኤ ይልቅ አለመሞትን እንደሚመርጡ
ዘመናዊ ሰዎች፥ ጥንታዊው የትንሣኤ ሐሳብ ተቃራኒውን እንደሚያጸና ሳይገነዘቡ በመቅረታቸው ምክንያት ከአካላዊ ትንሣኤ ይልቅ የነፍስ ኢመዋትነትን ሊመርጡ ይችላሉ። ዘላለማዊነት አንዲሁ ረቂቅ ማንነትና የሕይወት እሴት ሳይሆን፥ ህልው፣ ኅብረታዊ፣ ትውስታ ያለውና የሚያፈቅር ነው፤ ይህ እውነት ደግሞ በዘላለም ባሕር ውስጥ ጠብታ ሆኖ መቀላቀልን ከሚያወሳው ንድፈ ሐሳቦች ሁሉ፣ እንዲሁም የላቀ ነው። በተጨማሪም ይህ እውነት የሕይወትን ትግል አሸንፎ በመኖር ከመቀጠል፣ ወይም ሞቶም ቢሆን ሕያው በሆኑ ሰዎች ልብ ውስጥ በመኖር ከመቀጠል ያለፈ ነው
በማለት ግለጿል።[1]
እውነተኛውን የክርስቲያኖች እምነት በተመለከተ ልናውቀው የሚገባው ነገር፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በትክክል የሚገልጠው ከሙታን ሕያው ሆኖ የተነሣው ማንነቱ መሆኑን ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአካል ከሙታን በመነሣቱ ምክንያት፣ ከክርስትና እምነት በስተቀር ሌሎች አመለካከቶች በሙሉ እምነት የሚጣልባቸው አይደሉም።
ይሁን እንጂ ስለ ክርስቶስ በአካል ከሙታን መነሣት የሚያወሳው እንዲህ ዐይነቱ እውነት፥ ከክርስትናው እምነት ውጪ ባሉ በሌሎች አስተሳሰብ የማይታመን ነው። በአይሁዶች ሃይማኖትና በእስልምና እምነት እንዲሁም በክርስትናው፥ የሙታን ትንሣኤ ጒዳይ የሚታመን ነገር ቢኾንም፥ የይሁዲ እምነትና እስልምና ግን በክርስቶስ ትንሣኤ አያምኑም። ይህ እውነት ደግሞ በክርስትናው እምነት ስለ ክርስቶስ ከሙታን መነሣት የተያዘውን ጽኑ እምነት አከራካሪ ያደርገዋል። በተጨማሪም፥ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ የተነሣ በመጨረሻም የሰው ልጆች በሙሉ ከሙታን ይነሣሉ የሚለው እውነት ከፍልስፍና፣ ከሳይንሳዊና ከሌሎች የተለያዩ ሃይማቶች አመለካከት ጋራ የሚጋጭ ነው። እንዲሁም ደግሞ እጅግ ተወዳጅ የሆነውና ክብር ያለበት ይህ የትንሣኤ ትምህርት ባለፉት ዘመናትም ሆነ በአሁኑ ዘመን ካሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እምነቶችና አስተሳሰቦች ጋራ የሚስማማ አይደለም።
ስለዚህም የክርስቶስ ትንሣኤ ትምህርት በክርስትናው እምነትና በሌሎች ሃይማኖቶችና ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦች መካከል መሠረታዊ ልዩነት የሚፈጥር ጒዳይ ነው። በዚህም ምክንያት የክርስትና እምነት የሚያስተምገረው ይህ የክርስቶስ ትንሣኤ ትምህርት ከሌሎች ሃይማኖቶችና ፍልስፍና ትምህርቶችና አስተሳሰቦች የተለየ የሆነው። በየዘመናቱ የሚነሡ ሃይማኖታዊና ፍልስፍናዊ ትምህርቶች ራሳቸውን ሙሉ አድርገው ስለሚያዩ ከክርስትናው የክርስቶስ ትንሣኤ ትምህርት ጋራ ተቃራኒ ሆነው እናገኛቸዋለን።
በክርስቶስ ትንሣኤ ማመን፥ እምነትን በእግዚአብሔር ላይ መጣል ነው
በክርስቶስ ትንሣኤ ማመን የምርጫ ጒዳይ አይደለም። የክርስቶስ ትንሣኤ በግልጽ በሚታወቅ ጊዜና ስፍራ በበርካታ ምስክሮች ፊት የተከናወነ ታሪካዊ ሃቅ ሲሆን፥ ሰፊ ማስረጃ ያለውን እውነት ነው። ስለዚህም በትንሣኤው ማመን በእግዚአብሔር መኖርና በተፈጥሮ እውነትነት ላይ መሠረታዊ እምነት የሚጠይቅ ነገር ነው። ይህን እውነት ዎልሃርት ፓንነበርግ የተሰኘ ምሁር፥
የኢየሱስን ትንሣኤ ታሪካዊ እውነትነት በተመለከተ አጠቃላይ ውሳኔያችን ወይም የምንሰጠው ፍርድ ልዩ ልዩ ተያያዥ ሁኔታዎችን አይተንና አገናዝበን የምንሰጠው ውሳኔ ብቻ ሊሆን አይገባም። ነገር ግን ብዙ ጉዳዮችን በጥልቀት ከመፈተናችንና ከመገምገማችን በፊት፣ የነገሩን እውነትነት በሚገባ በመረዳት በዚያ ላይ ተመሠረተ ጉዳይ ሊሆን ይገባል። ይህንንም በተመለከተ ጳውሎስ፣ “ትንሣኤ ሙታን ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው” በማለት እንደሞተገው፣ እኛም በክርስቶስ ትንሣኤ ካላመንን ምንም ያህል ጠንካራ ማስረጀ ለማቅረብ ብንሞክር እምነታችን ከንቱ ነው (1ቆሮ. 15፥17)
በማለት ነበር ያብራራው (1994፡2:362)።
እምነት ያለ ክርስቶስ ትንሣኤ ከማንኛውም የሰው ልጆች ፍልስፍና እና አመለካከት የተለየ ትምህርት ሊሆን አይችልም። ስለዚህም በክርስቶስ ትንሣኤ ማመን ራሱን ችሎ እንደ ንጽረተ ዓለም ይሠራል። ሆኖም፥ እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሙታን እንዳስነሣው ማመን በጣም ያልተለመደ፣ በጣም መለኪያ የሌለው፣ በጣም ክሥተታዊ፣ እጅግ ወሳኝና አይጨበጤ ነው (በተለይም ደግሞ አጠቃላይ ትንሣኤንና ሊመጣ ያለውን የመጨረሻውን ፍርድ በተመለከተ)። በመሆኑም በዚህ እውነት ማመን በመሠረታዊነት መለኪያ በሌለው የእግዚአብሔር ኀይልና ብርታት እንዲሁም በርሱ የመፍጠር ችሎታ መታመን ነው። ይህም ማለት በአጭሩ በእግዚአብሔርና በተስፋዎቹ ማመንን ይጠይቃል። ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ የቱንም ያህል ጠንካራ መስረጃዎችን በማቅረብ አጥብቆ መሟገት፥ እምነትን ርግጠኛና ሙሉ ሉያደርግ ይችላል እንጂ በሰዎች ውስጥ እምነትን ሊፈጥር አይችልም።
እርሱ በዓለም ላይ ካለው ድርጊትና ግልጠት ጋራ ተያይዞ ያለው የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት
ካልቪን እንዳለው በክርስቶስ አካላዊ ትንሣኤ ማመን በሁለት ነገሮች ላይ ይደገፋል፥ የመጀመሪያው በክርስቶስ ትንሣኤ እውነትነትና በግልጽ ለሰዎችም መታየቱን ማመን ሲሆን፥ ሁለተኛ ደግሞ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ማመን ነው (3.25.3-4፡990, 993-94)። ከዚህ በታች ባሉት ክፍሎች ውስጥ በምናደርጋቸው ውይይቶች የክርስቶስ ትንሣኤ በግልጽ ለሰዎች ሁሉ የታየ እውነት መሆኑንና ስለ ትንሣኤው የተነገሩ ታሪካዊ እውነቶችን እንመለከታለን። ከሁሉ በፊት ግን መረዳት ያለብን እውነት ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ በቂ ማብራሪያ ሊሆን የሚችል ተፈጥሯዊም ሆነ ሰዋዊ ዕውቀት እንደሌለ ነው። በሌላ አነጋገር፥ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣ እግዚአብሔር ስለሆነ የክርስቶስን ትንሣኤ ከእግዚአብሔር ለይተን ለመረዳት የምንጥር ከሆነ ግልጽ ልሆንልን አይችልም። በመሆኑም በአጭሩ፥ ክርስቶስን ከሙታን ሊያስነሣ የቻለው የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት ስለሆነ ጒዳዩ ጥልቅ ምስጢር ነው ማለት ነው።
እግዚአብሔር ከፈጠረው ዓለም ጋራ ኅብረት በማድረግ መቀጠሉን ከሚገልጡ ነገሮች አንዱ ሥራውና ራሱን ለሕዝቡ የገለጠበት መንገድ ነው። አጽናፈ ዓለሙን የፈጠረው አምላክ ርሱ በመግቦቱ አጽንቶ ያቆማል፤ ይመራል፤ ይጠብቃል፤ ያስተዳድራል፤ እንዲሁም ለህልውናው የሚያስፈልገውን ሁሉ ያቀርባል። በዚህ መልኩ ሥራውን መሥራቱ ርሱ ፍጥረተ ዓለሙና በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ያለውን ዘላለማዊ ኀይሉንና መለኮታዊ በሕርዩን በግልጽ ያሳያል (ሮሜ 1፥19-20)። መላለው ከእግዚአብሔር መላኮታዊ አገዛዝ በታች ነው፤ ርሱ የሁሉ ፈጣሪና እውነትን ሁሉ የመግለጥ ኀይል ያለው አምላክ ነው።
ምድር ከፈጠራች አምላክ ከእግዚአብሔር የተሰወረች አይደለችም፤ ሥራዎቿም ከዕይታው ውጪ አይደሉም። መላለሙ ከእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ውጪ እንዳልሆነችና በውስጧ የሚከናወኑ ነገሮች ሂደትና ውጤትም ምን ዐይነት መሆን እንዳለበት መፍቀድና መወሰንም የርሱ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፥ “ርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በርሱ ነው” ይላል (ቈላ. 1፥17)።
ተኣምራቱና አሻራዎቹ
እግዚአብሔር እንደ ፈጣሪ አምላክነቱ ሁሉንም ነገር አስቀድሞ በየቦታው እንዳስቀመጠውና እንደወሰነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ሲሆን፥ ርሱ በታሪክ የሠራቸው ያልተለመዱ ተኣምራቶች ደግሞ ይህን ያጸኑልናል። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ የሠራቸውንና የጊዜና እግዚአብሔር አስቀድሞ ፍጥረት ውስጥ ያስቀመጣቸውን የተፈጥሮ ሕጎችን ወደ ጎን ያደረጉ ድንቅ ነገሮችን ስለማድረጉ ይነግረናል። እነዚህ ነገሮች ተኣምራት ናቸው። እግዚአብሔር በታሪክ ከሠራቸው ግልጽና ወደር ከማይገኝለት ተኣምራዊ ሥራዎች አንዱ የክርስቶስ ትንሣኤ ነው። ትንሣኤ እንዴት ሊሆን ቻለ? ተብሎ ቢጠየቅ፥ ከተለመደው የተፈጥሮ ሂደት ውጪ በመሆኑ ምክንያት እንዲህና እንዲያ ነው ብሎ ማብራራት አይቻልም። ይህ ክሥተት በእግዚአብሔር መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የተፈጸመ እጅግ ወሳኝ ነው። በክርስቶስ ትንሣኤ ማንም ሊቋቋመው የማይችል የእግዚአብሔር መለኮታዊ ኀይልና ሥልጣን ተገልጧል። ትንሣኤ የእግዚአብሔርን ተኣምራት ምንነት በግልጽ ማሳየት ችሏል። በሌላ አባባል፥ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እንደሰፈሩ እንደሌሎች ተኣምራቶች ሁሉ፥ የክርስቶስ ትንሣኤም እግዚአብሔር የፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ ባለቤት፣ በማዳንም ሆነ በመፍረድ ኀይሉ ታላቅና ተኣምረኛ ባለሥልጣን መሆኑን ያሳየናል። በተለይም ከሁሉም ነገር በላይ የክርስቶስ ትንሣኤ ስለ ክርስቶስ መለኮታዊ ማንነት ሙሉ ዕውቅና የሚሰጥ፣ ጠንካራና ግልጽ የእግዚአብሔር ኀይል ማረጋገጫ ማኅተም መሆኑን መገንዘብ አለብን። ይህ እውነት ስዊንበርን የተሰኘ ጸሐፊ፥ “የክርስቶስ ትንሣኤ በሕይወቱና በአገልግሎቱ ላይ እንዳረፈበት ማረጋገጫ ማኀተም ወይም አሻራ ሊታይ ይገባል” በማለት ገልጾ ነበር (123)።
ወሰን የለሽ የእግዚአብሔር ኀይል ማለት ርሱ የወደደውን የትኛውንም ነገር ያደርጋል ማለት ነው
እንደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ገለጻ ከሆነ፥ የትኛውንም ዐይነት ትንሣኤ መጠራጠርና እውነቱን መካድ የሚመነጨው የእግዚአብሔርን ኀይልና ሁሉን ቻይነቱን ካለመረዳት ነው። ኢየሱስ ትንሣኤ ለሚክዱ ሳዱቃውያን፥ “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል አታውቁምና ትስታላችሁ” ነበር ያላቸው (ማር. 12፥24)።
ለዚህ እውነት የምንረዳው ሙታንን የማስነሣት ኀይልና ሥልጣን ያለው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ነው። የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት የርሱን ወሰን የለሽ ኀይል ይገልጣል። ሁሉን ቻይነቱ ርሱ በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ብቸኛ ኀያልና ተጽእኖ ፈጣሪ አምላክ መሆኑን ነው። የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት ማለት፥ ርሱ በአጽናፈ ዓለሙ ላይ ማድረግ የሚፈልገውን ነገር በሙሉ ማድረግ ይችላል ማለት ነው። ስለዚህም ሐሳቡንና የሚከለክልና ፈቃዱን የሚያግድ ማንም፣ ምንም የለም። ርሱ ፈቃዱን ያለ ምንም ፈተና ወይም በየትኛውም ዐይነት የችሎታ እጥረት ይተገብራል። ሁሉን ቻይነት ማለት የእግዚአብሔር ዕውቀት ገደብ የለሽ ነው ማለት ነው፤ የትኛውም ተገዳዳሪ ኀይል አያስቆመውም፤ የትኛውንም ዐይነት ዛቻ አይፈራም፤ የትኛውም ዐይነት ስጋት አያሠቃየውም።
ከሰው ልጆች ችሎታና ኀይል በተቃራኒ የእግዚአብሔር ኀይልና ችሎታ ወሳኝ በሆኑ የታሪክ ክሥተቶች ተገልጧል። ለእግዚአብሔር የሚሳነም ምንም ነገር የለም (ዘፍ. 18፥14፤ ኤር. 32፥17)። በመሆኑም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉም ነገር ይቻላል” ያለው (ማቴ. 19፥16)። እግዚአብሔር እንዲደረግ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ይደረጋል፤ የርሱ ዓላማና ፈቃድ ከግብ ይደርሳል፤ ማንም ሊያደናቅፈው አይችልም። እግዚአብሔር በኀይሉ፣ በጒልበቱና በችሎታው እጅግ የላቀ አምላክ በመሆኑ፥ ያለ ምንም ከልካይና እንቅፋት ማድረግ የሚፈልገውንና የሚያስደስተውን ነገር ሁሉ ያደርጋል (መዝ. 115፥3)።
ከእግዚአብሔር ዕይታ አንጻር፥ የተፈጥሮ ሕጎች በራሳቸው የላቁ ግቦች ሳይኑ የእግዚአብሔር ዓላማ ፈጻሚ መሣሪያዎች ናቸው። ህልው ሆኖ ያለው እያንዳንዱ ነገር ድርጊት አስከሣች በሆነው የእግዚአብሔር ኀይል አማካይነት የሚሠራ ነው። በቋሚነት የሚሠሩ ተለምዷዊ ክሥተቶች ጭምር ከመጀመሪያው ጀምሮ በዚያ መልኩ እንዲሠሩ ባዋቀረው አምላክ መግቦታዊ ኀይል የሚሠሩ ናቸው። በምድር ላይ እንዴት ሊፈጸሙ ቻሉ? እና ምን ዐይነት ነገር ተፈጸመ? የሚበሉ ነገሮች ሳይቀሩ የሚወሰኑት በሁሉን ቻዩ አምላክ በእግዚአብሔር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ እውነት፥ “አቤት፣ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሰማያትንና ምድርን በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ፈጥረሃል፤ የሚሳንህም አንዳች ነገር የለም” በማለት ይገልጣል (ኤር. 32፥17)። ዋናውና መሠረታዊው እውነት፥ እግዚአብሔር ኀያል አምላክ እንደመሆኑ መጠን፥ ኀይልና ችሎታው ከራሱ ማንነት ውጪ በሆነ በየትኛውም ነገር የተወሰነ እና የተገደበ አይደለም የሚል ነው።
እግዚአብሔር ከራሱ ተፈጥሮ ጋራ የሚቃረንና የሚቃወም አንዳችም ነገር አይፈጽምም። ርሱ የሚሠራውን ነገር በሙሉ የሚሠራው ከባሕርያቱ ጋራ በሚስማማ መንገድ ነው። ርሱ በሥራዎቹና በዕቅዶቹ ሁል ጊዜም መልካም ነው። ከእኛ ተመልክሮ አንጻር ሲታዩ ክሥተቶች ተለምዷዊ በሆኑ ቢመስሉም፥ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ሕግ ተከትለው ወጥ በሆነ መንገድ ይጓዛሉ። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በፍጥረት ሁሉ ላይ ሉዓላዊና ፈጣሪ አምላክ እንደመሆኑ መጠን፥ ያለ ምንም ካልካይ እንደ ፈቃዱ ምክር ጣልቃ ገብቶ ተኣምራዊ አሻራውን ያሳርፍበታል (ሲዊንበርን፡123)።
ፍጥረትና ትንሣኤ ለእግዚአብሔር ተመሳሳይ ውጤት አምጪ ናቸው
እግዚአብሔር ከምንም ፍጥረትን የፈጠረበት መንገድና ትንሣኤ በአሠራራቸው ተመሳሳይ ክሥተቶች መሆናቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት እንችላለን። እነዚህ ሁለቱ ክሥተቶች፥ ለሙታን ሕይወትን በሚሰጥና ያልነበረውንም እንደ ነበረ በሚያደርግ እግዚአብሔር የተፈጸሙ ናቸው (ሮሜ 4፥17)። በመሆኑም ፍጥረትና ትንሣኤ የእግዚአብሔር ማንነትና የሥራዎቹ ማረጋገጫ ማኅተሞች ወይም አሻራዎች ሲሆኑ፥ ያለ እነዚህ ነገሮች ሁሉም ነገር ምስጢር ሆኖ ይቀራል። እነዚህ ሁለቱ ነገሮች (ማለትም ፍጥረትና ትንሣኤ) ከምንም ነገር አንዳች ነገር መፍጠር እንዲሁም የሞተን ነገር ዐዲስ ፍጥረት አድርጐ ማንሣት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ የሚያስረግጡ ናቸው። ይህን እውነት ኤድዋርድ የተባለ ጸሐፊ፥
ትንሣኤ በእግዚአብሔር ኀይል ብቻየተከናወነ ነገር መሆን አለበት። ከእግዚአብሔር በስተቀር ፍጥረተ አካልንና ነፍስን ከምንም ሊፈጥር የሚችል ማንም የለም። ይህ ነገር በፍጥረት ዓለም ውስጥ በራሱ ሊሆን ይችላል ተብሎ ሊታሰብና ሊገመት የማይቻል ነው። በመሆኑም ትንሣኤን በየትኛውም ዐይነት ማስረጃ ለማስደገፍ ጥረት ቢደረግም እንኳን፥ ትንሣኤ ከሁሉ በላይ የእግዚአብሔርን ጣት ወይም ችሎታ የሚያሳይ ክሥተት ነው
በማለት ገልጾ ነበር (394)።
የትንሣኤን እውነት በተመለከተ ነገሩ እንዲህ ነው፥ እግዚአብሔር አጽናፈ ዓለሙንና በውስጡ ያሉትን በሙሉ በሉዓላዊ ኀይሉ ከምንም ነገር እንደፈጠረ እናውቃለን። ይህን እውነት ከተረዳን ደግሞ፥ ርሱ በሁሉን ቻይነቱ የሰው ልጆች ክፉ ጠላት የሆነውን ሞትን ጭምር ስለመርታቱ እነገነዘባለን። ስለዚህም የርሱን ሉዓላዊ ኀይልና ሁሉን ቻይነት ላለማመን ምክንያት ሊኖረን አይችልም። የፍጥረትን አፈጣጠርና የትንሣኤን ክሥተት ስናነጻጽር ሁለቱም ተመሳሳይ ነገሮች ናቸው። ትንሣኤ ከፍጥረት ሥራው ያነሣ ድርጊት አይደለም። ትንሣኤና የፍጥረት ሥራ ሁለቱም እግዚአብሔር በቃሉ ኀይል እውን ያደረጋቸው ነገሮች ናቸው።
እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን የመፍጠር ኀይልና ችሎታ እንዳለው ማመን፥ ርሱ በሕይወትና ሞት ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑን ማመንን ይጠይቃል። ይህን እውነት ሐዋርያው ጴጥሮስ፥ “የሕይወት መገኛ የሆነውን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤” በማለት ይናገራል (ሐዋ. 3፥16)። በፍጥረት ሥራና በትንሣኤ መካከል ስላለው ቀጥተኛ ግንኙነት በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ ቈላስይስ 1፥15-18 ባለው ክፍል ኢየሱስን፥ 1) የሁሉ ነገር ፈጣሪና መገኛ ምንጭ፣ እንዲሁም ፍጥረት ሁሉ ተጋጥሞ የቆመበት መሠረት፣ 2) የሁሉ ነገር መጀመሪያና ከሙታንም በኩር አድርጐ ያቀርበዋል።
ነገሩን ሰፋ ባለ መልኩ ስናየው፥ የፈጣሪ አምላክ ሁሉን ቻይነት ፍጥረታት በሙሉ ከሚያስቡትና ከሚጠብቁት ያለፈና እጅግ የላቀ ሆኖ ይገኛል። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አባት የሆነው ተርቱሊያን፥ “[ፍጡራን] ስለ እግዚአብሔር ዕውቀቱ አላቸው፤ ነገር ግን ይህ ዕውቀት ደካማ ዕውቀት ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ ስለ እግዚአብሔር ያላቸው መረዳት ርሱ እነርሱ በሚያስቡበት ልክ ብቻ እንደሚሠራ ከማሰብ የመነጨ ነው” ብሎ ነበር (38፣ ANF 3:573)። ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን አማኞች በጻፈው መልእክቱ፥ “እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው እንደ ኀይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፣ … በዘመናት ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ክብር ይሁን፤ አሜን” በማለት ያውጃል (ኤፌ. 3፥20)።
የእግዚአብሔር ሙታንን የማስነሣት ሥራው፥ አጽናፈ ዓለምን ከመፍጠር ሥራው ያነሣ ተደርጐ ሊታይ ይችላል። በመሆኑም አንዳንዶች፥ “ትንሣኤ ተኣምራዊ ሥራ ቢሆንም አካላዊ ፍጥረትን እንደመፍጠር ከምንም ነገር የተገኘ አይደለም” በማለት ይሞግታሉ (ሼድ፣ 481_82)። የሙታንን አካላዊ ትንሣኤ በተመለከተ፥ “የሰው ልጅ አካል ከመጀመሪያው ይልቅ ለሁለተኛ ጊዜ ዘላለማዊ ሆኖ ይኖራል” ቢባል ስሕተት አይደለም። ያን አካል መጀመሪያ በመለኮታዊ ኀይሉ ከምንም የፈጠረው አምላክ የመጀመሪያ ሥራውን እንደገና በመድገም የሞተውን አካል አንስቶታል (ሼድ፣ 868)። ተርቱሊያን ይህን እውነት ውብ በሆነ መልኩ፥
እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ከምንም ነገር ሊፈጥር ከቻለ፣ ሞቶ የበሰበሰውን ሥጋችንን እንደገና ማስነሣይ ይቻለዋል። በሌላ አነጋገር፥ ሌሎች ነገሮችን ከምንም ነገር መፍጠር ከቻለ፣ ለሞተው ሥጋችን ድምፁን በማሰማት ሕያው ማድረግ ትንሣኤ መስጠት ይቻለዋል። በርግጥ ከባዱ ነገር ኖሮ የሞተውን ሕያው ማድረግ ሳይሆን ከምንም ነገር ዐዲስ ነገር መፍጠር ነው። በርግጥ ይህ እውነት በምርህ ደረጃ ስናየው፥ የሞተን ሥጋ እንደገና አስነሥቶ ከማደስ መጀመሪያ መፍጠር ይቀላል
በማለት አስቀምጦታል(ተርቱሊያ 11; ANF, 3:553)፡፡
ትንሣኤ በሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ኀይል የተከናወነ ክሥተት ነው
መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ገደብ የለሽ ኀይል ጋራ በተያያዘ የክርስቶስን ትንሣኤ ባሕርያት በመጨረሻው ዘመን ከሙታን በሚነሡ አማኞች ትንሣኤ ጋራ አቆራኝቶ ጠላቅ ያለ እውነት ያቀርባል (1ቆሮ. 15፥35-53)። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን እውነት በሚገልጽበት በዚህ ክፍል፥ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚመጡትስ በምን ዐይነት አካል ነው?” የሚሉ ጥያቄዎችን ይጠይቃል (ቁ. 35)። ጳውሎስ እነዚህን ጥያቄዎች በሚመልስበት ጊዜ፥ ትንሣኤ አንድ ዐይነት ባሕርይ ብቻ ያለው ነገር ሳይሆን ብዙ ዐይነት ባሕርያት እንዳሉት ያወሳል፤ ምክንያቱ ደግሞ ሥጋ ሁሉ አንድ ዐይነት አይደለምና ነው። ጳውሎስ የሰው ሥጋ፣ የእንስሳት ሥጋ፣ የወፎች ሥጋ፣ የዐሣ ሥጋ የተለያየ መሆኑን እንደ ማጽኛ ምሳሌ ያቀርባል (ቁ. 39)። በመጨረሻው ዘመን ትንሣኤ የአማኞች አካል ሕያው ሆኖ ይወጣ፤ (1ቆሮ. 15፥51)። በሌላ ቋንቋ፥ የአማኞች ሥጋ ዐዲስ ይሆናል፤ ወይም ወደ ዐዲስ ፍጥረትነት ተለውጦ የተፈጠረት ልዩ ዓላማ በብቃት ለመፈጸም የሚያስችል ይሆናል።
የቀደመው ማንነታችንና ተፈጥሯዊው አካላችን ወደ ዐዲስና የተሻለ ማንነት መለወጥ ሳያስፈልገው፣ መንፈሳዊው አካላችን ግን ከእግዚአብሔር ሐሳብ ጋራ ሊስማማ በሚችል መልኩ ፍጹም የሆነውን ዐዲሱን የሕይወት መጠይቅ ማሟላት በሚችልበት ሁኔታ እንደገና ይቃኛል (1ቆሮ. 15፥44)። በመሆኑም በመጀመሪያ፥ ከሙታን የሚነሡ አማኞች ልክ እንደ ኢየሱስ አካል የከበረ የትንሣኤ አካል ሆኖ ይለወጣል። ሁለተኛ፥ ይህ ዐይነቱ ትንሣኤ እንዴት ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ መነሣቱ አይቀሬ ነው። ለዚህ ጥይቄ ቀላሉ መልስ፥ የሙታን ትንሣኤ ሊሆን የሚችለው በሁሉን ቻይ አምላክ በእግዚአብሔር ሥልጣንና ኀይል ብቻ ነው የሚል ነው። ይህ ማለት በአጭሩ እግዚአብሔር በሁሉን ቻይነቱ ይህን ማድረግ ይችላል ማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን እውነት፥ “እርሱም ሁሉን ለራሱ ባስገዛበት ኀይል፣ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል” በማለት ይገልጻል (ፊልጵ. 3፥20)።
እግዚአብሔር ተፈጥሮን ማደስ ከቻለ፥ ትንሣኤ አስቸጋሪ አይደለም
“በዓለም ታሪክ መጨረሻ በሚሆነው ትንሣኤ እያንዳንዱ ግለ ሰብ የራሱን አካል በሚገባ ያውቀዋል” ይላል ግሪጎሪ ዘኒሳ የተሰኘ የቤተ ክርስቲያን አባት። እግዚአብሔር የሰውን ነፍስ ከሞት በኋላ እንኳን የራሱን አካላዊ ማንነት መገንዘብ በሚችልበት ሁኔታ እንደፈጠረው ግሪጎሪ ያምን ነበር። በሌላ ቋንቋ፥ እግዚአብሔር እያንዳንዱን ነፍስና ሥጋ/አካል አንዱ ለሌላው አስፈላጊና ርስ በርሳቸው ተመጋጋቢ እንዲሆን አድርጐ ቃኝቶታል። በመሆኑም በሙታን ትንሣኤ ወቅት የሰው ነፍስና ሥጋው/አካሉ በአምላኩ በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደገና አንድ ይሆናሉ፤ የተለያዩ የአካል ክፍሎችም በፍጥነት በመሰብሰብ አንድ ላይ ይጣመራሉ። በዚህ ሐሳብ ላይ መገንዘብ ያለብን ዋናው ነጥብ ይህ ነው፤ ሁሉን ቻዩ አምላክ በሞት ምክንያት የተለያየውን የአማኞችን ነፍስና ሥጋ/አካል ማምጣትና አንድ በማድረግ ዘላለማዊነትን ማጐናጸፍ ይችላል፤ ይህን ተግባሩን ደግሞ የሚያደነቅፈው ኀይል የለም።
እያንዳንዱ ነገር እኛ ልንለካውም ሆነ ልንገነዘበው በማንችል መልኩ በእግዚአብሔር ኀይና ችሎታ የሚንቀሳቀስ ነው። ከእኛ ዐቅምና ዕይታ በላይ የሆነ ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ዐቅምና ችሎታ በላይ አይደለም (ግሪጎሪ፣ 2.5፡417)። ሁሉም ነገር የሚደገፈውና የሚወሰነው በአምላካችን ዓላማና ሥልጣን መሠረት ነው። ርሱን የሚያቅተው ወይም የሚያዳግተው ነገር የለም። ነገሮች በሙሉ ትርጒምና ስሜት ሊሰጡን የሚገባው ከዚህ የተነሣ ነው። ከላይ ግሪጎሪ እንዳመለከተው፥ እግዚአብሔር ተፈጥሮን ማደስ ከቻለ፥ ለርሱ ለሙታን አካላዊ ትንሣኤ መስጠት አይከብደውም። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የሰውን ዘር ካለመኖር ወደ መኖር እንዳመጣና ከርሱ ጋራ ኀብረት ማድረግ እንዲችል እንዳደረገው በማውሳት በግልጽ ያስተምረናል። ይህ ኀብረት ደግሞ እያንዳንዱ ሰው በሙሉ ማንነቱ ከእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዓላማ በታች እንዲኖር የሚያደርግ ነው። ከሙታን የሚነሣው የትንሣኤ አካል፥ ከእግዚአብሔር ጋራ፣ እንዲሁም ርስ በርሳችን በፍቅርና በአንድነት እንድንኖር የሚያስችል ነው። በዚህ ሕይወት እያንዳንዳችን ርስ በርሳችን እየተደጋገፍን ከክርስቶስ ጋራ አንድ በመሆን እንኖራለን። እንደ እግዚአብሔር ልጆች፣ እንደ ክርስቶስ ወንድሞችና እህቶች በፍቅርና በአንድነት እንጂ፥ በጥላቻና አንኖርም፤ በዚህም በዙሪያችን ለሚኖሩ መልካም ምሳሌና ምስክሮች እንሆናለን።
[1] White, ‘Resurrection of the Dead,’ 746.
ምዕራፍ 7
የኢየሱስ ትንሳኤ እውነተኝነት
ጠለቅ ያለው ታሪካዊ ማስረጃ
ከታሪክ ጠቃሚ ጎኖች አንዱ የወደፊት ጉዳይ የሚወሰነው ባለፈ ጊዜ በተደረጉ ነገሮች ዕውቀት ላይ መሆኑ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የወደፊቱን የዓለና የሰውን ልጆች ሕይወት ወቅ የሚቻለው ከቀደመው እውነት በመነሣት ስለሆነ ነው። በሌላ ቋንቋ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ባለፉት ዘመናት በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለያዩ ስፍራዎች ስለ ተፈጸሙ ድርጊቶችና እና ስለ የሰው ልጆች መጨረሻ በግልጽ ያስተምራል።
ይህ እውነት በመጀመሪያ የክርስቶስ ትንሣኤ እውነተኛ ክሥተት መሆኑን ያስረዳናል። የክርስቶስ ትንሣኤ እጅግ ጠቃሚና መሠረታዊ እውነት ያዘለ ታሪካዊ ክሥተት ነው። ክሥተቱ ደግሞ በጊዜና በስፍራ የሆነ እውነተኛ ነው። በመሆኑም የክርስቶስን ትንሣኤ ከታሪካዊ እውነታ ለማፋታት መሞከር፥ ክርስትናን ራሱ ከክርስቶስ አገዛዝና መንግሥት ውጪ ለማድረግ መጣር ይሆናል።
በመሆኑም የክርስቶስ ትንሣኤ የተለመዱ ታሪካዊ ክሥተቶችንና የተፈጥሮ ሕጎችን ሁሉ ዐልፎ የሚሄድ ታሪካዊ እውነት ነው። ሁሉን ቻዩ እግዚአብሔር የተለመዱ ተፈጥሯዊ ሕጎችንና ደንቦችን በሙሉ በመጣስ በክርስቶስ ትንሣኤ ድንቅ ተኣምራዊ ሥራውን ሠርቷል። የክርስቶስ ትንሣኤ ከሰዎች ጥበብና መረዳት፣ እንዲሁም ከተፈጥሮ ሂደት በላይ የሆነ ክሥተት ነው። በተጨማሪም ክሥተቱ ከእግዚአብሔር የማዳንና ፍጥረትን የማደስ ሥራ ጋራ የተቆራኘ ነው።
ይህን እውነት በተመለከተ ዋርፊልድ የተሰኘ ጽሐፊ፥ “ክርስትና የትኛውንም ዐይነት ሃይማኖት ተክቶ የቆመ የእምነት ተቋም ሳይሆን፥ በተለየ መልኩ እግዚአብሔር ዓለምንና ኀጢአተኞችን ለማዳንና ለመዋጀት ያወጣው ዕቅድ ላይ የተመሠረተ ታሪካዊ ክሥተት ነው። በመሆኑም በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ውስጥ የክርስቶስ ትንሣኤ መሠረታዊውን ስፍራ ይይዛል” በማለት ገልጿል (541-42)።
ከክርስቶስ ትንሣኤ ጋራ ተያይዞ የተለያዩ ዐይነት ነገረ መለኮታዊና ታሪካዊ ጒዳዮች ይነሣሉ። ሆኖም ግን የክርስቶስን ትንሣኤ በተመለከተ የትኛውም ዐይነት ተግባራዊና ታሪካዊ እውነታዎችና ማስረጃዎች ቢነሡና ለውይይት ቢቀርቡ፥ ክሥተቱን ማብራራት የሚቻለው በተፈጥሯዊ መንገድ ሳይሆን በግልጠተ መለኮታዊና ሥነ መለኮታዊ መንገዶች ብቻ ነው። በርግጥ የክርስቶስ ትንሣኤ ተኣምራዊ የመለኮት ሥራ ቢሆንም፥ ከሌሎች ክሥተቶች ተለይቶ ለብቻው ሊታይ የሚገባው ነገር አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ የክርስቶስ ትንሣኤ በታሪክና በተፈጥሯዊ ሂደቶች ውስጥ ሊካተት የሚካተትና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሌሎች ታሪካዊ ክሥተቶች ጋራ ተጣምሮ የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ኀይልና ግብሩን መግለጥ የሚችል እውነት ስለሆነ ነው። ስለዚህም ይህ እውነት ከግልጠተ መለኮታዊና ሥነ መለኮታዊ መንገድ በተጨማሪ በሳይንሳዊና አመክንዮአዊ መንገድም ጭምር ሊጠናና ሊብራራ የሚችል ነው።
የታወቀን እውነታ ምርጡ ማብራሪያ
ስለ ጒዳዩ ልዩ ልዩ ምሁራን ካጠነቀሩት ጥብቅ ታሪካዊ አመለካከቶች ጋራ አያይዘን ስንመለከት፥ የኢየሱስ ትንሣኤ በጣም ሰፊና ከባድ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህን እውነት በተመለከት አስተማማኝና ርግጠኛ መረጃዎችን የምናገኘው ከዐዲስ ኪዳን ዘገባዎች ነው። በርግጥ በዘመናችን የክርስቶስን ትንሣኤ ታሪካዊነት በአሳማኝ ማስረጃዎች አስደግፈው አሳማኝ በሆነ መልኩ የሚያቀርቡልን በርካታ የዐዲስ ኪዳን ምሁራን አሉ። ይህን እውነት በተመለከተ ኦደን የተባለ ጸሐፊ፥
ከታሪካዊው የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በላይ በጥንቃቄ የተዘገበ የኢየሱስ የማንነትና የአገልግሎቱ ገጽታ የለም። የክርስቶስ ትንሣኤ በጣም አስፈላጊና መሠረታዊ ከመሆኑ የተነሣ፥ ታሪካዊ ማስረጃዎቹ በጥንቃቄ ተዋቅረው ከቀደመው የክርስቲያን ማኅበረ ሰብ የድነት አዋጅ ጋራ በመጣመር ለትውልዶች እንዲተላለፍ ተደርጓል። በመሆኑም ከወንጌላት ትረካዎች በቀዳሚነት የምንረዳው የክርስቶስን ትንሣኤ ካልሆነ፥ ወንጌል በወጒ አልተረዳንም ማለት ነው
በማለት ገልጾ ነበር (ኦደን፣ 2:495)።
የክርስቶስ ትንሣኤ በማስረጃ መረጋገጥ አለበት የተባለ እንደሆን፥ “ማረጋገጫ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማብራራት ይጠበቅብና። ትንሣኤ አንድ ሰው፥ “ማረጋገጫ” ለሚለው ነገር በሰጠው የራሱ ፍቺ መሠረት የሚረጋገጥ ከሆነ፥ ትንሣኤ በማረጋገጫ ያለመረጋገጥ ስሜት አለው። ትንሣኤ፥ “ከክሥተቱ በፊትም ሆነ በኋላ በተፈጸሙ በየትኛውም ነገር የሚመሰል አይደለም፤ የሰው ሥራ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሥራ እንደመሆኑ መጠን ሙሉ ለሙሉ እጅግ ልዩ ክሥተት ነው።”[1] ይህ እንዲህ ሆኖ ሳለ ግን፥ ትንሣኤ በታሪክ ውስጥ የተከናወነ ነገር እንደመሆኑ መጠን ስለ ክሥተቱ መረጃዎችን ማጠናቀር፣ አሳማኝ በሆነ መልኩ መሟገትና እውነትነቱን መቀበል ይቻላል። ትንሣኤ በታሪክ የተፈጸመ የማይካድ እውነት ሲሆን፥ በበርካታ የዐይን ምስክሮች ምስክርነት የተረጋገጠ ነው።
የክርስቶስን ትንሣኤ እንዳንጠራጠር የሚያደርጒ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎች፣ የዐይን ምስክሮችና ሌሎችም ማረጋገጫዎች አሉ። በሌላ ቋንቋ የክርስቶስን ትንሣኤ ያለ ምንም ጥርጥር እውነተኛ ታሪካዊ ክሥተት አድርገን እንድንቀበል የሚያደርጒ በርካታ ማስረጃዎች አሉ (ስዊንበርግ፣ 126)። የክርስቶስን ትንሣኤ ታሪካዊነት የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። ይህን እውነት ስዊንበርግ፥
እግዚአብሔር መኖሩን ያለ ምንም መጠራጠር ርግጠኛ ሆነን ማመን ከቻልን፥ የክርስቶስን ከሙታን መነሣት ርግጠኛ ሆኖ ለማመን ምስክር አያስፈልግም። በርግጥ ባዶ መቃብሩና ከትንሣኤ በኋላ ርሱን የተመለከቱ በርካታ የዐይን ምስክሮች፣ ርሱ ያደረጋቸው ንግግሮችና ከዐይን ምስክሮቹ ጋራ ያድረገው ኅብረት ነገሩን በበቂ ሁኔታ እንድንገነዘብ የሚያደርግ በቂ ምስክር ነው። በመሆኑም ክርስቶስ ከሙታን መነሣቱን የሚያጸኑልን እንዲህ ዐይነት ምስክሮች ካሉልን፥ ይህ እውነት በክርስቶስ ትምህርቶችና ሥራ ላይ ያረፈ የእግዚአብሔር አሻራ እንደሆነና አድርገን ማጠቃለል እንችላለን
በማለት ያቀርባል።[2]
በሌላ ጐኑ ደግሞ አንዳንዶች፥ “ክርስቶስ ከሙታን ስለ መነሣቱ ርግጠኛ መሆን ብቻ ሳይሆን፥ ማወቅ አንችልም” በማለት ሌላ አማራጭ ሐሳብ በማቅረባቸው ምክንያት፥ የክርስቶስ አካላዊ ትንሣኤ ሊፈጸምም ላይፈጸምም ይችላል በሚል ሊታይ ይችላል። እንደ እነዚህ ሰዎች ሙግት ከሆነ፥ የክርስቶስ ትንሣኤ የሐሰት ፍልስፍና፣ ተራ ሃይማኖታዊ ልምምድና የፈጠራ ተግባር፣ እንዲሁም ከቀደሙት አስተሳሰቦች የተወረሰ ግምታዊ ቅዥትና የመልካም ምኞት መግለጫ ብቻ ነው። በሌላ ጐኑ ደግሞ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞቱን የማይቀበሉ፣ እንዲሁም ደግሞ ሬሳው በደቀ መዛሙርቱ መሰረቁን የሚገልጹ አመለካከቶችን የሚከተሉ ሰዎች ትንሣኤውን ለማጣጣል ጥረት ያደርጋሉ። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የክርስቶስ ትንሣኤ ስለ ክሥተቱ እውነተኝነት ማብራሪያ ሊሰጡ በሚችሉ በበርካታ ማስረጃዎች የተረጋጋጠ ጒዳይ ነው። በሌላ ቋንቋ፥ ስለ ጒዳዩ ስናስብ ሌላ ምንም አማራጭ ክርክር ወይም ሙግት ለማቅረብ መሞከር ፋይዳ የለውም።
አራት ተሟሟይ ሐቲቶች
ዐዲስ ኪዳን ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ አራት የተለያዩ ጒዳዮችን ያትታትል። የክርስቶስን ሕይወትና ሥራ የዘገቡ የተለያዩ የወንጌላት ጻሓፊዎች ሥራቸው አንዱ ከሌላው ጋራ ተናቦ ስለመመዝገቡ ሳይጨነቁ በራሳቸው መንገድ ጽፈዋል። የወንጌላት ትረካ ርስ በርሳቸው የሚጣረሱ የሚመስሉ አንዳንድ ዘገባዎች ያሉት ቢሆን፣ ከሌሎች ታሪኮች በተለየ የክርስቶስን ትንሣኤ በተመለከት መልእቶቹ ልዩ ዐይነት ባሕርይ አላቸው። ልዩ ልዩ ጒዳዮች እንዴት መዘገብ እንዳለባቸው የሚገራ መርህ ስላልነበር፥ ከወንጌላት መካከል አንዱ ብቻ ስለ ትንሣኤውም ሆነ ስለ ሌላ የኢየሱስ ታሪክ ሙሉ ማጠቃለያ አይሰጠንም። በመሆኑም አንዳንድ ትንሣኤውን የሚቃወሙና የሚተቹ ሰዎች በወንጌል ውስጥ የተገለጹትን ሌሎች እውነታዎችን ጭምር ሲቃወሙ ይስተዋላሉ። በወንጌላት ውስጥ የተፈጠሩ የሚመስሉ አንዳንድ ልዩነቶች የተፈጠሩበት ምክንያት የወንጌላት ጸሐፊዎች መረጃዎቻቸውን የሰበሰቡት ከተለያዩ የዐይን ምስክሮችም ባህሎችና በጊዜው በቀላሉ ከተገኙ ምንጮች ሲሆን፣ መረጃዎቹን ያጠናቀሯቸው ከክርስቶስ ሕይወትና አገልግሎት ጋራ የሚስማማ ሆኖ ስለተገኘ ነው። ይህን እንጂ ደግሞ ሁሉም የወንጌላት ጸሐፊዎች የክርስቶስን ትንሣኤ ሲዘግቡ በቦታና በጊዜ የተከሠተ እውነተኛና የማያጠራጥር ታሪካዊ ክሥተት ስለመሆኑ ርግጠኛ በሆነ መልኩ ዘግበዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም ወንጌላት፥ 1) የክርስቶስ መዋብር ባዶ ስለመሆኑ፣ 2) የትንሣኤው ዜና የመጀመሪያ አብሳሪዎች ሴቶች ስለመሆናቸው፣ 3) ከትንሣኤው በኋላ ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ መካከል እየተገኘ ልዩልዩ ንግግሮችን ስለማድረጉ ዘግበዋል።
አራት ዓይነት የማያከራክሩ ሃቆች
የክርስቶስ ትንሣኤን እውነተኝነትና ታሪካዊነት በተመለከተ፣ ትንሣኤው በማስረጃ የተደገፈና የማያከራክር ሃቅ ነው። የክርስቶስን ትንሣኤ በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብን በተመለከተ፣ በጒዳዩ ላይ ጥናት ያድረጒ በርካታ ምሁራን የሚስማሙበትና አዎንታዊ በሆነ መልኩ የሚቀበሉት ነው። ይህን በሚገባ መረዳት ሌሎች መላምቶች በሙሉ ለሚገነቡበትና ጥንካሬ ለሚያገኙበት ታሪካዊ እውነት ጠንካራ መሠረት ነው (ሊኮና፣ 617)። እነዚህ ታሪካዊ እውነቶች፥ 1) ኢየሱስ የሞተው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ነው፤ 2) ኢየሱስ ተቀብሮ የነበር ሲሆን፣ ከቀናት በኋላ መቃብሩ ባዶ ሆኗል፤ 3) ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ወዲያው ለበርካታ ተከታዮቹ ታይቷል፤ ከዚህም የተነሣ የትንሣኤውን ኢየሱስ ያዩና የሰሙ ደቀ መዛሙርት ሌሎች ሰዎች በትንሣኤው ኢየሱስ እንዲያምኑ ዐውጀዋል እና 4) ጌታ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ ከበርካታ ጊዜያት በኋላ ለጠርሴሱ ጳውሎስ በመገለጥ ሕይወቱን ለውጧል የሚሉ ናቸው።
ከላይ ያየናቸው ሁለቱ ነጥቦች በበርካታ ምሁራን እንደ ታሪካዊ እውነታ የሚወሰዱ ናቸው። በመሆኑም ኢየሱስ መሞቱና መቀበሩ፣ የደቀ መዛሙርቱ ተስፋ መቁረጥ፣ የመቃብሩ ባዶ መሆን እና የትንሣኤው ኢየሱስ ለጠርሴሱ ጳውሎስ ተገልጦ ጳውሎስ ከዐመፁ በርሱ ወደ ማመን እንዲለወጥ ማድረጒ በበርካታ የታሪክ ጻሐፊዎች ዘንድ ጭምር ቅቡልነት ያለውና በጠንካራ ድጋፍ የታገዘ ታሪካዊ ሃቅ ነው። ይህ እውነት የክርስቶስን ትንሣኤ የሚያምኑት ብቻ የሚቀበሉት ሳይሆን፣ በትንሣኤው ክርስቶስ በማያምኑት ዘንድ ጭምር ቅቡልነት ያለው ነው።
ሙሉው አካላዊ ማስረጃ
ነገሩ እንዲህ ከሆነ፣ ሙሉው አካላዊ ማስረጃ ከሌሎች ለብቻቸው መታየት ከሚችሉ በርካታ ማስረጃዎች ጋራ ተጣምሮ ሊቀብር ይችላል።
- የኢየሱስ ሞት
- የኢየሱስ የመቃብሩ ስፍራ
- ባዶ መቃብር
- ከትንሣኤው በኋላ የታየባቸው ሁኔታዎች
- ከትንሣኤው በኋላ ዐይተው ያመኑ የዐይን ምስክሮች
- የትንሣኤውን ኢየሱስ ያዩና የሰውሙ ደቀ መዛሙርቱ የሕይወት ለውጥ
- የካሃዲውና ዐመፀኛው ጳውሎስ በትንሣኤው ኢየሱስ መገለጥ መለወጥ
- በዘመኑ በነበረው ዓለም የነበሩ አማኞች በሙሉ እሁድን የአምልኮ ቀን አድርጐ የመቀጠል ልማድ
- ትንሣኤውን ተከትሎ የክርስትና እምነት መጀመሪያ በከፍተኛ ፍጥነት መስፋፋት
- ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ትንሣኤውን ሐሰተኛ ክሥተት ለማድረግ ሲደረግ የነበረው ሙከራ ያለመሳካት
- ትንሣኤውን በተመለከት ቅቡልነት ያላገኙ አማራጭ ንድፈ ሐሳቦች
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩ እውነቶች የክርስቶስን ትንሣኤ በተመለከተ እያንዳንዳቸው በየራሳቸው በቂ መረጃ መሆን የሚችሉ ቢሆንም፣ ከሁሉ በላይ ትንሣኤውን እውነተኛ የሚያደርገው ግን ትንሣኤው ራሱ እውነተኛ ታሪካዊ ክሥተት መሆኑ ነው። ከእነዚህ ሁሉ አንድ ላይ የተጠናቀረው ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጹ ዘገባዎች የላቀ እጅግ አስገራሚ ክብደት ያለው አማራጭ ማስረጃ ይሰጣል። ይህ አማራጭ ማስረጃ እጅግ ውስብስብና የትንሣኤውን እውነተኝነት ለማስረገጥ ከተጻፉ ከሌሎች ማስረጃዎች ጋራ ፈጽሞ የማይነጻጻሩና ከፍተኛ ቅቡልነት ማግኘት የሚችሉ ናቸው።[3] በመጨረሻም፣ የትንሣኤውን ታሪካዊነት በተመለከተ የሚኖረን ፍርድ፥ “በጊዜው የነበረው የክርስቶስ ተከታትይ ማኅበረ ሰብ ኢየሱስ ከሞት ተነሥቷል የሚል ሐሰተኛ የሆነ ሕያው ትርክት ፈትሯል” ወይም “ሕያው የሆነው ክርስቶስ ትንሣኤውን ተቀብሎ የሚያምንና የሚያስታውስ ማኅበረ ሰብ ፈጥሯል” ከሚሉ ከአንዱ ወገን ሊወድቅ ይችላል።[4]
ባዶው መቃብር
ሁሉም ወንጌላት የትንሣኤውን ትርክት የጀመሩት ኢየሱስ የተቀበረበት መቃብር ባዶ ሆኖ መገኘቱን በመዘገብ ነበር። ለምሳሌ፥ 1) በመቃብሩ ስፍራ ከመላእክት ጋራ የተገናኙ ሴቶች ክርስቶስ ከሙታን እንደተነሣና መቃብሩ ባዶ መሆኑን መስክረዋል፤ 2) ማቴዎስ 28፥11 ላይ የመቃብሩ ጠባቂዎች ክርስቶስ መነሣቱንና መቃብሩ ባዶ መሆኑን መስክረዋል።
በአንጻራዊነት የክርስቶስ መቃብር ባዶ ሆኖ መገኘት እንደ የትኛውም የተለመደ ክሥተት ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ ከሁሉ በላይ ያልተለመደውና ትልቁ ቁም ነገር ኢየሱስ ከሙታን ተነሥቶ መገኘቱ ነው። በሰው ልጆች ታሪክ የተለወደው ነገር ማንኛውም የሞተ ሰው በተቀበረበት መቃብሩ ውስጥ መኖሩ ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በመቃብሩ ውስጥ ተፈልጎ ሊገኝ አልቻለም። በእግዚአብሔር ኀይል ከሙታን ባይነሣ ኖሮ አስከሬኑ መቃብሩ ውስጥ ይገኝ ነበር። በመሆኑም ክርስቶስ ከሙታን መነሣቱን የማይቀበሉ ወይም የሚክዱ ሁሉ ስለዚህ ጒዳይ መፍትሒ ሊያመጡ ይገባል። ርሱ በእግዚአብሔር ኀይል ከሙታን ያልተነሣ ከሆነ አስከሬኑ የት ሄደ?
ኢየሱስ በርግጥም ሞቶ ነበር
የእስልምናው ሃይማኖት መጽሐፍ በሆነው በቁራን እንደሚታሰበው፣ “ኢየሱስ የእውነት አልሞተም” የሚለው አስተሳሰብ እስከዚህ ዘመን ሊቆይ የተገባ አልነበረም። አንዳንዶች እንደሚያስቡት ኢየሱስ የሞት በመምሰል አልተሰውረም። ርሱ በርግጠኝነት ሞቶ እንደነበር የመቃብሩ ክሥተቶች ብቻ ሳይሆኑ ስለ ሞቱ የተተረኩ ትርክቶች በሙሉ የማይካዱ እውነቶች ናቸው። የክርስቶስ ኢየሱስ የክስና የሞቱን ሂዳተ ያስተባብር የነበረው የሮም መቶ አለቃ ጲላጦስ ኢየሱስ የእውነት ለመሞቱ አንዱ ማስረጃ ነው (ማቴ. 15፥39፡44-45)። የወንጌላት ጸሐፊዎች፣ በተለይም ማርቆስ የኢየሱስን ሞት የተጠቀመው የግሪክ ቃል ptōma የሚል ሲሆን፣ ይህም “አስከሬን” ማለት ነው፤ በተጨማሪም የኢየሱስ አካል ሞት ወይም ሞተ የሚል ነው (ማር. 15፥43-45)። ይህም የሚያስረግጠው ኢየሱስ የእውነትም መሞቱን ነው። የኢየሱስ ሞት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ማንኛውም የሞተ ሰው፣ አስከሬኑ መቀበሩም ርግጥ ነው።
ከጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶችና የነገረ መለኮት ምሁራን አንዱ የሆነው አትናቴዎስ እንዳለው የክርስቶስ ትንሣኤ ወዲያው በድንገት የሆነ አይደለም። ትንሣኤው የሆነው ኢየሱስ ከሞተ ከሦስት ቀናት ወይም ከ36 ሰዓታት በኋላ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ መሞቱ ርግጥና ምንም ዐይነት ጥርጣሬ የሚያጭር አይደለም። በእውነት የክርስቶስ አካል ሞቶ ነበር (26; ed. St. Vladimir’s, 56)። ርሱ ሞቱ ሙሉ ለሙሉ ሳይሞት ወዲያው ቢነሣ ኖሮ፥ ሞቱን ማንም አያምንም ነበር (ብራክል፣ 627)። በሌላ ጐኑ ደግሞ ክርስቶስ ከሦስት ቀናት በላይ ለሆነ ጊዜ ዘግይቶ ከሙታን ቢነሣ ኖሮ በወቅቱ በዙሪያው የነበሩ ሰዎች በየፊናቸው ስለሚበታተኑ ስለሞቱ የሰጡትን ምስክርነትም ሆነ ከሙታን የተነሣው አካል የክርስቶስ መሆን ያለመሆኑን በርግጠኝነት መመስከር ባልቻሉ ነበር (አቴትናቴዎስ፣ 56)
በመሆኑም ለክርቶስ ትንሣኤ ጊዜ ወይም የወቅቱ ሁኔታ ጭምር ተጽእኖ ነበረው። ክርስቶስን የሰቀሉ ሰዎች ጭምር በዐይኖቻቸው ያዩትም ሆነ በጆሯቸው የሰሙት ነገር ከህልናቸው ደብዝዞ ሳይጠፋ፣ እንዲሁም ርሱን ስለ መስቀላቸው ትኲስ ምስክርነት እየሰጡ ሳለ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ከሦስት ቀናት በኋላ የማይበሰበስና የማይሞት አካል ይዞ በአስደናቂ ሁኔታ ከሙታን ተነሣ።
ኢየሱስ በርግጥ ተቀብሮም ነበር
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከተሰቀለ በኋላ መሞቱ ርግጠኛ ሆኖ ሲረጋገጥ አስከሬኑ በአርማቴናዊው ዮሴፍ ተወስዶ እንደተቀበረ ከወንጌላት ዘገባ መረዳት እንችላለን (ማቴ. 27፥57-61፤ ማር. 15፥42-47፤ ሉቃ. 23፥50-56፤ ዮሐ. 20፥38-42)። በወቅቱ በነበሩት አይሁዶች ወግ እና ባህል ከባባድ ወንጀሎችን የሠሩትን ጭምር መቅበር ትልቅ ትርጒም ነበረው (ዊሊያምስ፣ 133)። የሞተውን አካል ለቀብር ማዘጋጀት ከባድ ኀላፊነት ነው (ዮሐ. 19፥39_40)። በተጨማሪም የቀብር ሥርዐቱ ውድ ዋጋ ተከፍሎበት በልዩ ጥንቃቄ የሚደረግ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት፣ በዘመኑ በነበረችው ኢየሩሳሌም ለቀብር ስፍራነት የሚሆኑ ድንጋዮች በጣም ውድ በመሆናቸው ነው። የኢየሱስ አስከሬን የቀብር ሥርዐት የተፈጸመው እንደ አንድ ተርታ ሰው ቀብር ሳይሆን፣ በሕዝብ ዘንድ በሀብታምነቱ በሚታወቅና ትልቅ ተጽእኖ ፈጣሪ በሆነው በአርማታዊው ዮሴፍ እና ጲላጦስ በተባለው የመንግሥት ባለ ሥልጣንና አገረ ገዥ ነው።
የክርስቶስ መቃብር በወታደሮች ኀይል ይጠበቅ ነበር
የአርማቲያው ዮሴፍ የኢየሱስን መቃብር በትልቅ ድንጋይ ዘግቶት ሲሆን፣ መቃብሩም በወታደሮች እንዲጠበቅ ተደርጐ ነበር። መቃብሩን እንዲጠብቁ ስንት ወታደሮች እንደተመደቡ ባይታወቅም፣ መቃብሩ በጲላጦስ ትእዛዝ መኀተም እንዲደርግበት ተድርጎ እሰከ ሦስተኛው ቀን ድረስ በወታደሮች ይጠበቅ እንደነገር ግን ግልጽ ነው።
መቃብሩ ማኀተም ተደርጐበት በወታደሮች በጥንቃቄ ይጠበቅ የነበረው፣ አስከሬኑ በተከታዮቹ እንዳይሰረቅ በሚል ነበር። በመሆኑም ጠባቂ ወታድሮችን ዐልፎ የጲላጦስን ማኅተም በማስወገድ አስከሬኑን ለመስረቅ የሚደፍር ሰው ሊኖር አይችልም። በተጨማሪም የመቃብሩ ጠባቂዎች የኢየሱስ ጠላቶች ናቸው። ይህን እውነት ማቴዎስ፥
በተደጋጋሚ አትኩሮች ተሰጥቶበት እንደተነገረው ክርስቶስ የተቀበረበት ሥፍራ በክርስቶስ ጠላቶች በራሳቸው ነበር ተጠብቆ የነበረው፡፡ ይህን ጉዳይ ማቴዎስ፥ “ሴቶቹ በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ከጠባቂዎቹ ጥቂቶቹ ወደ ከተማ በመሄድ የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩላቸው። የካህናት አለቆችም ከሽማግሌዎች ጋር ተሰብስበው ተማከሩ፤ ለወታደሮቹ በቂ ገንዘብ በመስጠት እንዲህ አሏቸው፤ ‘ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት’ በሉ፤ ይህ ወሬ በገዥው ዘንድ ቢሰማ እንኳ፣ እኛ እናስረዳዋለን፤ ምንም ክፉ ነገር እንዳይደርስባችሁ እናደርጋለን። ወታደሮቹም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ ታዘዙት አደረጉ። ይህም ታሪክ እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁዶች ዘንድ በሰፊው እንደ ተሠራጨ ነው” በማለት ጽፏል (ማቴ. 28፥11_15)። በመሆኑም የክርስቶስ ትንሣኤ እውነተኝነቱ ተረጋግጦ የተመሰከረውና የታወጀው በኢየሱስ ወዳጆች ሳይሆን በጠላቶቹ ነው።
ወደ ባዶው መቃብር መመልከት
ከወንጌላት ጸሐፊ አራተኛው የሆነው ዮሐንስ በትንሣኤው ወቅት ወደ ኢየሱስ መቃብር ስፍራ ቀድሞ የደረሰው ሰው መቃብሩ ባዶ ሆኖ እንዳገኘውና በመቃብሩ ውስጥ ከፈኑን ብቻ እንዳየ ጽፏል (ዮሐ. 20፥8)። ይህን ድንቅ ነገር ካየ በኋላ፣ ይህ ያየው ደቀ መዝሙር ጌታ ከሞት መነሣቱን ወዲያም እንዳመነ እንመለከታለን። በሌላ ቋንቋ፣ በኢየሱስ መቃብር ውስጥ ከፈኑ ብቻ መቅረቱ ኢየሱስ ከሙታን መነሣቱን ያስረግጣል ማለት ነው። ስለዚህም የኢየሱስ መቃብር ባዶ መሆን በሚከተለው መልኩ አጠር ተደርጐ ሊቀርብ ይችላል፤
- የኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ የመቀበሩ ታሪካዊ እውነታ መቃብሩ ባዶ የመሆኑን እውነት ያስረግጥልናል።
- የኢየሱስ መቃብር ባዶ የመሆን ታሪክ በቀደሙ ምንጮች ለየብቻው ተዘግቧል።
- መቃብሩ ባዶ መሆኑን ሴቶች አይተው መስክረዋል።
- አይሁዶች ለደቀ መዛሙርቱ አስቀድመው የሰጧቸው ምላሽ የኢየሱስ መቃብር ባዶ መሆኑን ያስረግጣል።[5]
የኢየሱስ መቃብር ባዶ ሆኖ መገኘት ለብቻው የትንሣኤ ማረጋገጫ ሊሆን ባይችልም፣ ስለ ጒዳዩ ቀዳሚና ጠቃሚ መረጃ ሊሆን ግን ይችላል። መቃብሩ ባዶ እስከሆነበት ቀን ድረስ አስከሬኑ በዚያ ስፍራ መሆኑን የሚቀበል ማንኛውም ሰው ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጐ መነሣቱን መቀበል አይቸግረውም (ክሬግ፣ 263)።
ሌሎች አማራጮች ለማመን የሚቸግሩ ናቸው
የኢየሱስ ክርስቶስን መቃብር ባዶ ሆኖ መገኘት በተመለከተ የሚቀርቡ ሌሎች ሁለት አማራጭ አመለካከቶች አሉ። የመጀመሪያው ክርስቶስ የእውነት አልሞተም የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስ መቃብር ባዶ እንደሆነ የተናገሩት የመቃብሩን ስፍራ ስለማያውቁ የተሳሳተ መቃብር አግኝተው ነው የሚል ነው። በተጨማሪም የኢየሱስ አስከሬን በወዳጆቹ ወይም በጠላቶቹ እንደተሰረቀ የሚያምኑም አሉ፤ እንዲሁም የኢየሱስ አስከሬን በደቀ መዛሙርቱ እንደተሰረቀ የሚናገሩም አሉ። እነዚህን አመለካከቶች የሚሰነዝሩ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ሞት ጥልቅ ግንዛቤ የሌላቸው፤ ወይም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ርሳቸው ለፈጠሩት ሐሰተኛ ወሬ ጭምር ለመሞት ዝግጁ እንደሆኑ አድርገው የሚያስቡ ናቸው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መቃብሩ ባዶ ነው የሚል የሐሰት ወሬ ፈጥረው አሰራጭተዋል የሚሉ ሰዎች፣ ትርክቱ ሆን ተብሎ የተወጠነ የሐሰት ሴራ ስለሆነ ዘለቄታ የሌለው ነው፤ በመሆኑም ጫና እና ስደቱ ሲበዛባቸው ሐሰትነቱ ይገለጣል ይላሉ። ነገር ግን በወቅታዊ ሁኔታ ተገፋፍተው ሐሰትን በማመን ወደ አንዳች ዐይነት ውድድር ውስጥ የገቡ ሰዎች ለሞት የሚያበቃ መከራ ለመቀበል ፈቃድኛ አይሆኑም። ከዚህ በተቃራኒ ግን አየሱስ ከሞት ተነሥቷል እውነት ለሐዋርያት ተጨባጭ ግላዊ እውነት ስለሆነ ለዚህ እምነታቸው ለመሞት ዝግጁ ነበሩ። በተጨማሪም ክሥተቱ ታሪካዊ ስለመሆኑ ጠንካራ ሙግት ማቅረብ ይቻላል።[6]
የድኅረ ሞት መገለጥ
የባዶ መቃብሩ ታሪክ ብቻውን የኢየሱስን ትንሣኤ ሙሉ ለሙሉ ሊገልጠው አይችልም። ከሁሉ አስቀድማ መቃብሩ ጋራ የተገነችው መግደላዊት ማሪያም የኢየሱስን አስከሬን በመቃብሩ ውስጥ ስታጣ በመቃብሩ አጠገብ ለነበረው መልአክ የተናገረችው የመጀመሪያው ነገር አስከሬኑ ተሰርቆ ሊሆን ይችላል የሚል ነበር (ዮሐ. 20፥13)። ነገር ግን ለማሪያም ጥያቄ ግልጽ መልስ የሰጠው ሌላ አካል ሳይሆን የትንሣኤው ኢየሱስ ራሱ ነበር። ስለዚህም ማሪያም ኢየሱስ የእውነትም እንደተነሣ ያመነችው ባዶ መቃብር አይታ ብቻ ሳይሆን የትንሣኤው ኢየሱስ ተገልጦ በማየቷም ጭምር ነበር (ዮሐ. 20፥14-18)። የትንሣኤ ኢየሱስ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው መቃብሩ በነበረበት የአትክልት ስፍራ ነው።
የትንሣኤው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በተለያዩ ስፍራዎች ለተለያዩ ጊዜያት ተገልጦ ኅብረት አድርጐ፣ ተደጋጋሚ ትምህርቶችንና መመሪያዎችን ሰጥቶ ነበር (ማቴ. 28፥1-20፤ ማር. 16፥9-19፤ ሉቃ. 24፥1-53፤ ዮሐ. 20፥19-21፥25፤ ሐዋ. 1፥3-9)። የትንሣኤው ኢየሱስ በመጀመሪያ የታየው በተለያዩ የኢየሩሳሌም መንደሮች ሲሆን፣ ቀጥሎም በገሊላና በአካባቢው ይታይ ነበር (ማር. 16፥7)። ሉቃስ የትንሣኤውን ኢየሱስ በተመለከተ፥ “… እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ ለመረጣቸው ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የሰጣቸው ትእዛዝ ነው። ከሕማማቱም በኋላ ራሱ ቀርቦ ሕያው መሆኑን፣ ለእነዚሁ በብዙ ማስረጃ እያረጋገጠላቸው አርባ ቀንም ዐልፎ ዐልፎ እየታያቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነገራቸው” ይላል (ሐዋ. 1፥2-3)። በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ የትንሣኤውን ኢየሱስ በተመለከተ፥ “እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ ከገሊላ ጀምሮ እስከ ኢየሩሳሌም ከእነርሱ ጋር ለነበሩትም ብዙ ቀን ታያቸው፤ እነርሱም አሁን ለሕዝቡ ምስክሮቹ ናቸው” ይላል (ሐዋ. 13፥30)። በመሆኑም እነዚህና ሌሎች የትንሣኤው ኢየሱስ ከተለያዩ ሰዎች ጋራ በተለያዩ ስፍራዎች በቀጥታና ግልጽ በሆነ መልኩ ያደረጋቸው ኅብረቶች፣ ትምህርቶችና መመሪያዎች ርሱ ሕያው መሆኑን ማሳያ ናቸው (ካልቪን፣ 3.25.3፡ 991)።
ቢያንስ ዐሥራ አራት የተለያዩ አጋጣሚዎች
የትንሣኤው ኢየሱስ በተለያዩ መንገዶች ራሱን የገለጠ ቢሆንም፣ እያንዳንዱ ክሥተት ግን አልተመዘገበም ነበር። ዐዲስ ኪዳን ከክርስቶስ እርገት በፊት የተከናወኑ ዐሥራ አንድ መገለጦችንና እርገቱን ተከትሎ የመጡ ሦስት ክሥተቶችን በአጠቃላይ ዐሥራ አራት ክሥተቶችን ዘግቦልናል። 1) ለመግደላዊት ማሪያም መታየት (ማቴ. 28፥1፤ ማር. 6፥19፤ ዮሐ. 20፥11-18)፤ 2) ከመቃብሩ ስፍራ ሲመለሱ ለነበሩ ሴቶች መታየት (ማቴ. 28፥2፤ 8-10)፤ 3) ለጴጥሮስ መታየት (ሉቃ. 24፥34፤ 1ቆሮ. 15፥5)፤ 4) ለሁለቱ የኤማሁስ መንገደኞች መታየት (ማር. 16፥12-13፤ ሉቃ. 24፥13-31)፤ 5) ከቶማስ ውጪ ለነበሩ ደቀ መዛሙርት መታየት (ሉቃ. 24፥36-43፤ ዮሐ. 20፥19)፤ 6) ቶማስን ጨምሮ ለደቀ መዛሙርቱ መታየት (ማር. 15፥14፤ ዮሐ. 20፥26-29)፤ 7) በጥብሪያዶስ ባሕር ላይ ዓሣ ሲያጠምዱ ለነበሩ ደቀ መዛሙርት (ለስምዖን ጴጥሮስ፣ ለቶማስ፣ ለናትናኤል፣ ለያዕቆብ፣ ለዮሐንስ እና ሌሎች ሁለት) መታየት (ዮሐ. 21፥1-23)፤ 8) በገሊላ ተራራ አካባቢ ለነበሩ ዐሥራ አንድ ደቀ መዛሙርት መታየት (ማቴ. 28፥16)፤ 9) እስከዚያው ቀን ድረስ በሕይወት ለነበሩ ለዐምስት መቶ ያህል ወንድሞች መታየት (1ቆሮ. 15፥6)፤ 10) ለያዕቆብ መታየት (1ቆሮ. 15፥7)፤ 11) በእርገቱ ወቅት በዙሪያው ለነበሩ የዐይን ምስክሮች መታየት (ማቴ. 28፥18-20)፤ 12) ለእስጢፋኖስ መታየት (ሐዋ. 7፥55)፤ 13) ለጳውሎስ መታየት (ሐዋ. 9፥17፤ 1ቆሮ. 15፥8) እና 14) በፊጥሞ ደሴት ላይ በነበረበት ወቅት ለዩሐንስ መታየት (ራእ. 1፥9-12)።[7]
የዚህ ዐይነቱ ተመክሮ ልዩ ባሕርዩ ምንድን ነው?
የኢየሱስ ትንሣኤ የመጀመሪያ የዐይን ምስክሮችና ከትንሣኤው በኋላ የተገለጠላቸው ሰዎች ነገሩን እንዴት ተረዱት? ይህን በተመለከተ በርካታ አማራጭ ምላሾ ሊቀርቡ ይችላሉ፤
- የጒዳዩን እውነተኛውንዓላማ በርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። በርግጠኝነት ማወቅ የሚቻለው ደቀ መዛሙርቱን ነገሩን እንዴት እንደተረዱትና እንዴት ይፋ ሊያወጡ እንደቻሉ ብቻ ነው።
- ክሥተቱን በተመለከተ ደቀ መዛሙርቱና ሌሎች የዐይን ምስክሮች ትንሣኤው እውነት እንደሆነ አምነው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ነገሩ በትክክል የተረጋገጠ እውነት ሊሆን አይችልም።
- የእያንዳንዱ ክሥተት ታሪካዊነቱ (ለምሳሌ፦ ባዶው መቃብር) ተፈትኖ ልረጋገጥ ይችላል። ነገር ግን ሌሎች ጒዳዮች ከጥርጣሬ ባለፈ ታሪካዊነታቸውን ማስረገጥ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።
- ታሪካዊነታቸውን በበቂ ማስረጃዎች ማረጋገጥ የሚቻልባቸው ክሥተቶች አሉ (ለምሳሌ፦ ባዶ መቃብርና ከትንሣኤው በኋላ በርካታ የዐይን ምስክሮች ማየታቸው)።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ አመለካከቶች ሁሉም ጠቃሚ ቢሆኑም፣ አራተኛው ነጥብ ግን ከሁሉ ይልቅ የተሻለና የትንሣኤው እውነታዎችን መግለጽ የሚችል ነው።
ሐዋርያት በነፍሳቸው ለመወራረድ ዝግጁ ነበሩ
ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ዘገባዎች ታሪካዊ ተኣማንነት በተመለከተ ምሁራን የተለያዩ አመላካከቶችን ይሰጣሉ። ስለ ትንሣኤው ርግጠኝነት የተዘገቡ አራት ምክንያቶችን እንደምከተለው እንመልከት፤
- ሐዋርያት የትንሣኤውን ታሪካዊነትና ተኣማኒነት በማመን ለዚህ እውነት እስከሞት ድረስ ነፍሳቸውን ለመስጠት ዝግጁ ነበሩ የሚለው ከሁሉ የላቀ መከራከሪያ ነው። ሐዋርያት የትንሣኤውን ኢየሱስ በተለያዩ ጊዜያት ስለማየታቸውም ሆነ ርሱ ለሌሎች በርካታ ሰዎች እንደታየ ርግጠኛ ነበሩ። በዚህም ርግጠኛ እምነት ምክንያት ሰማእት ለመሆን ጭምር ዝግጁ ሲሆኑ፣ በእምነታቸው እስከ መጨረሻ ጸንተዋል። በርግጥ ሰማእትነት ለክርስቲያኖች ዐዲስ ነገር ባይሂንም፣ ማክ ዶናልድ እንዳለው ለክርስትና ዐዲስ ነገር አስቀድመው በራሳቸው ላዩትና ላመኑት ነገር ሐዋርያት ነፍሳቸውን መስጠታቸው ነው። የሐዋርያት እምነት የተመሠረተው ከሌሎች በሰሙት ምስክርነት ላይ ሳይሆን እነርሱ ራሳቸው ሞትን ድል አድርጐ ከተነሣው ኢየሱስ ጋራ የነበራቸው ኅብረት ነው። በተጨማሪም ያመኑት የትንሣኤ ጌታ እውነተኛ መሲሕ ስለ ነበር፣ ነፍሳቸውን ሙሉ ለሙሉ በዚህ እምነት ላይ አሳርፈው ነበር (ማክ ዶናልድ፣ 261፤ 265)። በመቀጠልም ማክ ዶናልድ፣
ሐዋርያቱ የሞቱት ከሙታን የተነሣውን የትንሣኤውን ኢየሱስ ራሳቸው ዐይተው በማመናቸው ነው … እነዚህ ሐዋርያት ተሳስተው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ለዚህ እምነታቸው ሰማእት ለመሆን መወሰናቸው እምነታቸው ምን ያህል በርግጠኛ እውነት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ እና አምላካቸውም ታማኝ እንደሆነ ማሳያ ነው። ሐዋርያት ዋሾዎች አይደሉም። ከሙታን የተነሣውን ጌታ ዐይተውና አምነው መስክረዋል፤ እስከሞት ለመጽናት ፈቃደኛ በመሆን ይህን እምነታቸውን ገለጹ። አንዳንዶች ደግሞ ለዚህ እምነት ሞቱ። እነዚህ ሐዋርያት ከእምነታቸውና ለአምላካቸው ከነበራቸው መሰጠት ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸውን የሚያሳይ ምንም ዐይነት ማስረጃ የለም። በርግጥ ይህን ስንል ደግሞ እነርሱ በሁሉም ነገር ፍጹም ናቸው ማለት አይደለም። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ስለመነሣቱ ርግጠኛ ስለነበሩ ሕይወታቸው በዚህ እውነት ላይ የተመሠረተ ነበር (ማክ ዶናልድ፣ 3፡125)።
የትንሣኤው ኢየሱስ መገለጥ ገጽታዎችና ቁጥር
ነገሩን እንደ ወረደ ከወሰድነው፣ የተለያዩ ሰዎች ከሞት የተነሣውን ኢየሱስን እንዳዪ የገለጹ ዘገባዎችንና ግልጽ የሆኑ ቁጥሮችን ከባዶ መቃብር ጋራ አንድ ላይ አድረገን ስናጠናቅረው፣ የክርስቶስ ትንሣኤው እውነተኛ ታሪካዊ ክሥተት ስለመሆኑ ጠንካራ ማስረጃ መገንባት እንችላለን።
ይህን እውነት በተመለከተ ወንጌላት የተለያዩ ሐሳቦች የሚሰነዝሩ ቢሆንም፣ በትንሣኤው ክሥተት እውነትነትና ታሪካዊነት ላይ ግን ዘገባዎቹ ስምሙ ናቸው። ከዚህ በፊት እንዳወሳነው፣ የወንጌላት ጸሓፊዎች መረጃዎቻቸውን ያጠናቀሩት በተለያዩ መንገዶች ቢሆንም፣ ስምሙነታቸው ግን መሠረታዊ ችግር አይደለም። ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ለበርካታ ሰዎች ስለ መታየቱ በወንጌላት በተለያዩ መልኮች የዘገቡ በመሆኑ አከራካሪ ነጥቦች መነሣታቸው የሚጠበቅ ነው። የወንጌላት ጸሓፊዎች ከትንሣኤው በኋላ ስለሆነው የኢየሱስ መገለጥ ያቀረቧቸው ሐሳቦችና ምስክርነቶች በመጠኑ የተለያዩ ይመስላሉ። በርግጥ ስለ ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ መታየት በተመለከተ በርካታ አስገራሚና አስደናቂ ገለጻዎች ተዘግበዋል። ለምሳሌ ሂል ዊሊያምስ የተሰኘ ጸሐፊ፥
ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ በይሁዳና በገሊላ ከተሞች ገጠራማ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በቤትና በውጪ በጠዋትና በማታ መታየቱን፣ በቀጠሮም ሆነ ያለቀጠሮ በከፍታ ስፍራዎች፣ በባሕር ዳርቻ፣ በቅርብም በሩቅም፣ ሴቶች ጭምር በተገኙበት ጉባኤያት መገኘቱ በግልጽ ተዘግቦልናል። የትንሣኤው ኢየሱስ በእነዚህ ስፍራዎችና ጉባኤዎች ሲቀመጥ፣ ሲቆም፣ ሲራመድ፣ ከእነርሱ ጋራ መዕድ ሲቆርስና ሲነጋገር እንደነበር ተጽፏል። ርሱ በተገለጠባቸው ስፍራ የነበሩ ሰዎች ከትንሣኤው ኢየሱስ ጋራ ስለመነጋገራቸውም ተገልጿል። የትንሣኤው ኢየሱስ ባልተገለጠበትና ሰዎች ባላዩበት እንዲሁም ስለ ክሥተቱ ምስክርነት ባልሰጡበት ሁኔታ በወንጌላትና በመልእክቶች ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቷል ተብሎ ሊጻፍ ችሏል ብሎ ማመን እጅግ ከባድ ነው
በማለት ገልጿል።[8]
መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ስለመነሣቱና ሕያው ስለመሆኑ፣ እንዲሁም መጀመሪያ በኢየሩሳሌም፣ ቀጥሎም በገሊላና አካባቢው በግልጽ ለተለያዩ ሰዎች ስለመታየቱ የዐይን ምስክሮችን ዘገባ ያቀርብልናል። እነዚህ ክሥተቶች ቢያንስ ለዐሥራ አንድ የተለያዩ ጊዜያትና ሁኔታዎች ስለመፈጸማቸው ሐዋርያው ጳውሎስ ጠቅለል አድርጐ አቅርቦልናል (1ቆር. 15፥5-8)። ስለ ትንሣኤው ኢየሱስ የሚሰጡ የዐይን ምስክሮች ዘገባ ከግለ ሰብ ወደ ቡድን፣ እንዲሁም ከቡድን ወደ ጉባኤ እያደገ የሚሄድ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በአንድ ጊዜ ከዐምስት መቶ ለሚበልጡ ሰዎች ስለመታየቱ በግልጽ ተዘግቧል (1ቆሮ. 15፥6)።
ስለዚህም የትንሣኤው ቡድናዊ ተመክሮ፣ ማለትም ከጥቂት ቡድን እስከ በርካታ ሕዝብ የትንሣኤውን ኢየሱስ ማየታቸው ቡድናዊ ቅዥት ወይም ግላዊ ስሕተት ተደረጐ እንዳይወሰድ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። መጀመሪያ፣ ወንጌላት ደቀ መዛሙርቱ በተስፋ መቁርጥና ጥርጣሬ ውስጥ ስለመሆናቸው፣ እንዲሁም የትንሣኤው ኢየሱስ ሲገለጥላቸው ለማመን ያመነቱም ነበሩ። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ከሙታን እንደሚነሣ በእምነት ይጠብቁ ነበር ብሎ ማመን አስቸጋሪ።[9] ሁለተኛ፣ ወንጌላት በሚጻፉበት ወቅት በሕይወት ከነበሩና የትንሣኤውን ኢየሱስ መገለጥ በጋራ ከተለማመዱ ከተለያዩ ምንጮች የተሰበሰቡ ልዩ ልዩ ዘገባዎችን ሆን ተብሎ በተወጠነ መልኩ ለማታለልና ለማሳሳት የተጠናቀሩ ናቸው ብሎ ማሰብ ማለት እጅግ ከባድ ነው። ሦስተኛ፣ በተለያዩ ጊዜያት በልዩ ልዩ ስፍራዎች የሚገኙ ሰዎች የጋራ ቅዥትና አእምሮ ፈጠር ምኞች ሊሆን የሚችልን ነገር ከግብ ፈጥረው ሰዎችን ለማሳሳት ተባብረው አድመዋል ብሎ ማመን ከሁሉ በላይ አስቸጋሪና ከባድ ነው።
የትንሣኤው የመጀመሪያ የዐይን ምስክሮች ሴቶች ነበሩ
በይሁዳ ቦታ ሐዋርያ ለመተካተ በተደረገው የምርጫ ሂደት እንደ መስፈርት ሆኖ የቀረበው የትንሣኤው ኢየሱስ በማየት የዐይን ምስክር መሆን ነበር (ሐዋ. 1፥22)። የትንሣኤው የመጀመሪያ የዐይን ምስክርች ሁለቱም ማሪያም ተብለው የሚጠሩ ሴቶች ነበሩ (ማቴ. 27፥61፤ 28፥1)። እንደ ሉቃስ 24፥11 ዘገባ ከሆነ የሁለቱም ማሪያሞች እና የሌላ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ዮና ምስክርነት አንንድ ላይ ሲታይ ከመደነቅና ከፍርሀት የተነሣ ነገሩን ለማመን እንደከበዳቸው የሚያሳይ ነበር (ማር. 16፥3-4፡8)። ተከታዮቹ በርግጥም ኢየሱስ ከሙታን እንደተነሣ ያመኑት የትንሣኤውን ኢየሱስ በተደጋጋሚ ከተመለከቱ በኋላ ነበር (ሉቃ. 24፥31፡36)። ነገር ግን ሁሉም ወንጌላት ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ የታየባቸው በርካታ ክሥተቶች በታሪካዊነታቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆኑ የዘገቡ ሲሆን፣ በመጀመሪያም የታየው ለሴቶች (በተለይም ለመግደላዊት ማሪያምና ለያዕቆብ እናት ማሪያም) ስለመሆኑ በግልጽ ዘግበዋል (ማቴ. 28፥1፤ ማር. 16፥1፤ ሉቃ. 23፥55-24፥1፤ ዮሐ. 20፥1-11)። እነዚህ ሴቶች በተደጋጋሚ የክርስቶስ የመሰቀሉ፣ የመቀበሩና የባዶ መቃብሩ ምስክሮች እንደሆኑ ተጠቅሰው እንድመለከታለን (ማር. 15፥40-47፤ ሉቃ. 23፥55፤ 24፥3)።
በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ሴቶች እንደ እውነተኛና ቀዳሚ ምስክሮች ተደረገው የምታሰቡ ባይሆኑም፣ እነዚህ ሴቶች ግን የትንሣኤው ቀዳሚ ምስክሮች መሆናቸው የትንሣኤውን እውነትነትና ታሪካዊ ተኣማኒነቱን የሚያጸና ነው። በተጨማሪም በዚያ ዘመን የነበረ የአይሁዶችም ሆኑ የግሪክ ባህል ሴቶችን እንደ ታማኝ ሕጋዊ ምስክር አድርጐ አይቀበልም ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ 1ቆሮንቶስ 15፥1-8 ባለው ክፍል ኢየሱስ ከትንሣኤ በኋላ የታየባቸውን ሁኔታዎችና የዐይን ምስክሮች ሲዘረዝር ሴቶችን ያልጠቀሰበት ምክንያት ከዚህ አመለካከት የመነጨ ሊሆን ይችላል። የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ጆሴፈስ ከስሜታዊነትና ደካማነታቸው የተነሣ የሴቶችና የባሪያዎች ምስክርነት እንደ ታማኝ ምስክርነት እንደማይቆጠር ገልጾ ነበር።[10] ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በማኅበረ ሰቡ የሚገኙ ባህሎችን ሁሉ በሚቃረን መልኩ የክርስቶስን ትንሣኤ ቀዳማይ ምስክሮች ከወንዶች ሐዋርያት ይልቅ ሴቶች እንደሆኑ ገልጿል። የነገሩ እውነተኝነት አስገድዷቸው ሴቶችን እንደ ቀዳሚ ምስክር ጠቀሱ እንጂ አይሁዳውያን የነበሩ የወንጌላት ጻሐፊዎች ማቴዎስና ዮሐንስ ሴቶችን እንደ ሕጋዊ ምስክር አልጠቀሷቸውም ነበር (ሲዊንበርን፣ 114)።
ከዚያም በላይ ከሥነ መለኮታዊና ከታሪካዊ እውነታ አንጻር ስንመለከተው የክርስቶስ ትንሣኤ የዐይን ምስክሮች ጒዳይ ሁለቱንም ጾታዎች ያጠቃለለ ነው። አንዳንድ ቀዳማይ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚያትትቱት ከሆነ፣ የሴቶች ምስክርነት የሚወክለው ቤተ ክርስቲስያን የክርስቶስ ትንሣኤ ቀዳሚ ምስክር መሆን እንዳለባት ነው ይላሉ (Peter Chrysologus 2002፡305)።
መገለጡ ሙሉ ለሙሉ አካላዊ ነበር
እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ገለጻ ከሆነ፣ ጌታችን ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ በተለያዩ ጊዜያት፣ ለተለያዩ ሰዎች፣ በልዩ ልዩ ሁኔታዎች መታየቱ የትንሣኤውን እውነተኝነት የበለጠ የሚያረግጥ ነው (1ቆር. 15፥5_8፡11)። ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ የታየባቸው ሁኔታዎች ግልጽና ተጨባጭ ናቸው። በተጨማሪም የትንሣኤው የዐይን ምንስክሮች የትንሣኤውን ኢየሱስ ካዩ በኋላ፥ 1) ከርሱ ጋራ ፊት ለፊት እንደተገናኙና እንደተነጋገሩ፣ 2) ርሱ ሲናገራቸው እንደሰውሙ፣ 3) ከርሱ ጋራ ለአራት ጊዜያት ያህል እንደ ተመገቡና እንደጠጡ፣ 4) ቢያንስ ለሁለት ጊዜያት በአካል አግኝተው እንደነኩት፣ 5) አያሌ ኪሎ ሜትሮችን ዐብረው እንደተራመዱና ረጅም ንግግር እንዳደረጒ አመልክተዋል። የትንሣኤው ኢየሱስ በተገለጠባቸው ስፍራዎችና ሁኔታዎች የነበሩ ክሥተቶች፥ ከሰዎች ጋራ የነበረውን ግንኙነት፣ ግልጽ ንግግሮች፣ ጠላቅ ያለ ገለጻዎችንና መመሪያዎችን ያካተተ ነበር።
ዐዲስ ኪዳናዊ ዘገባዎች የትንሣኤው ኢየሱስ የሚበላ፣ የሚተጠጣና የሚነካ አካል እንዳለው፣ ከልዩ ልዩ ሰዎች ጋራ ኅብረት መፍጠር የሚችል፣ ሰላምታ የሚለዋወጥ፣ ጥያቄዎችን ተጠይቆ የሚመልስ እንደሆነ ያትታትሉ። በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜም ለረጅም ጊዜያት ወስዶ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችን በምሳሌያዊ መንገዶች የሚያስተምር ድንቅ መለኮታዊ መምህር ስለመሆኑም ተዘግቧል። ለምሳሌ፣ በተኣምራዊ መንገድ በርካታ ዓሣዎች እንዲያዙ ማድረጒና ደቀ መዛሙርቱ እያዩ ወደ ሰማይ ማረጒ ዐቢይ ማስረጃዎች ናቸው (ኦዴን፣ 2፡489)።
አንድ ሰው የቊሳዊ ኢአማኝነትን አቋም ቢይዝ፥ ይህን እምነቱን ሊያናጋ የሚችል የማስረጃ መጠን አይኖርም። የቀረቡ ማስረጃዎችን በሙሉ መስመር በመስመር ሊሞግታቸው ይችላል፤ … ያለቀለት መርቻ ሙግት ለማቅረብ አስቸጋሪ የሆኑ በርካታ፣ ውስብስብና አሰልቺ የመጨረሻው አማራጭ የሙግት ማብራሪያዎች ያቀርባል። ከዚህ በተቃራኒ ግን በወንጌል የተዘገቡ ክሥተቶችን ታሪካዊነት መቀበል እጅግ በጣም ቀላል ነው … አንድ ሰው በእነዚህ ዘገባዎች ውስጥ የበለጠ ግንዛቤ ማግኘት ስለሚፈልጋቸው ነገሮች አንድ በአንድ እየጠየቀ ምላሽና ማብራሪያ ሊያገኝ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ደግሞ አንድና ቀላል ማብራሪያ ስለ ሁሉም ጒዳዮች ለብቻው ስሜት በሚሰጥ መልኩ አመርቂ ምላሽ ሊሆን ይችላል።[11]
ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ የተገለጠባቸው መንገዶችና ክሥተቶች በማያጠራጥር መልኩ እውነተኛና ግልጽ ናቸው (ዩሐ. 21፥1)። በተጨማሪም መገለጦቹ በቃል ጭምር የተሰናዱና ትርጒም የሚሰጡ ናቸው። የትንሣኤው ኢየሱስ የተገለጠው ርሱን ሰቅለው ለገደሉ ጠላቶቹ (ጲላጦስ፣ ቀያፋ እና ሌሎች) ሳይሆን ለወዳጆቹ ነው። እነዚህ የቅርብ ወዳጆቹ ዋናው የትንሣኤ የዐይን ምስክሮች ናቸው (ሐዋ. 10፥41)።
ተጠራጣሪው ቶማስና ተተኪዎቹ
የትንሣኤው ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ መታየቱ ሲነገር፣ በዐዲስ ኪዳን ውስጥ የመጀመሪያ የሆነውን የኢየሱስን መለኮትነት የመጠራጠር ግልጽ ምላሽ አጫረ። “የቶማስ ኑዛዜ” በማለት ልንጠራው የሚቻለው ኑዛዜ በቀጥታ የኢየሱስን መለኮታዊ ማንነት የሚመለከት ሲሆን፥ “ጌታዬ” (kyrios) እና “አምላኬ” (theos) በሚሉ ቃላት ተገልጿል (ዮሐ. 20፥28)። ቶማስ የትንሣኤው ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ ጋራ የተካከለ መለኮት እንደሆነ የተናዘዘበት ምክንያት የትንሣኤውን ኢየሱስ በሚገባ መረዳቱ ነበር (ዮሐ. 5፥23)። የክርስቶስን እውነተኛ ማንነት በሚገባ ለመረዳት ከሙታን የተነሣውን ኢየሱስን ማመን ግድ ነው።
ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በተገለጠበት ወቅት ቶማስ በስፍራው አልነበረም ነበር፤ ስለዚህም ተጨባጭ ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ ኢየሱስ ከሞት መነሣቱን እንደማያምን ገለጸ (ዮሐ. 20፥25)። ለዚህ የቶማስ ጥያቄ የትንሣኤው ኢየሱስ የሰጠው መልስ፥ 1) ቶማስ ይህን በሚናገርበት ጊዜ ርሱ በስፍራው ባይኖርም ሁሉን ነገር የሚያውቅ እንደሆነ የሚገልጥ፣ 2) ርሱ እንዲታመኑበት የሚሻ፣ አለማመንና ጥርጣሬን ለማስወገድ ፈቃደኛ በመሆን ተጠራጣሪውን ቶማስን በበቂ ማስረጃ ለመደገፍ ዝግጁ የሆነ ሕያው አምላክ መሆኑን የሚያሳይ፣ 3) የማስረጃው ሁኔታ ጥቂት እምነት በጊዜ ሂደት አለማመን ወደ ማመን እንዲቀየር ለማድረግ በቂ መሆኑን የሚያመልክት ነው። ቶማስ ወደ እምነት የመጣበት መንገድ በሕይወት ዘመኑ ርሱ ከክርስቶስ ጋራ ለነበረው ግንኙነት በጣም አስፈላጊ ነበር። በርካቶች የትንሣኤውን ኢየሱስ በአካል ሳያዩ በማመን ይድናሉ። የትንሣኤውን ኢየሱስ ሳያዩ የማመን ልምምድ ትልቅ በረከት ሲሆን፣ በታሪክ ውስጥ ከርሱ ጋራ ለሚኖር ኅብረት እጅግ ወሳኝና የብጽዕና መሠረት ነው። የዐዲስ ኪዳን አማኞችን ስንመለከት በርካቶች በትንሣኤው ኢየሱስ ያመኑት ርሱን ፊት ለፊት በማየት ሳይሆን፣ ስለርሱ በንግግርም ሆነ በጽሑፍ የተሰጡ ምስክርነቶችን በማመን ነው። የዐዲስ ኪዳን ምሁሩ ዲ.ኤ. ካርሰን በትክክል እንደገለጸው፥ ኢየሱስ ወደ ላይ ካረገ በኋላ በርካታ አማኞች ወደ ርሱ የመጡት ስለርሱ የተነገሩ ምስክርነቶች በማመን ነበር። የትንሣኤው ኢየሱስ ካረገ በኋላ ተከታዮቹ መጽሐፍ ቅዱስን ያነቡና ያንን መጽሐፍ ይሰቡ ስለነበር በርካቶች ያንን እውነት አመኑ (ካርሰን፣ 1992፡660)።
ሰንበትን መጠበቅ
ከዐስራ ሁለቱ የጌታ ሐዋርያት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ራእይ ዘመን ድረስ (ራእ. 1፥10) ስንመለከት እሁድ የጌታ ቀን ሆኖ እንደሚያሰብ እንረዳለን። ይህ ነገር በብዚዎች ዘንድ የተዘነገ ጒዳይ ቢሆንም ለክርስቶስ ትንሣኤ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ነው። የቀድሞው ክርስቲያን ወንድሞች በአንድ ላይ ተሰብስበው እንጀራ ይቆርሱና ያመልኩ የነበሩት ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ነበር (ሐዋ. 20፥7)። ይህ ልማድ በየሳምቱ ቀጥሎ የነበር ሲሆን (1ቆሮ. 16፥2)፣ ተሰብስቦ በጋራ ማእድ መጋራት የሚደረግበት ቀን የጌታ መቃብር ባዶ መሆኑ ከተረጋገጠበት ቀን ጋራ ቀጥታ የተቆራኘ ነው (ማቴ. 28፥1፤ ማር. 16፥2፡9፤ ሉቃ. 24፥1፤ ዮሐ. 20፥1፡19)።
በተለይም በአይሁድ ክርስቲያኖች የእምነት ዐውድ እሁድ ከሌሎች ቀኖች የተለየ ትኩረት የሚሰጥበት የአምልኮ ቀን ነበር። ከክርስቲና ውጪ እሁድ ቀንን ቀድሶ ሳምንታዊ የአምልኮ ቀን ያደረገ ሌላ ሃይማኖት የለም። የክርስትና እምነት እሁድ ቀንን ልዩ የአምልኮ ቀን እንዲሆን ያደረገው ከጌታ ትንሣኤ ጋራ በተያያዘ ነው፤ ምክንያቱም የጌታ መቃብር ባዶ መሆኑ የተረጋገጠውና ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጐ የተነሣው በዚያ ቀን ነውና። ቤተ ክርስቲያን የጌታ እራት የምትወስደው በእለተ እሁድ ነው (በተጨማሪም እሁድ ነገረ መለኮታዊ ፋይዳ ያለው ቀን ነው)፤ ክርስትና የክርስትና እምነት ከሆነበት ከመጀመሪያው ዓመት ጀምሮ የጌታ ትንሣኤ በእለተ እሁድ የተፈጸመ የክርስትና እምነት ማእከላዊ ክሥተት ሆኖ ሰንብቷል።[12]
እሁድ እለት ብቸኛው የክርስቲያኖች የአምልኮ ቀን የሆነበት ምክንያት የመጀመሪያዎቹ አማኞች ኢየሱስ ከሙታን የተነሣው በዚያ ቀን እንደሆነ ስላመኑ ነው። ጌታ ከተሰቀለበት ከዓርብ ቀን ጀምሮ ሲቆጠር እሁድ ሦስተኛ ቀን ይሆናል (ማቴ. 16፥21፤ 17፥23፤ 20፥19፤ 27፥64)፤ ወይም፣ “ከሦስት ቀናት በኋላ” ተብሎ ይጠራል (ማር. 8፥31፤ 10፥34፤ 14፥58፤ 15፥29)። በአይሁዶች የቀን አቆጣጠር ስልት የቀን ጥቂት ሰዓታትና ሙሉው ቀን አንድ ቀን ተብሎ ይቆጠራል። በመሆኑም ክርስቶስ ሞት ከተቀበረ በኋላ ለተወሰኑ ቀናት መቆየቱ እውን ነው። ለምሳሌ፣ ኒሳን የሚባለው ወር ዓርብ 14ኛ ቀን ሲሆን፣ እሁድ ደግሞ 16ኛው ቀን ነው፤ በመሆኑም ከዓርብና ከእሁድ ቀናት የተወሰኑ ሰዓታት ከቅዳሜ (ኒሳን 15) ሙሉ ቀን ተጨምሮ ሦስት ቀናት ይሆናሉ ማለት ነው (ኦዴን፣ 1፡627)።
ይህ አመለካከት የመጀመሪያው አማኞች እሁድን የአምልኮ ቀን አድርገው የቀደሱት የብሉይ ኪዳንን፥ “በጌታ ፊት የመሆን” የበኩራት በዓል የሚደረግበትን ቀን መሠረት አድርገው ነው (ዘሌ. 23፥9-14) የሚለውን አስተሳሰብ ተቃርኖ ይቆማል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ፥ “የሦስተኛ ቀን ተሐድሶ” የሚለው ጭብጥ ከሆሴዕ 6፥2 በመወሰድ ትንሣኤው በሦስተኛ ቀን እንደሚሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች ተናገረ (ማቴ. 16፥21፤ ሉቃ. 24፥45-46)። ትንሣኤው በርግጠኝነት በዚያ እለት ባይሆንም ደቀ መዛሙርቱ ያን ቀን እንደ ሦስተኛ ቀን አድርገው ወስደዋል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ ይህን ቀን በዚህ ሁኔታ ስለመቀበላቸው ሲታሰብ፣ በሦስተኛው ቀን አንዳች ነገር እንደሆነ ማሰብ ግድ ነው (ባቪንክ፣ 455)። በዚህ ነጥብ ላይ ማስተዋል ያለብን ትልቁ እውነት፣ የፋሲካው እሁድ እለት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ እሁድ ኢየሱስ ከሙታን የተነሣበት የጌታ ቀን እንደሆነ መቀበል እንዳለብን ነው። ምክንያቱ ደግሞ እሁድ እንደ ጌታ ቀን መቀበል ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ትልቅ ምስክርነት ስለሚሰጥ ነው።
የክርስትና እምነት ጅማሬ
የክርስትናን እምነት እና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ አማኞች በእሁድ ቀን በአንድ ላይ ተሰብስበው ማምለካቸው በእምነታቸው ጉዳይ ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ይህ የክርስትና እምነት ምንጩና መጀመሪያው ክርስቶስ ከሙታን በመነሳቱ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርትም የሚያስተምሩን በዚሁ ታሪካዊ ዘገባ ላይ ተመሥርተው ነው። በአጠቃላይ ሐዋሪያዊው እምነትና ሕይወት የተመሠረተውም በዚሁ እምነት ላይ ነው እንጂ ለክርስትና እምነት መነሣት ሌላ የተሸለ ገለጻና ማብራሪያ የለም ማለት ይቻላል
ይህ በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ የተመሠረተው እምነታቸው ነው ብዙዎችን በአጠቃላይ ወደ ሐዋሪያዊ አገልግሎት እና በተለይም ደግሞ ወንጌልን ወደ መስበክ የመራቸው። ይህም የሆነው ከትንሣኤ ክሥተት በኋላ ወዲያው ትንሣኤውን ተከትሎ ነበር። የክርስቶስ ትንሣኤ ዐዋጅም የሆነው ቀጥታ የክርስቶስን ስቅለት ተከትሎ ነበር። ይህም ጉዳይ በአፈ ታሪኮችና በባህላዊ ግምቶችና ህልሞች ላይ ሳይሆን በአጠቃላይ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ላይ በተለይም ደግሞ በወንጌሎችና በሐዋሪት ሥራ ዘገባዎች በምንመለከታቸው የዐይን ምስክሮች ምስክርነት ላይ ተመስርቶ ነው።
ሰለ ክርስቶስ እውነት ተጽእኖ ፈጣሪነትም ሆነ የወንጌሉ መልእክት መስፋፋት ጉዳይ በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ ተመሠረተ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ያለ ክርስቶስ ትንሣኤ እምነት ሁሉ ባዶ ስለሚሆን ሐዋሪቱም ምንም ዐይነት መልእክት ሊኖራቸው አይችልም። ለእውነተኛ ክርስትና ያለ ክርስቶስ ትንኤ ስለ እግዚአብሔር እውነት፣ ለኀጢአትም መፍትሒ እና ከሞት በኋላም እውነተኛ ተስፋ ሊኖር አይችልምና። ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥122-19 እንደሚያረጋግጥልን፣ ሐዋርያቱም እንደሚረዱት ያለ ኢየሱስ ትንሣኤ የክርስትና እምነት ምንም ዐይነት መሠረት የሌለው ከንቱ ነገር ይሆናል (ግርሃም 2009፣151)። ስለዚህ የክርስትና መወለድም ሆነ ማደግ በአጠቃላይ በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ የተመሠረተ ነው ማለት ይቻላል።
ፍርሀት ከሞላበት ግራ መጋባት ወደ ድፍረት የሞላበት ርግጠኝነት መለወጥ
የክርስቶስን ትንሣኤ በተመለከተ ቀዳሚ የክርስቶስ ተከታዮችም ሆነ በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ፈጽሞ ያልጠበቁት ነገር መሆኑን ማወቁ ጠቃሚ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሞቱና ትንሣኤው አስቀድሞ በተደጋጋሚ የነገራቸው ቢሆንም፣ ደቀ መዝሙርቱ ስለዚህ ጒዳይ ስላለሰቡ፣ ከክርስቶስ ሞት በኋላ ሊሆን ስላለው ነገር ምንም ዐይነት ዝግጅት አላደረጒም ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው ሲሞት በፍርሀትና ተስፋ በመቊረጥ በተቆለፈ ቤት ውስጥ ተደበቊ (ዮሐ. 20፥19)። ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ እንደተናገረው ሞቱና ትንሣኤው እውን ሆኖ ሲገኝ፣ የጌታ ተከታዮች ጭምር ግራ እንደገባቸው እናስተውላለን። የወንጌል ዘገባዎች በሙሉ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደደነገጡ፣ ግራ እንደገባቸውና በአለማመንና በመገረም እንደተሞሉ ያትታሉ (ሉቃ. 24፥11-41)።
ምንም እንኳን ጌታ የሚወደው የተባለው ደቀ መዝሙር በኢየሱስ ላይ የተለመደ እምነቱን ቢያሳይም (ዮሐ 20፥8-9)፣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ በክርስቶስ በማመን መቀጥል የመቻላቸው ጒዳይ አስቸጋሪ ሆኖ ተስተውሏል።የትንሣኤው የመጀመሪያ የዐይን ምስክር የሆነችው መግደላዊት ማሪያምክርስቶስ ሕያው እንደሆነ በነገረቻቸው ጊዜም ቢሆን ደቀ መዛሙርቱ በቀላሉ ሊያምኑበት አልቻሉም ነበር (ማር. 16፥11)። ዮሃናና የያእቆብ እናት የነበረችውን ማሪያምንና የሌሎች ሰዎች የዐይን ምስክርነት የትንሣኤውን እውንነት የሚያጸና ቢሆንም እንኳን፣ ደቀ መዛሙርቱ ግን ጒዳዩ ምንም ስሜት የሚሰጥ ነገር ሆኖ ስላላገኙት ሊያምኑና ምስክርነቱንም ወደ ሌሎች ሊያስተላልፉ አልቻሉም(ሉቃ. 24፥10-11)። ይህ አለማመን ከፍ ብሎ የምናየው ቶማስ፥ ምስማር የተቸነከሩትን የእጆቹን ምልክቶች ካላየሁ፣ ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ጣቴን ካላደረግሁ፣ በጐኑም እጄን ካላስገባሁ አላምንም” በማለት ከተናገረው ጥርጣሬ የሞላበት ንግግር ነው (ዮሐ. 20፥25)። የትንሣኤውን ጌታ በግላቸው ከመገናኘታቸው በፊት የተከታዮቹ አመለካከትና አጠቃላይ ስሜታቸው በጥርጣሬ፣ በፍርሀትና በጸጸት የተሞላ ነበር (ዮሐ. 20፥11 19 እና 25)።
ታዲያ የደቀ መዛሙርቱ ተሐድሶና ለውጥ ምክንያቱ ምንድን ነበር?
ኢየሱስ በተያዘበት ወቅት ተከታዮቹ በሙሉ ጥለውት እንደሸሹ እንመለከታለን (ማር. 14፥50)። ጴጥሮስ በሁኔታው ተደናግጦ በተደጋጋሚ ካደው (ማር. 14፥66-67)። ሐዋርያው ጳውሎስ የትንሣኤው ኢየሱስ አግኝቶች ከመሸነፉ በፊት (ሐዋ. 9፥3-7) የክርስቶአስና የቤተ ክርስቲያን ጠላትና አሳዳጅ ነበር (ሐዋ. 8፥1፡3፤ 9፥12)። ነገር ግን የትንሣኤው ኢየሱስ በተከታዮቹ ዘንድ የነበረውን ፍርሀት፣ ጸጸትና ግራ መጋባት አስወግዶ የተሰበረና የደቀቀ ልባቸውን በመለወጥ እምነታቸውን ከፍ አድርጐ ሲያነሣ እንመለከታለን። የሐዋርያት እምነትና ሕይወት ከፍርሀት ወደ ድፍረት ተለወጦ ከፍ ያለው በትንሣኤው ኢየሱስ አማካይነት ነበር። በተጨማሪም በፍርሀትና በክህደት ውስጥ የነበሩ ደቀ መዛሙርቱ ወዲያው የትንሣኤው ቀዳሚ ምስክር በመሆን በአደባባይ በድፍረት እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሙታን እንዳስነሣው መስበክ ጀመሩ (ሐዋ. 2፥31-32)። ከዚህ እምነትና ድፍረት ከሞላበት ስብከታቸው የተነሣ በአንድ ጊዜ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሕዝቦች በትንሣኤው ኢየሱስ ወደ ማመን መምጣት ጀመሩ (ሐዋ. 2፤41)። የኢየሱስ ከሙታን መነሣት ደቀ መዛሙርቱ ለክርስቶስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ የነበራቸው አመለካከት ሙሉ ለሙሉ በመቀየር ስብከትና አገልግሎታቸው ሌላ አቅጣጫ እንዲይዝ አደረገው።
ለሐዋርያቱ የወንጌል ዐዋጅ ትልቁ ተስፋና የሥልጣናቸው መሠረት የክርስቶስ ትንሣኤ ነው። የመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን ከተረዳቻቸው ነገሮች አንዱና ዋናው፣ ቀዳማይ ተልእኮዋ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ መስበክና ሌሎችም እንዲሰብኩ ማነሣሣት እንደሆነ ነው። በሌላ ቋንቋ፣ የሐዋርያት ስብከትና መልእክቶች መሠረታዊ መነሻቸው የክርስቶስ ትንሣኤ ነው። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ትንሣኤ የምታውጀው በስብከት፣ በልዩ ልዩ ሥርዐቶች (ለምሳሌ፣ ጥምቀት)፣ በቅዱስ ቊርባን ሥርዐት፣ በክርስቲያናዊ ኅብረትና በግብረ ገባዊ ሕይወት ነበር። ለዚህ የትንሣኤው ወንጌል በተለያዩ ዘመናት በርካቶች ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድረገው ሰጠተዋል። ከክርስቶስ ትንሣኤ በፊትም ሆነ በኋላ የነበሩ ደቀ መዛሙርት ለዚህ ወንጌል ሕይወታቸውን ለመስጠት ጭምር ዝግጁ ነበሩ (ሐዋ. 15፥26)።
የባለሥልጣናቱ ኀይል የሞላበት ተቃውሞ
የክርስቶስ ትንሣኤ ምስክር ከሆኑ ቀዳሚ ተከታዮች በርካቶች ክርስቶስን በቀጥታ እንዳዮትና ከርሱ ጋራ ኅብረት እንዳደረጒና ይህ ክሥተት ደግሞ ያለ ምንም ዕቅድ የሆነ ድንገቴ ነገር እንዳልሆነ ተናግረው ነበር። የእነዚህ ሰዎች ለክርስቶስ ስም ሲሉ ራሳቸውን ለመከራ፣ ለግርፋትና ለሥቃይ፣ ነፍሳቸውን ደግሞ ለመሥዋዕታዊ ሞት አዘጋጅተው ነበር። ለክርስቶስ ስም የትኛውንም ዐይነት ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ስለነበሩ በታላቅ መከራና ስደት ውስጥ ጭምር የትንሣኤውን ወንጌል የምስራች ይሰብኩ ነበር። አንዳንዶች እንደሚያስቡት የክርስቶስ ትንሣኤ አፈ ታሪክና ተረት ቢሆን ኖሮ ተከታዮቹ ራሳቸውን ለመከራና ለስደት እንዲሁም ለሞት አሳልፎ መስጠታቸው ምንም ትርጒም የሚሰጥ ነገር ባልሆነ ነበር። አንድ የሞተ ሰው ሌሎች ሙታንን በሙሉ ቀድሞ በአካላዊ ትንሣኤ ተነሥቷል የሚለው ሐሳብ (ዊሊያምስ፣ 135)[13] ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን በነበሩ አይሁዶችም ሆነ የይሁዳዊነት ትምህርት ውስጥ ያልነበረ ነበር፤ በመሆኑም የኢየሱስን ስምና ማንነት ገናና ለማድረግ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ከሞት ተነሥቷል የሚለውን ሐሳብ ፈጥረው እንዳወጁ ተደርጐ ተወሰደ። ስለዚህም ኢየሱስ ከሙታን ሕያው ሆኖ ተነሥቷል የሚለው ዐዋጅ ሐዋርያቱን ለእስራት፣ ለሥቃይ፣ ለግድያና ለከባድ አካላዊ ጒዳት ዳረጋቸው። ኢየሱስ ከሞት መነሣቱን ርግጠኛ ባይሆኑና ጥቂት ጥርጣሬ ያደረባቸው ቢሆን ኖሮ እነዚህ ሰዎች ይህን ሁሉ መከራና ሥቃይ ለመቀበልና ለሞት ራሳቸውን አሳልፈው ባልሰጡ ነበር። በተጨማሪም እውነተኛ የሆነው የትንሣኤ ሐሳብ በውስጣቸው ሥሩ ያልሰደደ ቢሆን ኖሮ የእነዚህ ሰዎች ሕይወት በዚህ መልኩ ከመሠረቱ ሊለወጥ አይችልም ነበር።
ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን ትንሣኤ ዐዋጅ ያደረጒት ኢየሱስ ተሰቅሎ በተገደለበትና በተቀበረበት የኢየሩሳሌም ከተማና በአካባቢው በነበሩ መንደሮች ነበር። በትንሣኤው ኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት እምነቱ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ መጣ። በዚህም ምክንያት የክርስቶስ ተከታዮች፥ “ዓለምን ሁሉ ያወኩ” ተብለው እስከመጠራት የደረሱ ሲሆን (ሐዋ. 17፥5)፣ እንቅስቃሴው በዘመኑ ከነበረው ከየትኛውም የሃይማኖት፣ የፖለቲካና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በላይ በፍጥነት እየተስፋፋ ገሠገሠ። ሌላው እጅግ በጣም የሚገርመው እውነት የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በተጨማሪ የዘመኑ ታሪክ ጸሐፊ በነበረው ጆሴፈስ መዘገቡ ነበር።
የክርስትና ዓላማና ታሪካዊ ሰበቡ
እንደ ኦዴን ገለጻ ከሆነ፣ ትንሣኤውን ያብራሩት ወንላቱ ሳይሆኑ፣ ትንሣኤው ነበር ወንጌላቱን ያብራራው (ኦዴን፣ 2፡451)። በመሆኑም የትንሣኤውን ጌታ በመገናኘት ሕይወታቸው የተለወጠ ማኅበረ ሰብ ባይኖር ኖር፣ የመስቀሉን ምስጢር የሚያስታውስ ማኅበረ ሰብ አይኖርም ነበር። የክርስቶስ ትንሣኤ እውነተኛ ክሥተት ባይሆን ኖሮ፣ የሐዋርያት ስብከትና ትምህርት፣ የወንጌላት ዘገባዎች በሙሉ ቅዥትና ተረት ሆነው በቀሩ ነበር። የክርስትና እምነት በመጀመሪያዎቹ ሦስት ምእተ ዓመታት ውስጥ በታላቅ መከራና ስደት ውስጥ ሆኖ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ ዓለምን ያጥለቀለ ቢሆንም፣ ክርስቶስ የእውነት ከሙታን ያልተነሣ ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ከንቱ በሆነ ነበር። የክርስትና እምነት ታሪካዊነቱ ያለ ክርስቶስ ትንሣኤ ትርጒም የለሽ ሊሆን ስለሚችል ማንም ሰው ስለዚህ ጒዳይ መናገርም ሆነ ዋጋ መክፈል ባልተገባውም ነበር።
[1] Robert C. Doyle, Eschatology and the Shape of Christian Belief (2008 edition [Orig. Paternoster, 1999]), 47; following Barth and Pannenberg.
[2] Swinburne, Was Jesus God?, 127. An apologetic case for the historicity of Christ’s resurrection draws on a wealth of resources. Various excellent materials are available at www.garyhabermas.com. Fine introductory presentations of historical evidence for Christ’s resurrection include David Baggett ed., Did the Resurrection Happen? A Conversation with Gary Habermas and Anthony Flew (IVP, 2012); William Lane Craig, Reasonable Faith: Christian Truth and Apologetics. Third edition (Crossway, 2008), 333-404; idem, On Guard: Defending Your Faith with Reason and Precision (David Cook, 2010), 219-264; Douglas Groothuis, Christian Apologetics: A Comprehensive Case for Biblical Faith (IVP Academic/Apollos, 2011), 527-566; David Gooding and John Lennox, Christianity: Opium or Truth? (Myrtlefield, 2014), 105-137; Josh McDowell and Sean McDowell, Evidence That Demands a Verdict (Thomas Nelson, 2017), chapter 10; and Swinburne, Was Jesus God?, 114-127. More developed and detailed book-length treatments include Licona, The Resurrection of Jesus; Swinburne, The Resurrection of God Incarnate; and Wright, The Resurrection of the Son of God. An excellent advanced-level analytical philosophical approach is Timothy McGrew and Lydia McGrew, ‘The Argument from Miracles: A Cumulative Case for the Resurrection of Jesus of Nazareth,’ in The Blackwell Companion to Natural Theology, eds. William Lane Craig and J. P. Moreland (Blackwell, 2009), 593-662.
[3] Swinburne, Was Jesus God?, 122-23. See Allison’s examination of some tenous sceptical arguments (The Resurrection of Jesus, 323-335).
[4] Oden, Systemat ic Theology, 485.
[5] Craig, On Guard, 263; slightly amended.
[6] An extended scholarly argument on this point is Sean McDowell, The Fate of the Apostles: Examining the Martyrdom Accounts of the Closest Followers of Jesus (Ashgate, 2015).
[7] ኦዴን፣ 1፡626
[8] Williams, Can We Trust the Gospels?, 134-35.
[9] Bavinck, Reformed Dogmatics. Abridged, 456.
[10] Flavius Josephus, Jewish Antiquities, Books 1-4, 4.219 [15]; trans. H. St. J. Thackeray (William Heineman/Harvard University Press, 1961), 581.
[11] Williams, Can We Trust the Gospels?, 133, 136.
[12] Swinburne, Was Jesus God?, 120.
Copyright © 2022 by Benjamin T. F. Dean